“ኅብረታችን በጣም የተለየ ነው “ብስራት ገበየሁ

ለመጀመርያ ጊዜ ከተመሰረተበት 1982 በኋላ በተለያዩ ጊዜያት ሲፈርስ እና በድጋሚ ሲቋቋም ቆይቶ በ2002 በአዲስ መልክ በድጋሚ የተመሰረተው ወልቂጤ ከተማ ባሳለፍነው ዕሁድ ነገሌ ላይ ከአርሲ ነገሌ ጋር 1-1 ከተለያየ በኃላ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊጉ አድጓል። ከጨዋታው በኋላ በቡድኑ ረዘም ያለ ጊዜ ያሳለፈው እና ዘንድሮ በአምበልነት በመምራት ድንቅ ዓመት ያሳለፈው ብስራት ገበየሁ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።


መዝገቡ ወልዴ

ደስ የሚል ጊዜ ነበር ያሳለፍነው። ከቡድን ጓደኞቼ ጋር ሆኜ ይህን ስኬት በማየቴም እጅጉን ደስተኛ ነኝ። የዛሬው ድል በውስጤ ሁለት አይነት ስሜት እንዲኖረኝ አድርጎኛል። ለረጅም ዓመታት የዚህ ቡድን አምበል የነበረው መዝገቡ ወልዴ በህይወት አለመኖር ሀዘን ቢሰማኝም የሱን ቃል በማክበራችን ደግሞ ከምልህ በላይ ደስተኛ እንድሆን አስችሎኛል።

ፈተናን ማለፍ

ከዚህ ቀደም መከራ እና ውጣ ውረዶች የበዙበት ጊዜ ነበር። በየስታዲሞቹ የተለያዩ ጫናዎችን ያሳለፍንበት፤ ያንን ሁሉ አልፈን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመቀላቀል ግን አልቻልንም። ዛሬ ላይ ግን ሁሉም በመልካም አልፎ ያውም ከሜዳ ውጪ ተጫውተህ ነጥብን ስትይዝ እና ፕሪምየር ሊግ ስትገባ ስታይ ደስታህ ወደር አይኖረውም።

ኅብረት

ኅብረታችን በጣም የተለየ ነው። ደጋፊው፣ ተጫዋቹ፣ አሰልጣኙ እና የቡድኑ አባላት በሙሉ ደስ የሚል የመረዳዳት አመለካከት ነበረው። መተባበራችን ነው ለዚህ ያበቃን።

ፕሪምየር ሊግ

ክለባችን ለፕሪምየር ሊጉ ከአሁኑ አንዳንድ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። ደግሞም የተሻለ ሆኖ እንደሚቀርብ ዕርግጠኛ ነኝ። በዚሁ ጥንካሬ ከቀጠልን ፕሪምየር ሊጉም ላይ የዋንጫ ተፎካካሪ እንሆናለን የሚል እምነት አለኝ”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡