የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ቀሪ የ20ኛ ሳምንት እና መበደኛ የ21ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ተከናውነው ሀዲያ ሆሳዕና ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደጉን ሲያረጋግጥ አርባምኝጭ ከተማ ደ ነቀምት ሳይጓዝ ቀርቷል።
ሆሳዕና ላይ ሀዲያ ሆሳዕና ሺንሺቾን አስተናግዶ 3-0 አሸንፏል። ፎቶ እና ባህላዊ የአንገት ልብስ ለሺንሺቾ ተጫዎቾች በማበርከት በጀመረው ጨዋታ በቅርቡ ህይወቱን ላጣው ወንድወሰን ዮሐንስ የህሊና ፀሎት የተደረገ ሲሆን ለተጫዋቹ ቤተሰብ የገንዘብ ማሰባሰብ ተግባር ሲከናወን ተመልክተናል። በአጠቃላይ 16,748 ብር መሰብሰቡም ታውቋል።
የመጀመርያው አጋማሽ በብዙ መለኪያዎች ባለሜዳው ሆሳዕናዎች ብልጫ የታየበት ነበር። እንግዶቹ ሺንሺቾዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ፈጣን እንቅስቅሴ በማድረግ ንፁህ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት ባይሳካም በ4 ኛው ደቂቃ ከርቀት ብርሃኑ ኦርዴሎ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ያዳነበት ጨዋታው የመጀመሪያው ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ነበር ። የተወሰደባቸውን የኳስ እንቅስቃሴ ብልጫ ማስመለስ የቻሉት ነብሮቹ በ10ኛው ደቂቃ ሱራፌል ጌታቸው ያሻማውን ኳስ እዩኤል ሳሙኤል ያደረገው ጥረት ሳይሳካ በቀረው ሙከራ ወደ ጎል ደርሰዋል። በ21ኛው ደቂቃ ፍራኦል መንግስቱ ላይ በተስራ ጥፋት የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት አዩብ በቀታ ወደ ግብነት በመለወጥ ሆሳዕናዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል።
በመስመር በኩል ማጥቃታቸውን የቀጠሉት ሆሳዕናዎች የግብ ልዩነታቸውን የሚያሰፉባቸው አጋጣሚዎችን መፍጠር የቻሉ ሲሆን በ34ኛው ደቂቃ ላይ ስንታየሁ አሸብር ያሻማውን ኳስ የሺንሺቾ ግብ ጠባቂ ቀድሞ በመውጣት ቢመልሰውም ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ሱራፌል ጌታቸው በድጋሚ መትቶ በግቡ አግዳሚ በኩል የወጣችበት እድል አስቆጭ ነበረች።
በርካታ የሜዳ ላይ ጥፋቶች እንዲሁም ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ እና የጠራ የግብ እድል በሁለቱም ቡድን በታየበት ሁለተኛው ምዕራፍ ሺንሺቾ ጫና ፈጥረው ሆሳዕናዎች ደግሞ ጥንቃቄ በመምረጥ የተንቀሳቀሱበት ነበር። ብርሃኑ ኦርዲላ በ47ኛው ደቂቃ በግንባሩ የገጨውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሲያድንበት በ59ኛው ደቂቃ ከርቀት የመታው ኳስ በግቡ አናት ላይ ወጥታበታለች። በ60ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘውን የቅጣት ምት እድል ኤፍሬም ታምራት መትቶ የግቡን አግዳሚ ታኮ የወጣበትም ሌላው የሺንሺቾ ጠንካራ ሙከራ ነበር።
ባለሜዳዎቹ በሒደት በደጋፊዎቻቸው ታጅበው እንቅስቃሴያቸው እጅጉን በማፍጠን በረጃጅም ኳሶች ጫና ፈጥረዋል። በ65ኛው ደቂቃ ስንታየው አሽብር ያሻገረውን ኳስ እዩኤል ሳሙኤል በግሩም ሁኔታ አክርሮ በመምታት ድንቅ ጎል አስቆጥሮ የሆሳዕናን የግብ ልዩነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል። በ72ኛው ደቂቃ ደግሞ የሺንሺቾ አማካይ ተከላካይ ስህተት ታክሎበት ዳግም በቀለ ለእዩኤል የሰነጠቀለትን ኳስ እዩኤል የግል ጥረቱ ታክሎበት ወደ ግብነት በመለወጥ ለቡድኑን ሶስተኛ ለራሱ ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይታይበት በሆሳዕና አሸናፊነት 3-0 ውጤት ተጠናቆ ሀዲያ ሆሳዕናም ከ2008 በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊግ መመለስ ችሏል።
ቡታጅራ ላይ ካፋ ቡናን ያስተናገደው ቡታጅራ ከተማ 2-1 በማሸነፍ ወሳኝ ነጥብ አስመዝግቧል። አፈወርቅ ዮሐንስ እና ክንዴ አቡቹ የድል ጎሎችን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ሲሆኑ ኦኒ ኡጅሉ የካፋን ብቸኛ ጎል አስቆጥሯል።
ስልጤ ወራቤ በሜዳው ነገሌ ቦረናን አስተናግዶ በተመስገን ዱባ ጎሎች 2-0 ማሸነፍ ችሏል። ነጌሌ ቦረና በሊጉ ተመሰንበት በመጨረሻው ሳምንት ድል አስመዝግቦ የካፋ ቡና እና ቡታጅራ ውጤትን ይጠብቃል።
ቤንች ማጂ ቡና በሜዳው ሻሸመኔ ከተማን 3-2 ሲያሸንፍ ነቀምት ላይ ነቀምት ከአርባምንጭ ከተማ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በአርባምንጭ ከተማ አለመገኘት ምክንያት ሳይከናወን ቀርቷል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡