የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ አራት ጨዋታዎች ዛሬ ተከናውነው ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ወደ አንደኛ ሊግ ሲወርድ ቀሪዋ አንድ የወራጅ ቦታ ላይ ላለመገኘት የሚደረገው ፉክክር ቀጥሏል።
ቡታጅራ ላይ ቡታጅራ ከተማ ከ ቤንች ማጂ ቡና ያደረጉት ጨዋታ በባለሜዳው 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ወራጅ ቀጠናው ውስጥ ለሚገኘው ቡታጅራ አፈወርቅ ዮሐንስ እና ጀማል በዲሴ ሲያስቆጥሩ በድሉ በመታገዝ ከወራጅ ቀጠናው መውጣት ባይችልም ከበላዩ ከሚገኙት ቡድኖች ጋር ልዩነቱን ማጥበብ ችሏል።
ሻሸመኔ ከተማ ስልጤ ወራቤ ወራቤን አስተናግዶ ከወራጅነት ስጋት መራቅ ችሏል። የሻሸመኔን ብቸኛ የድል ጎል በ25ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ፈይሳ ከድር ነው።
ቦንጋ ላይ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭን ያስተናገደው ካፋ ቡና 4-0 በማሸነፍ ወሳኝ ሦስት ነጥብ ሲያስመዘግብ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ወደ ከፍተኛ ሊጉ ባደገበት ዓመት ወደ አንደኛ ሊግ መውረዱን አረጋግጧል።
ሌላው በዚህ ምድብ ላለመውረድ ፉክክር እያደረገ የሚገኘው ነጌሌ ቦረና ጅማ አባ ቡናን አስተናግዶ 2-0 ማሸነፍ ችሏል። ነጌሌ በድሉ ነጥቡን 22 ቢያደርስም ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ ከፍ ብሎ አሁንም ከስጋት መላቀቅ አልቻለም።
በዚህ ሳምንት ሊደረጉት የነበሩት የነቀምት ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ እንዲሁም የሀዲያ ሆሳዕና ከ ካምባታ ሺንሺቶ ጨዋታዎች በነቀምቱ ወንድወሰን ዮሐንስ ህልፈት ምክንያት ሳይከናወኑ ቀርተዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡