ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ መደረግ ሲጀምሩ በምድብ ሀ ጊዮርጊስ እና ሀዋሳ ከተማ፤ በምድብ ለ አዳማ እና ሀላባ አሸንፈዋል።
በምድብ ለ አዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማን ከአዲስ አበባ ከተማ ያገናኘው ወሳኝ ጨዋታ በአዳማ ከተማ የ2-0 በሆነ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል። አዳማ ከተማ የነጥበረ ልዩነቱን ለማጥበብ፣ አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ የምድብ አሸናፊነቱን ለማረጋገጥ እንዲሁም ሁለቱም ቡድኖች የሚከተሉት በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ የጨዋታ አቀራረብ ጨዋታውን ተጠባቂ አድርጎታል።
እንደተጠበቀው በርካታ የግብ ዕድሎች የተፈጠሩበት መልካም የሚባል የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ተመልከትንበት የተጠናቀቀ ጨዋታ ሆኖ አልፏል። ብዙም ሳይቆይ ነው ገና በጨዋታ ጅማሬ 1ኛው ደቂቃ በአዲስ አበባ ግብ ጠባቂ ዮሴፍ ወንድማገኝ እና ተከላካይ ኢያሱ ለገሰ መካከል በተፈጠረ አለመግባት የተነሳ እያሱ ለገሰ በራሱ ላይ ባስቆጠረው ጎል አዳማዎች ቀዳሚ የሆኑት። በበፍጥነት የዚች ጎል መቆጠር የአዲስ አበባ ተጫዋቾችን እንዳይረጋጉ ሲያደርግ አዳማዎችን ጎሏ አነቃቅታቸዋለች። በመሐል ሜዳ ላይ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የወሰዱት አዳማዎች የአዲስ አበባ የተከላካዮችን መዘናጋት ተከትሎ ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር የሚችሉበትን ነፃ የጎል አጋጣሚ ዮሐንስ ፈንታ ሳይጠቀምበት የቀረው የሚያስቆጭ ነው። ኳሳቸው እየተቆራረጠ የተቸገሩት አዲስ አበባዎች ተረጋግተው ወደ ጨዋታው በመግባት አላዛር ሽመልስ ከቀኝ መስመር ተከላከይ በማለፍ ያሻገረውን ብሩክ ሰሙ አግኝቶ ወደ ጎል በቀጥታ ቢመታውም ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቶበታል።
የመሐል ሜዳ የበላይነት ለመውሰድ በሚደረግ ትንቅንቅ መልካም የጨዋታ እንቅስቃሴ እንድናይ ባስቻለን በዚህ ጨዋታ በፍጥነት ወደ ጎል የሚደርሱት አዳማዎች በታዛንያ አስተናጋጅነት አምና በተካሄደው ከ17 ዓመት የሴካፋ ዋንጫ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እስከ ፍፃሜ ድረስ አብሮ በተጓዘው ስብስብ ውስጥ ለወደፊቱ ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች መሆኑን ያሳየው ቢንያም አይተን ጥሩ የጎል ዕድል አግኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው ጎል መሆን የሚችል አጋጣሚ ነበር።
የአዳማን ተከላካዮች ሰብሮ በመግባት በቀጥተኛ ኳስ የግብ ዕድል መፍጠር የተቸገሩት አዲስ አበባዎች ከሳጥን ውጭ የጎል ዕድል ለመፍጠር ሞክረዋል። ለዚህም ማሳያ በሁለት አጋጣሚውች ሙከሪም ምዕራብ ከሳጥን ውጭ አክርሮ በመምታት የፈጠራቸው የጎል አጋጣሚዎች ተጠቃሽ ነበሩ። ጨዋታው መጀመርያው ደቂቃ ከነበረው ፍጥነት እየቀነሰ ቀጥሎ ወደ እረፍት መዳረሻ ላይ ሁለት ለጎል የቀረቡ የጎል ሙከራዎችን በሁለቱም በኩል ተመልክተናል። በአዲስ አበባ በኩል 41ኛው ደቂቃ አሸናፊ ጉታ ከግራ መስመር ተከላካዮችን በመቀነስ ወደ ጎል ያሻገረውን ብሩክ ሰሙ በግንባሩ ገጭቶ በረኛውን ቢያልፈውም የአዳማ ተከላካይ ጎል እንዳይሆን እንደምንም ተንሸራቶ ያዳነው። በአዳማ በኩል 43ኛው ደቂቃ ዮሐንስ ጥሩ የጎል አጋጣሚ አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ከዕረፍት መልስ በ49ኛ በዕለቱ ድንቅ እንቅስቃሴ በአዳማ በኩል ካሳዮን ተጫዋቾች መካከል አንዱ የነበረው ወንድማገኝ እንግዳ በጥሩ መንገድ አመቻችቶ ያቀበለውን ዮሐንስ ፈንታ ከበረኛ ጋር ተገናኝቶ ጎል አስቆጠረ ሲባል የአዲስ አበባ ግብጠባቂ ዮሴፍ የያዘበት ተጨማሪ ጎል መሆን የሚችል ነው። ጎል ለማስቆጠር ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት አዳማዎች በተመሳሳይ መንገድ ወንድማገኝ እንግዳ ያቀበለውን ኳስ በ54ኛው ደቂቃ ዮሐንስ ፈንታ ወደ ጎልነት በመቀየር 2-0 መምራት ችለዋል።
አዲስ አበባዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ በማሰብ አሰልጣኝ ደምሰው ፍቅሩ በአንዴ የሦስት ተጫዋቾች ቅያሪ ያደረጉ ቢሆንም እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ ኳሱን ተቆጣጥሮ ከመጫወት ባለፈ የጎል እድል ለመፍጠር ሲቸገሩ ተመልክተናል። ይልቁንም የጎል ዕድል ለመፍጠር ከተከላካዮቹ ጭምር የግብ ክልላቸውን ነቅለው ለማጥቃት ሲሳቡ ለአዳማ አጥቂዎች ክፍተት በመፍጠር በራሳቸው ላይ አደጋ ይፈጥሩ ነበር። ለአዳማዎች ሦስተኛ ጎል መሆን የሚችል ዕድል ዮናስ አብነት ከበረኛው ዮሴፍ ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው ሌላው በአዳማ በኩል የሚጠቀስ የጎል ሙከራ ነበር። የአዲስ አበባ በኩል አላዛር ሽመልስ በግሉ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ በቀር በጨዋታው የተሳካ የጎል እድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ጨዋታው በአዳማ 2 – 0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ የአንድ ጨዋታ ዕድሜ የቀረው የምድብ ሀ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ውድድር አዲስ አበባ የዛሬውን ጨዋታ አሸንፎ አልያም ነጥብ ተጋርቶ የሚወጣ ቢሆን ኖሮ የምድቡ አሸናፊ ሆኖ ማጠናቀቅ የሚችል የነበረ ቢሆንም መሸነፉን ተከትሎ በሚቀጥለው ሳምንት ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ገብቷል።
በመጨረሻም የአዳማዎቹ የመሐል ሜዳ ተጫዋቾች ወንድማገኝ እንግዳ እና አላሚን ከድር ያደረጉት እንቅስቃሴ ለወደፊት ተስፋ የሚጣልበት ነው።
በምድብ ሀ መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ድሬዳዋ አምርቶ 1-0 አሸንፏል። የጊዮርጊስን ብቸኛ የድል ጎል ያስቆጠረው በተከታታይ ለቡድኑ ውጤታማነት ጉልህ ሚና እየተጫወተ የሚገኘው ታዲዮስ አዱኛ በ34ኛው ደቂቃ ነው። ተከታዩ ሀዋሳ ከተማም በሜዳው ጥሩነሽ አካዳሚን 3-2 በማሸነፍ በአንድ ነጥብ ልዩነት ቅዱስ ጊዮርጊስን መከተሉን ቀጥሏል።
የ17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች
ምድብ ሀ
ቅዳሜ ሰኔ 8 ቀን 2011
ሀዋሳ ከተማ 3-2 ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ
ድሬዳዋ ከተማ 0-1 ቅዱስ ጊዮርጊስ
ወላይታ ድቻ 3-0 ኢ/ወ/ስ አካዳሚ (ፎርፌ)
እሁድ ሰኔ 9 ቀን 2011
አምቦ ጎል ከ ኢትዮጵያ ቡና (አምቦ)
ሲዳማ ቡና ከ መከላከያ (ይርጋለም)
ምድብ ለ
ቅዳሜ ሰኔ 8 ቀን 2011
አዳማ ከተማ 2-0 አአ ከተማ
ሀላባ ከተማ 2-0 ወልቂጤ ከተማ
እሁድ ሰኔ 9 ቀን 2011
ፋሲል ከነማ ከ አሠላ ኅብረት (ጎንደር)
አፍሮ ፅዮን ከ ኢትዮ መድን (24 ሜዳ)
አራፊ ቡድን – ኢትዮ ኤሌክትሪክ
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡