የቡና እና መቐለ ጨዋታ ለማክሰኞ ተራዝሟል

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ 04:00 በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። የቡና እና መቐለ ጨዋታም በድጋሚ ተራዝሞ ወደ ማክሰኞ ዞሯል።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ጂራ፣ በም/ፕሬዝዳንት ኮሎኔል ዐወል አብዱራሂም እና የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ፕሬዝደንት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ በተገኙበት ዛሬ በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል ድንገተኛው ጋዜጣዊ መግለጫ የተከናወነ ሲሆን ለአጭር ደቂቃ በቆየው በዚህ መግለጫ አቶ ኢሳይያስ ጅራ ጨዋታው በተመልካች ፊት ማክሰኞ እንደሚደረግ አብራርተዋል። ” ዛሬ በዝግ ይካሄዳል ተብሎ ቀጠሮ የተያዘለት የኢትዮጵያ ቡና እና የመቐለ 70 እንደርታ ጨዋታ የፀጥታ አካላት ኃላፊነት በመውሰድ ለተመልካች ክፍት ሆኖ እንዲካሄድ ነግረውናል። በዚህ መሠረት ክለቦቹ በተለይ ባለሜዳው ኢትዮጵያ ቡና ሙሉ ኃላፊነት ለመውሰድ የተስማማ መሆኑን ለመግለፅ እፈልጋለው።

“ይህን መነሻ በማድረግ ፖሊስ ሀገራዊ የማትሪክ ማጠቃለያ ፈተና በመሆኑ ይህ ፈተና ሳያልቅ ምንም ዓይነት ውድድር በኃላፊነት ወስዶ ማገዝ እንደማይችል ባስቀመጠልን አቅጣጫ መሰረት ፈተናው ማክሰኞ ጠዋት ሲጠናቀቅ እኛ ደግሞ ውድድራችንን ከዛ ቀጥለን 10:00 ለተመልካች ክፍት ሆኖ እንዲካሄድ ከሊግ ኮሚቴ ጋር ተነጋግረን ወስነናል። እንዲሁም የሁለቱ ክለብ አመራሮች በተገኙበት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲሰጥ አቅጣጫ የተቀመጠ በመሆኑ ይህ ጋዜጣዊ መግለጫ ተዘጋጅቷል። ባጋጣሚ የመቐለ ኃላፊዎች እዚህ የማይገኙ በመሆኑ እንጂ በዚህ መግለጫ ላይ ይገኙ ነበር። ፌዴሬሽኑ ከዚህ በፊት እንዳስቀመጠላቹ ምንም አይነት የጥፈተኝነት ውሳኔ አይደለም ያስተላለፈው። የዲሲፒሊን ግድፈት ተፈፅሞ የነበረ ቢሆን ኖሮ አቋማችን ያው በዝግ እንደሚሆን እንዲታወቅ እንፈልጋለን። ” ብለዋል።

መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ በበኩላቸው ይህን ብለዋል። ” እንግዲህ ሁለታችን የመጣነው ከአንድ ቦታ ነው። ስለዚህ ብዙ የምናገረው ነገር አይኖርም። በፌደራል ፖሊስ በኩል የተነሱ ጥያቄዎች ነበሩ። ይህን ጨዋታ በዝግ ስታደርጉ ሁለቱ ክለቦችን አወያይታቹ የሚል ነበር። እንደሚታወቀው ሁለታችንም ክለቦች በግንባር ተገናኝተን ያወራነው ነገር የለም። ስለዚህ ከፌደራል ፖሊስ የተነገረን ለሠላም ዋስትና የሚሰጠው ሁለቱ ክለቦች በግንባር ተገናኝተው ጨዋታው እንዴት በሰላም መጠናቀቅ እንዳለበት መነጋገር ያስፈልጋል በማለቱ እስከ ማክሰኞ ድረስ በሁለታቹ መካከል ይህ ውይይት ይካሄዳል። ከሜዳ ውጭ ያለውን የፀጥታ አካላት ኃላፊነት ይወስዳሉ፣ በሜዳ ውስጥ ያለውን እኛ ኃላፊነት በመውሰድ ጨዋታው ማክሰኞ የሚካሄድ እንደሆነ ተናግረዋል። ”

በዚህ መልኩ የተደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ በቦታው የተገኙት የሚዲያ አካላት ምንም አይነት ጥያቄ እንዲያቀርቡ እድል ሳይሠጥ ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ
በኢንተርኔት መቋረጥ ምክንያት በድረ-ገጻችን ላይ የወጡ ጽሁፎች መዘግየት ሊታይባቸው ይችላል።