በከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ ወልቂጤን እየተከተለ ያለው መድን እና ላለመውረድ እየተጫወተ የሚገኘው ዲላ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ትላንት በዲላ መሪነት 2-0 በዝናብ ተቋርጦ ዛሬ ረፋድ ቀሪው 45 ደቂቃ በመቀጠል በዲላ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ተመሳሳይ የአጨዋወትን መንገድ የተከተሉት ሁለቱም ክለቦች ረጃጅም ኳሶችን ወደ ፊት ተሰላፊዎቻቸው በመጣል ለመጠቀም ያለመ እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን የዲላ ከተማዎች ደግሞ ይበልጥ የተሳካ ነበር። በተለይ በቀኝ በኩል ተሰልፎ ሲጫወት የነበረው ዘመድኩን ሽርኩ ከእግር ሲነሱ የነበሩት ኳሶች ለመድን ተከላካዮች ፈተና ሲሆን ተመልክተናል፡፡ መድኖች 6ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል በለጠ ከቀኝ ማዕዘን ያሻገረውን ኳስ አቤል ማርቆስ ቢያገኛትም በቀላሉ ያመከናት የመጀመርያዋ ሙከራ ስትሆን 9ኛው ደቂቃ አምበሉ ምስጋናው በግራ የዲላ የግብ ክልል ወደ ግብ ያሻገራት ኳስ አብዱለጢፍ ሙራድ ጋር ደርሳ ተጫዋቹ ወደ ግብ ቢመታውም ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ ይዞበታል። ዳግም ኳሷን ከያዘ በኃላ በረጅሙ ሲለጋው ሀብታሙ ፍቃዱ ጋር ደርሳ ተጫዋቹ ጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረው ዳዊት ተረፈ ሰጥቶት አማካዩ የመድን ግብ ጠባቂ ጆርጅ ደስታን አቋቋም ተመልክቶ ከሳጥን ውጪ ግሩም ግብ አስቆጥሮ ዲላን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ ሁለተኛ ግብ እስኪያክሉ ድረስ በይበልጥ ረጃጅም ኳስ ላይ ትኩረት ያደረጉት ዲላዎች 22ኛው ደቂቃ ተጨማሪ ጎል አስቆጥረዋል። ዘመድኩን ሺርኮ በቀኝ አቅጣጫ በረጅም ወደ መድን የግብ ክልል ያሳለፋትን ኳስ አጥቂው ኤደም ኮድዞ በደረቱ አብርዶ ሲያመቻችለት አማካዩ ፋሲል አበባየሁ ከመጀመሪያው ጋር ተመሳሳይ የሆነ ግብ አስቆጥሮ ዲላን ወደ 2-0 ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡
ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ ወደ ጨዋታ ለመመለስ የተከላካይ ክፍላቸውን ወደ አማካይ ክፍሉ አማካዮቹን ወደ አጥቂዎቹ በማስጠጋት አጥቅተው ለመጫወት የሞከሩት መድኖች በርካታ አጋጣሚን እያገኙ ወደ ግብ መለወጥ አልቻሉም። 29ኛው ደቂቃ ጀሚል ያዕቆብ በረጅሙ አሻግሮ ምስጋናው በግንባር ገጭቶ ለጥቂት አግዳሚውሙየን ነክታ የወጣችበት እና አጥቂው አብዱለጢፍ ሙራድ ከግብ ጠባቂው ዳግም ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ዳግምን አልፎ በቀላሉ ያመከናት ለብልጫቸው ማሳያዎች ናቸው፡፡
የመጀመሪያው አጋማሽ በዲላ 2-0 ከተጠናቀቀ በኃላ ወደ እረፍት ቢያመሩም ሜዳው በጎርፍ በመሞላቱና ለጨዋታ እጅጉን ምቹ ባለመሆኑ በእለቱ ዋና ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ እና በረዳቶቹ አማካኝነት የሁለቱም አምበሎች እና ቡድን መሪዎች ጋር ከተነጋገሩ በኃላ ጨዋታው ወደ ዛሬ 4:00 ሰአት ተቀይሮ ሁለተኛው አጋማሽ ተካሂዷል፡፡ የዛሬው ጨዋታ ቀሪው ደቂቃ ከመደረጉ በፊት መድኖች ሜዳው ለጨዋታ ምቹ አደለም በሚል ቅሬታን ያቀረቡ ቢሆንም ሜዳ ደረቅ እስኪል ድረስ 45 ደቂቃዎችን ዘግይቶ ነበር ሊጀመር የቻለው። መድኖች በድጋሚ ጨዋታው ሊጀመር ሲል የዲላ ከተማ ቡድን መሪ አለመገኘቱን በመጥቀስ በሌላ መለወጡ አግባብ እንዳልሆነ በመግለፅ ክስ ያስመዘገቡ ሲሆን የእለቱ ኮሚሽነር ቡድን መሪው በድንገተኛ ችግር ምክንያት በደብዳቤ መለወጡን አሳውቀውናል በማለት ምላሽ ከሰጡ በኃላ በእለቱ ዳኛ ቢኒያም መሪነት የዛሬው ጨዋታ ጀምሯል፡፡
ከትላንት እንቅስቃሴያቸው በተለየ በሙሉ የማጥቃት ኃይላቸው ወደ ሜዳ የገቡት መድኖች በዲላ ላይ ፍፁም የሆነ ብልጫን ወስደዋል፡፡ ዲላዎች ደግሞ አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት ከሚያደርጉት አጋጣሚዎች በስተቀር የኋላ መስመራቸውን በማስጠበቁ ተጠምደው ውለዋል፡፡ መድኖች በርካታ ጊዜያቸውን በዲላ የሜዳ ክፍል ውስጥ ባሳለፉበት ጨዋታ 49ኛው ደቂቃ ዮናታን ብርሀነ በቀኝ በኩል የላካትን ኳስ ጀሚል ያዕቆብ ቢያገኛትም በቀላሉ አምክኗታል፡፡
ሜዳው ኳስን ለማንሸራሸር ምቹ ካለመሆኑ የተነሳ ረጃጅም ኳሶች ከመመልከት ውጪ በቅብብሎሽ የሚገኙ እድሎችን መመልከት አልቻልም። በተለይ ተጫዋቾች ኳስን ሲይዙ ሜዳው አቅጣጫን ሲያስታቸው የነበረበት ሂደት ተመልካችን ያዝናናም ነበር። መድኖች 52ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል ሜዳ የተገኘችውን የቅጣት ምት ኪዳኔ ተስፋዬ በረጅሙ ሲያሻማ ከተከላካይነት ወደ አጥቂ ስፍራ ላይ ተስቦ ሲጫወት የነበረው ሂደር ሙስፋ በግሩም አጨራረስ አስቆጥሮ መድኖች ማንሰራት እንዲችሉ አድርጓል፡፡
መድኖች አቻ ለመሆን ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ ሲሆን አማካዩ ሚካኤል ለማ ከርቀት ሁለት ጊዜ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ በተመሳሳይ መንገድ ያወጣበት የሚጠቀሱ አስቆጪ ሙከራዎች ናቸው፡፡ 81ኛ ደቂቃ ጀሚል ያዕቆብ በአየር ላይ በግሩም ሁኔታ ያቀበለውን ኳስ አብዱለጢፍ ሙራድ በግንባር ገጭቶ ወደ ውጪ ለጥቂት የወጣችበት፣ የጨዋታው መጠናቀቂያ ጭማሪ ሰዓት ላይ ከቅጣት ምት ጀሚል አሻምቶ አጥቂው አቤል ማርቆስ በግንባር ገጭቶ የግቡን ቋሚ ታካ የወጣችበትም የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ መድኖች ምንም እንኳን የበላይነትን ቢያሳዩም በጥብቅ መከላከል ላይ ትኩረት ያደረጉት ዲላዎች ተሳክቶላቸው ጨዋታው 2-1 በባለሜዳው አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡
ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኃላ በመድን በኩል ድንቅ እንቅሴቃሴን በማድረግ ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረው ተከላካዩ ሂደር ሙስፋ በእንባ ከሜዳ ሲወጣ የተመለከትነው ሲሆን በርካቶችም ወደ ተጫዋቹ ተጠግተው ለክለቡ ያሳየውን ተግባር በማፅናናት በጭብጨባ አድናቆት ችረውታል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡