ከፍተኛ ሊግ ሀ| ሰበታ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደጉን ሲያረጋግጥ አውስኮድ ወደ አንደኛ ሊግ ወርዷል

በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሀ 21ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሙሉ እሁድ ተከናውነው ሰበታ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊግ ያደገበትን፣ አውስኮድ ወደ አንደኛ ሊግ የወረደበትን ውጤት አስመዝግበዋል።

ለገጣፎ ላይ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ በለገጣፎ ለገዳዲ እና ሰበታ ከተማ መካከል ተከናውኖ 1-1 ተጠናቋል። ሰበታ ከተማም አንድ ጨዋታ እየቀረው ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉን አረጋግጧል። የሁለቱም ከተማ ከንቲባዎች እንዲሁም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ እና በርከት ያሉ የለገጣፎ እና የሰበታ ደጋፊዎች በታደመበት በዚህ ጨዋታ በፈጣን እንቅስቃሴ ተጭነው የተጫወቱት ለገጣፎዎች በ2ኛው ደቂቃ ሐብታሙ ፍቃደ ከርቀት አክርሮ በመምታት ባደረገው የመጀመርያ የጎል ሙከራ ነበር የሰበታን የግብ ክልል መፈተሽ የጀመሩት። ብዙም ሳይቆይ ሐብታሙ ከመስመር ያሻገረውን የሰበታ ተከላካዮች በግንባር ገጭተው ኳሱን ለማራቅ ቢያስቡም ተቆርጦ እዛው የቀረውን ኳስ አጥቂው ሳዲቅ ተማም በአግባቡ በመጠቀም ለገጣፎን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደጋቸውን ለማረጋገጥ ጎል ወደ ማስቆጠር ግዴታ ውስጥ የገቡት ሰበታዎች ጫላ ድሪባ ከርቀት የሞከረውና በዕለቱ ለሰበታ መልካም እንቅስቃሴ ሲያደርግ የዋለው ኢብራሂም ከድር ከማዕዘን ምት ተደርቦ ሲመለስ ያገኘውን ኳስ ወደ ጎል ሲመታው የለገጣፎው ግብጠባቂ አንተነህ ሀብቴ ያዳነበት ጎል መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎች ፈጥረዋል።

ከጨዋታው እንቅስቃሴ ይልቅ በኳስ አቀባዮቹ በሚፈጥሩት የኳስ መዘገይት የተነሳ የጨዋታውን መንፈስ ሲቆራረጥ ለማስተዋል የቻልን ሲሆን ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት ብልጫ የነበራቸው ሰበታዎች ወደ ፊት ሄደው በጎል ሙከራ ያልታጀበ እንቅስቃሴ በመሆኑ ሲቸገሩ ይልቁንም በሚነጠቁት ኳሶች ለገጣፎዎች በመልሶ ማጥቃት አደጋ ለመፍጠር ተንቀሳቅሰዋል። በጥሩ ቅብብሎች ወደፊት በመግባት የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ተጫዋች ፍርድአወቅ ሲሳይ 30ኛው ደቂቃ ሳጥን ውስጥ ኳሱን ይዞ በመግባት በግራ እግሩ ወደ ጎል ቢመታውም በድጋሚ የለገጣፎ ግብ ጠባቂ አንተነህ በጥሩ ብቃት ወደ ውጭ ያወጣበትም ሌላው የሰበታ ተጠቃሸ ሙከራ ነበር።

ከዕረፍት መልስ የአቻነት ጎል ፍለጋ ጥረታቸውን የቀጠሉት ሰበታዎች የፕሪምየር ሊጉን ትኬት የቆረጡበትን ጎል በ53ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። ኢብራሂም ከድር ከግራ ወደ ቀኝ ሰብሮ በመግባት ከርቀት ግሩም የሆነ ጎል አስቆጥሮ የሰበታ ደጋፊዎችን በደስታ አስጨፍሯል።

በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ግርግር ያላጣው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከጎሉ መቆጠር በኃላ መጠነኛ ግርግር ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም እንቅስቃሴው ቀጥሎ ለገጣፎዎች በተደጋጋሚ የሰበታን የግብ ክልል ሲፈትሹ ውለዋል። 65ኛ ደቂቃ የሰበታ ግብ ጠባቂ ሰለሞን ደምሴ ከለገጣፎ አጥቂዎች ከርቀት ቅጣት የተመታውን እና ከማዕዘን ምት የተሻገረውን በግንባር የተገጩ ሙከራዎች አድኗል። የጨዋታው ደቂቃ ወደ መጠናቀቂያው ሲቃረብ ሙሉ ለሙሉ ወደ መከላከል ያመዘኑት ሰበታዎች በለገጣፎዎች በኩል የሚደረገውን ጎል ፍለጋን በመከላከል ቆይተዋል። በተለይ ለገጣፎዎችን አሸናፊ የምታደርግ የግብ ዕድል 86ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ዳዊት ቀለመወርቅ በግንባሩ በመግጨት ወደ ጎል የመታውን ኳስ የሰበታው ግብጠባቂ ሰለሞን ያዳናት ለለገጣፎዎች የሚያስቆጭ ነበር። በመጨረሻም የዕለቱ ዳኛ የጨዋታው ጭማሪ ሦስት ደቂቃ መስጠታቸውን ተከትሎ ተገቢ አይደልም በማለት ለገጣፎዎች ቅሬታ ያሰሙ ሲሆን ጨዋታውም አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል። በ2003 ከፕሪምየር ሊጉ የወረደው ሰበታ ከተማም ከ8 የውድድር ዘመናት በኋላ በምድብ ሀ አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ ወደ ሊጉ ተመልሷል።

ወደ አክሱም ያመራው አውስኮድ 1-0 ተሸንፎ ከምድቡ የመጀመርያው ወራጅ ቡድን መሆኑን አረጋግጧል። የአክሱምን ብቸኛ የድል ጎል ያስቆጠረው ሙሉጌታ ረጋሳ ነው።

ቡራዩ ከተማ በሜዳው ገላን ከተማን ገጥሞ በክንዳለም ፍቃዱ ብቸኛ ጎል 1-0 አሸንፏል። ከመውረድ ለመትረፍ ያለውን ጭላንጭል ተስፋም ወደ ቀጣዩ ሳምንት አስቀጥሏል።

አቃቂ ቃሊቲ ከሜዳው ውጪ ወሳኝ ነጥብ ይዞ ተመልሷል። ደሴ ከተማን በዮናስ ባቢና ጎል 1-0 ያሸነፈው አቃቂ ቃሊቲ በድሉ በመታገዝ ከመውረድ ለመትረፍ ከቀጣይ ጨዋታ አንድ ነጥብ ማግኘት በቂው ሆኖለታል።

ወልዲያ ላይ ወልዲያ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 1-0 ያሸነፈበት እና ወሎ ኮምቦልቻ ከፌዴራል ፖሊስ 0-0 የተለያዩበት ጨዋታዎች ሌሎች የዚህ ሳምንት መርሐ ግብር አካል ናቸው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡