ትልቋ ናይጀርያ፣ ጠንካራዋ ጊኒ እና ለውድድሩ እንግዳ የሆኑ ሁለት ሀገራትን የሚያገናኘው ይህ ምድብ ምንም እንኳ ከወዲሁ የብዙዎች ትኩረት የሳበ ምድብ ባይሆንም ለትልቁ ውድድር አዳዲስ የሆኑ በርካታ ተጫዋቾች ያካተተ ምድብ እንደመሆኑ ከብዙዎች ግምት ውጭ ጥሩ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ተጠብቋል።
🇳🇬 ናይጀርያ
የተሳትፎ ብዛት – 16
ምርጥ ውጤት: 3 ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ (1980፣ 1994፣ 2013)
በውድድሩ ላይ ጥሩ ክብረወሰን ካላቸው ሃገራት ረድፍ የምትገኘው ናይጀርያ ዘንድሮም ለዋንጫ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ቡድኖች ትጠቀሳለች።
ደቡብ አፍሪካ፣ ሲሸልስ እና ሊቢያ የነበሩበት ምድብ ‘ E ‘ በበላይነት ያጠናቀቁትና እንደባለፉት ውድድሮች በትልቅ ደረጃ የሚጫወቱ በርካታ ኮከቦች ያልያዙት ‘ሱፐር ኤግልስ’ ምንም እንኳ የበቁ ኮከቦች ባይዙም ልምድ ያለውና የማጣርያው ኮከብ ጎል አግቢ ሆኖ የጨረሰው ኦድዮን ኤግሃሎን ጨምሮ ኦቢ ሚካኤል እና በአርሰናል የኡናይ ኤምሪ ተቀዳሚ ምርጫ የነበረው ኢዎቢን እንደመያዛቸው ቀላሉን ምድብ በበላይነት ይጨርሳሉ ተብሎ ይገመታል።
በጀርመናዊው ጌርሞት ሮኸር የሚመሩት ንስሮቹ በ2013 በስቴፈን ኬሺ መሪነት ያሳኩትን የአፍሪካ ዋንጫ ድል በዚህ ውድድርም ለማሳካት ወደ ግብፅ እንደሚያመሩ ከወዲሁ እየገለፁ ይገኛሉ። ከሌሎች አፍሪካ ሃገራት በተሻለ በዓለም ዋንጫው የምድብ ጨዋታዎች ጥሩ ተፎካካሪ የነበሩት እና በውድድሩ አይስላንድን አሸንፈው በአርጀንቲና በጠባብ ውጤት የተሸነፉት ናይጀርያዎች በታላቁ ውድድር ላይ ባሳዩት ጥሩ ተፎካካሪነት በአፍሪካ ዋንጫው ላይ ለዋንጫ ተገማች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።
ከዚ በተጨማሪ ናይጀርያዎች ግብፅን አሳባ ላይ ካሸነፉበት የአቋም መለክያ ጨዋታ ጨምሮ በቅርብ ግዜያት ባደረጓቸው አቋም መለኪያ ጨዋታዎች ላይ ያስመዘገቡት ጥሩ ውጤት ሌላው ከቡድኑ የሚነሳ ጥሩ ጎን ነው።
🇬🇳 ጊኒ
የተሳትፎ ብዛት፡ 12
ምርጥ ውጤት፡ የፍፃሜ ተፋላሚ (1976)
ሳይጠበቁ ትላልቆቹ አይቮሪኮስት እና ኮንጎ የሚገኙበትን ምድብ ‘ H ‘ በበላይነት ያጠናቀቁት ብሄራዊ ዝሆኖቹ በማጣርያው ላይ ያሳዩት ጥሩ ብቃት ሲታይ ቀላል ተጋጣሚ እንደማይሆኑ የታወቀ ነው።
የሚጠበቀው ኮከባቸው የሊቨርፑሉ ናቢይ ኬታ በጉዳት በመጀመርያዎቹ ጨዋታዎች በጉዳት የማያገኙት በፖል ፑት የሚመሩት ጊኒዎች ምንም እንኳ በማጣርያው መጀመርያዎቹ ጨዋታዎች በተከታታይ ጥሩ ውጤት አምጥተው ምድቡን በመሪነት ቢያጠናቅቁም በመጨረሻዎቹ ሶስት ጨዋታዎች ያመጡት ተከታታይ የአቻ ውጤት ግን በመጥፎ ጎኑ የሚነሳ ነው።
በ2017 ጋቦን ባዘጋጀችው አፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ ያልቻሉት ጊኒዎች በቅርብ ዓመታት በተሳተፉባቸው ውድድሮች በምድብ ጨዋታዎች ጥሩ ውጤት ነው ያላቸው። ቡድኑ ጋቦን እና ኢኳቶርያል ጊኒ በጣምራ አዘጋጅተውት በምድብ ላይ ከተሰናበተበት ዓመት ውጭ በተቀሩት አራት ውድድሮች ስምንት ውስጥ መግባት የቻለ ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን ነው።
አብዛኞቹ ተጫዋቾቻቸው ከመከላለኛ ደረጃ ካላቸው ሊጎች የመረጡት ጊኒዎች ከቡድናቸው የሊቨርፑሉ ናቢይ ኬታ፣ የቱሉዙ ኢስያጋ ሲላ እና የቦርዶው ፍራንሲስ ካማኖ የሚጠበቁ ተጫዋቾች ናቸው።
🇲🇬 ማዳጋስካር
የተሳትፎ ብዛት፡ ለመጀመርያ ጊዜ (2019)
በውድድሩ ምርጥ ውጤት፡ የመጀመርያ ተሳትፎ
በታሪካቸው ለመጀመርያ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫው የሚሳተፉት ማዳጋስካሮች ሳይጠበቁ ነበር ኢኳቶሪያል ጊኒን አሸንፈው ወደ ውድድሩ ማለፋቸው ያረጋገጡት። ዝቅተኛ ግምት ተሰጥቷቸው በቅድመ ማጣርያ ወደ ምድብ ጨዋታዎች የገቡት ማዳጋስካሮች ሳኦቶሜ እና ፕሪንስፔን አሸንፈው ምድብ አንድ ላይ ሲደለደሉ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ያልፋሉ ብሎ የገመተ አልነበረም።
የአፍሪካ ግዙፏ ደሴት በኮሳፋ ዋንጫ እና በሌሎች ትናንሽ ውድድሮች ከመሳተፍ ውጭ በትልቅ ውድድር የመሳተፍ ታሪክ የሌላት ሲሆን በምድብ ‘ A ‘ ሴኔጋል ፣ ኢኳተርያል ጊኒ እና ሱዳን በተደለደሉበት ምድብ ሴኔጋልን ተከትላ ነበር ወደ ውድድሩ ያለፈችው። በማጣርያው መክፈቻ ጨዋታ ላይ በሜዳቸው አንታናሪቮ ላይ በሴኔጋል ሁለት ለባዶ ከመመራት ተነስተው አቻ ከተያዩ በኃላ የብዙዎች ትኩረት ስበው የነበረ ሲሆን በውድድሩ ላይ ይህ ነው የሚባል ታሪክ ባይኖራቸውም በአንፃራዊነት ከሌሎች ምድቦች ቀላል በሆነው ምድብ ጥሩ ተፎካካሪ የመሆን ዕድላቸው የሰፋ ነው።
በኒኮላስ ዲፕዩስ የሚመሩት ማዳጋስካሮች በሊዮን የሚጫወተው ጄረምይ ሞራል ጨምሮ በአልጀርያ ኤምሲ አልጀርስ የሚጫወተው ኢብራሂም አማንዳ እና ሚኒሶታ ዩናይትድ የሚጫወተው ሮሜይን ሞታኔሬ በቡድናቸው የሚጠበቁት ተጫዋቾች ናቸው። የቡድኑ ስብስብ ለመጥራት እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ ረጃጅም ስሞች የተሞላ መሆኑ ለመጀመርያ ጊዜ ከማለፏ ጋር ተደማምሮ ትኩረት የሳበች ሀገር ሆናለች።
🇧🇮 ብሩንዲ
የተሳትፎ ብዛት፡ ለመጀመርያ ጊዜ (2019)
ምርጥ ውጤት፡ የመጀመርያ ተሳትፎ
በምድብ ‘ C ‘ ከማሊ፣ ደቡብ ሱዳን እና ጋቦን ጋር ተደልድለው ማሊን ተከትለው በአስር ነጥብ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ያለፉት ብሩንዲዎች ከኬንያ ፣ ዩጋንዳ እና ታንዛንያ ቀጥለው ምስራቅ አፍሪካን የወከሉ አራተኛ ሃገር ናቸው። የውድድሩ ተሳታፊ ሃገራት ወደ 24 ማደጉን ተጠቅመው ለመጀመርያ ጊዜ ከተሳተፉት ሃገራት አንዷ የሆነችው ሩዋንዳ በማጣርያው ጨዋታዎች ምንም ሽንፈት ሳታስተናግድ ወደ ውድድሩ በማለፍዋ በመጀመርያው ተሳትፎዋ ጥሩ ውጤት ታመጣለች ተብላ እንድትጠበቀ አድርጓታል።
በኦሊቨር ንያንጌኮ የሚመሩት ብሩንዲዎች ከጥቂት ተጫዋቾቻቸው በስተቀር የኢትዮጵያ ቡናው ሁሴን ሻባኒን ጨምሮ አብዛኞቹ ተጫዋቾቻቸው ከአፍሪካ ሃገራት ከሚገኙ ሊጎች የመረጡ ሲሆን የቡድኑን ውጤት ያሳምራሉ ተብለው የሚጠበቁ ጥቂት የማይባሉ ተጫዋቾች ይዘዋል። በተለይም በማጣርያው ላይ ደቡብ ሱዳን ላይ አራት ግቦች ያዘነበው እና የማጣርያው ስድስት ግቦች በማስቆጠር ሁለተኛ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ የጨረሰው ፊስቶን ዓብዱልረዛቅ እና የስቶክ ሲቲው አመፀኛ አጥቂ ሳይዶ በራሂኖ በቡድኑ የሚጠበቁ ኮከቦች ናቸው።
በምድቡ የሚጠበቅ ጨዋታ፡ ናይጄርያ ከ ጊኒ
ይሄ ምድብ ናይጀርያ እና ጊኒ የሚያገናኘው ጨዋታ የሚጠበቅ ጨዋታ ነው። ተስፋ የተጣለባቸው የቀጣይ ኮከቦች የያዙት እና ከወዲሁ ለዋንጫ የታጩት ናይጀርያዎች እና በማጣርያው ከነበሩት ምድቦች ጠንካራው የነበረው ምድብ ‘ H’ ሳይጠበቁ በበላይነት ያጠናቀቁት ጊኒዎች የሚያደርጉት ይህ ጨዋታ በቡድኖቹ ወቅታዊ ብቃት ምክንያት የምድቡ ትልቅ ጨዋታ ነው።
የምድቡ የሚጠበቅ ተጫዋች፡ ኦድዮን ኤግሃሎ
በርካታ አዳዲስ ፊቶች ያሳየናል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ምድብ ናቢ ኬይታን የመሰለ ትልቅ ተጫዋች ቢይዝም የሊቨርፑሉ ኮከብ የመጀመርያዎቹን ጨዋታዎች የማድረጉ ነገር አጠራጣሪ በመሆኑ የማጣርያው ኮከብ ግብ አግቢ ኦድዮን ኤግሃሎ የምድቡ አብሪ ኮከብ እንደሚሆን ይጠበቃል። ከኤግሃሎ በተጨማሪም የማጣርያው ሁለተኛ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የብሩንዲው ፊስቶን ዓብዱልረዛቅ ሌላ የሚጠበቅ ተጫዋች ነው።
ቅዳሜ ሰኔ 15 ቀን 2011
ናይጄርያ 2:00 ብሩንዲ (አሌክሳንድሪያ)
ጊኒ 5:00 ማዳጋስካር (አሌክሳንድሪያ)
ረቡዕ ሰኔ 19 ቀን 2011
ናይጄርያ 11:30 ጊኒ (አሌክሳንድሪያ)
ሀሙስ ሰኔ 20 ቀን 2011
ማዳጋስካር 11:30 ብሩንዲ (አሌክሳንድሪያ)
እሁድ ሰኔ 23 ቀን 2011
ብሩንዲ 1:00 ጊኒ (አል ሠላም፤ ካይሮ)
ማዳጋስካር 1:00 ናይጄርያ (አሌክሳንደርያ)
© የስኳድ ፎቶዎች ከካፍ የተወሰዱ ናቸው