የአሰልጣኞች አሰተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 0-0 መቐለ 70 እንደርታ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ቀሪ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ከ መቐለ 70 እንደርታ ያለ ጎል ከተለያዩ በኋላ አሰልጣኞቹ አስተያየት ሰጥተዋል።
“የአየር ሁኔታው እንደምንፈልገው እንድንቀሳቀስ አላስቻለንም”- ገዛኸኝ ከተማ (ኢትዮጵያ ቡና)

“ለዚህ ጨዋታ ያደረግነው ዝግጅት ለማሸነፍ ነበር፤ ነገርግን የአየር ሁኔታው እንደምንፈልገው እንድንቀሳቀስ አላስቻለንም። ሆኖም ከሞላ ጎደል ጥሩ ተንቀሳቅሰናል፡፡ በዚህ የሜዳ ሁኔታ ተጫዋቾቼ በዚህ መልኩ መንቀሳቀሳቸው በራሱ ጥሩ የሚባል ነው፡፡ ቡድናችን በዛሬው ጨዋታ ሽግግሮች ላይ ጥሩ አልነበርንም፤ መሀል ሜዳ ላይ የነበረን እንቅስቃሴ ግን በአንጻራዊነት ጥሩ የሚባል ነው፡፡”

“ከነበረብን ጫና ከደረሰብን እንግልት አንጻር ባለማሸነፋችን አልተከፋሁም”- ገብረመድህን ኃይሌ (መቐለ70 እንደርታ)

ስለጨዋታው

“ውጤቱ እንደጠበቅነው አልነበረም፤ እንደፈጠርናቸው እድሎች ውጤቱ ለኛ የሚገባን አልነበረም፡፡ ከነበረብን ጫና ከደረሰብን እንግልት አንጻር ባለማሸነፋችን አልተከፋሁም፡፡ ምንም እንኳን የተወሰኑ ክፍተቶች ቢኖሩብንም በዚህ ባልተመቸ ሜዳ ላይ ተጫዋቾቼ በግልም ሆነ እንደቡድን ያደረጉት ጥረትና ተጋድሎ የሚያስከፋ አይደለም፡፡”

ስለዋንጫ ተስፋቸው

“ሦስት ጨዋታዎች ነው የሚቀሩን። ከእነዚህም ሁለቱ በሜዳችን የምናደርጋቸው ናቸው። ሌላ ነገር ካልተፈጠረ አሁንም ለዋንጫው ሰፊ እድል አለን፡፡ ከመጣንበት አካሄድና ካለው ጫና አንጻር ሊያጠራጥር ይችላል፤ ካለን ነገር ተነስቼ ግን አሁንም ለዋንጫ የተሻለ ሰፊ እድል አለን፡፡”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡