የአፍሪካ ዋንጫ ዳሰሳ| ምድብ ሦስት

ምድቡ ላይ ባለ ከፍተኛ የጥራት ልዩነት ምክንያት በብዙዎች ትኩራት ያልተሰጠው እና ሁለት ትላልቅ ሀገራትን የያዘው ምድብ ሦስት ሁለቱ ትላልቅ ሀገራት ሴኔጋል እና አልጀርያ በተመሳሳይ በሚከተሉት ጥሩ የማጥቃት አጨዋወት እና የያዟቸው ከዋክብት ምክንያት በርካታ ጎሎች ይመዘገቡበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በርካታ ከዋክብት የያዙት ሴኔጋል እና አልጀርያ ጨምሮ ሁለቱም የሴካፋ ተወካዮች ኬንያ እና ታንዛንያ የያዘው ይሄ ምድብ ለሁለቱም ትላልቅ ቡድኖች ከባድ ይሆናል ተብሎ ባይጠበቅም ግቦች የበዙበት እና ጥሩ የማጥቃት አጨዋወቶች ይታይበታል ተብሎ ይገመታል።

🇸🇳 ሴኔጋል 

የተሳትፎ ብዛት – 15

ጥሩ ውጤት – የፍፃሜ ተፋላሚ (2002)

በማጣርያው ቀላል በነበረው ምድብ አንድ ተደልድለው ምድቡን በበላይነት ያጠናቀቁት የቴራንጋ አናብስት በምድቡ ወደ አንታናናሪቮ አምርተው በመጨረሻ ደቂቃዎች በተቆጠሩባቸው ሁለት ጎሎች ከማዳጋስካር አቻ ከተለያዩት ጨዋታ ውጭ የተቀሩት ጨዋታዎችን አሸንፈው ነበር በቀላሉ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ያለፉት።

በወጣቱ አሰልጣኝ አሊዮ ሲሴ እየተመሩ በማጣርያውና በዓለም ዋንጫው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያሳዩት የቴራንጋ አናብስት ለዋንጫው ቅድምያ ከሚሰጣቸው አገራት በቅድምያ ይቀመጣሉ። በውድድሩ በጥራትም በቁጥርም ውጤታማ አጥቂዎች የያዙት ሴኔጋሎች በሳዲዮ ማኔ የሚመራው የአጥቂ ክፍላቸው እና በካሊዱ ኩሉባሊ የሚመራው የተከላካይ ክፍላቸው የቡድኑ ጠንካራ ጎኖች ናቸው።

በስብስቡ ውስጥ የተካተቱ ሰባት አጥቂዎች ኢስማዒላ ሳር ፣ ኬይታ ባልዴ ፣ ምባየ ንያንግ ፣ ሙሳ ኮናቴ ፣ ምባየ ድያኜ ፣ ሳዳ ጦይብ እና ሰይዶ ማኔ በዚህ ውድድር ዓመት ለክለቦቻቸው በአጠቃላይ 112 ግቦች በማስቆጠር የጥራት ደረጃቸውን በሚገባ ያሳዩ ናቸው።

በአዲሱ ሚሌኒየም ወርቃማ ትውልዷን በመጠቀም ዓለምን ያስደነቀ ቡድን ባለቤት የነበረችው ሴኔጋልን በአምልነት የመራው አሊዩ ሲሴ አሁን ደግሞ በንፅፅር አስፈሪውን ስብስብ የያዘችውን ሀገር በአሰልጣኝነት በታሪኳ የመጀመርያ ለሆነው ድል ይመራታል ተብሎ ይጠበቃል።  

🇩🇿 አልጀርያ 

የተሳትፎ ብዛት – 18

ምርጥ ውጤት – አንድ ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ (1990)

በወጣቱ አሰልጣኝ ጃማል በልማዲ እየተመሩ ምድብ ‘D ‘ በአስራ አንድ ነጥብ በበላይነት ያጠናቀቁት የምድረ በዳ ቀበሮዎች በውድድሩ ከሚጠበቁ ቡድኖች ይጠቀሳሉ። የነበራቸውን ተደናቂ ስብስብ የሚተካ የትውልድ ክፍተት አጋጥሟቸው እንደ ቀደሙ ዓመታት በቡድናቸው ውስጥ ኮከቦች ማካተት ያልቻሉት አልጀርያዎች ከብዙዎች ግምት ውጭ ቤኒን ፣ ቶጎ እና ጋምቢያ ከነበሩበት ቀላል ምድብ ተቸግረው ነበር ያለፉት።

አሰልጣኝ ጃማል በልማዲ ባለፈው ውድድር ዓመት በካርሎ አንቾሎቲ የቋሚነት ዕድል የተነፈገው ፋውዚ ጉልሃምን ከስብስባቸው ውጭ ሲያደርጉት በማጣርያው ሳይጠበቅ የቡድኑ የነብስ አዳኝ የነበረው የአልሳዱ አጥቂ ባግዳድ ቦኔጃህ፣ ያሲን በራሂሚ ፣ ሶፍያን ፌጉሊ እና ርያድ ማህሬዝ ላይ ተስፋ አድርገው ወደ ግብፅ አምርተዋል።

አሰልጣኝ ጀማል በልማዲ በማህበራዊ የጌም ድረ ገፅ ላይ መቀመጫውን ገልጦ በመታየቱ የብዙዎች መነጋገርያ ሆኖ የነበረው ሃሪስ በልከብላ በዲስፕሊን ግድፈት ምክንያት ከስብስባቸው ውጭ በማድረጋቸው በብዙ አክራሪ አልጀርያውን አድናቆት እየጎረፈላቸው ይገኛል።

🇰🇪 ኬንያ

የተሳትፎ ብዛት – 6

ምርጥ ውጤት – የምድብ ጨዋታ

ሀገራችን ኢትዮጵያ በነረችበት ምድብ ‘ F ‘ የነበረችው እና በመጀመርያው የምድብ ጨዋታ ታላቋን ጋና አሸንፋ የብዙዎች ትኩረት ስባ የነበረችው ኬንያ ከምድቡ በ7 ነጥቦች ሁለተኛ ደረጃ አግኝታ ነበር ከ2004 የቱኒዚያ አፍሪካ ዋንጫ በኃላ ከአስራ አምስት ዓመት በኃላ ወደ ውድድሩ ያለፈችው። ዘግይተው ወደ አፍሪካ ዋንጫው ማለፋቸው ያረጋገጡት ሐራምቤ ስታርስ ከአስራ አምስት ዓመታት በኃላ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ውድድሩ ያመራሉ። 

በ2018 ስታንለይ ኦኮምቢን ተክተው ወደ አሰልጣኝነት ከመጡ በኃላ በብሄራዊ ቡድኑ የሚታይ ለውጥ ያመጡት ሰባስትያን ሚኜ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው አለን ዋንጋን ጥለው ክለብ አልባው የቀድሞ የአል-ናስር ቤንጋዚ ወጣት አጥቂ መሱድ ጁማ ቻካን ወደ ስብስባቸው አካተው በማምራታቸው አነጋጋሪ ሆነዋል።

በቶትንሃሙ አማካይ ቪክቶር ዋንያማ የሚመሩት ሐራምቤ ስታርስ የማርቲዝበርክ ተከላካዩ ብርያን ማንደላ በጉዳት ከስብስባቸው ውጭ ሲያደርጉ ፣ በ2010 ከኢንተርሚላን ጋር የቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ ያነሳውና አሁን በስፔን ሪያል ኦቬይዶ የሚጫወተው ማክዶናልድ ማሪጋም የሚኜ ጥሬ አልደረሰውም።

ለቅድመ ዝግጅት ፓሪስ የሰነበቱት ሐራምቤ ስታርስ ባለፈው ሳምንት በፓሪስ ከማዳጋስካር ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ አድርገው በቪክቶር ዋንያማ ብቸኛ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ አንድ ለባዶ አሸንፈዋል።

🇹🇿 ታንዛንያ 

የተሳትፎ ብዛት – 2 ጊዜ

ምርጥ  ውጤት – የምድብ ጨዋታዎች

ከሌሎች ምድቦች በአንፃራዊነት ቀላል ከነበረው ምድብ ‘ L ‘ ሌሶቶ እና ኬፕ ቨርድን ጥለው ጎረቤታቸው ዩጋንዳን በማስከተል ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለሁለተኛ ጊዜ ለመሳተፍ ትኬት የቆረጡት ታንዛንያዎች ከወዲሁ ከከባዱ ምድብ የማለፍ ግምት ባይሰጣቸውም በሁለተኛው ተሳትፏቸው ምን እንደሚፈጥሩ አይታወቅም።

በሴካፋ ውድድሮች አልፎ አልፎ ከሚያስመዘግቧቸው ጥሩ ውጤቶች አልፈው በአህጉራዊ ውድድሮች ይህ የሚባል ታሪክ የሌላቸው ታንዛንያዎች ከሰላሳ ዘጠኝ  ዓመት በኃላ ነው ወደ አፍሪካ ዋንጫው የተመለሱት።

በቀላሉ የማጣርያ ምድብ የመጀመርያ ጨዋታዎች ነጥብ ጥለው ለማለፍ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው የነበሩት ‘ የታይፋ ስታርስ ‘ በዳሬ ሰላም ዩጋንዳና ኬፕቨርዴን በሜዳቸው በሰፊ ልዩነት አሸንፈው ነበር ከበርካታ ዓመታት በኃላ ወደ ውድድሩ የተመለሱት።

በምድቡ ተጠባቂ ጨዋታ፡ ሴኔጋል ከ አልጀርያ

በአፍሪካ ዋንጫው ጠንካራ የማጥቃት መስመር ያላቸው ሁለት ቡድኖች የሚያገናኘው ይህ ጨዋታ ማራኪ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።

እጅግ በርካታ ከክለቦቻቸው ጋር ምርጥ ዓመት ያሳለፉ ትላልቅ አጥቂዎች እና ጠንካራ የመከላከል ክፍል የያዘው የአሊዩ ሲሴ ስብስብ በዚህ ጨዋታ ይቸገራል ተብሎ ባይጠበቅም በርያድ ማህሬዝ እና ባግዳድ ቦኔጃህ የሚመሩት የምድረበዳ ቀበሮዎች ቀላል ተጋጣሚ እንደማይሆኑላቸው የታወቀ ነው።

ከምድቡ የሚጠበቅ ኮከብ ተጫዋች – ሳድዮ ማኔ 

በሊቨርፑል እጅግ ድንቅ ዓመት አሳልፎ በጣምራ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው ሴኔጋላዊው የመስመር አጥቂ በቴራንጋ አናብስት ውስጥ የሚጠበቅ ኮከብ ተጫዋች ነው። ሰይዶ ማኔ በ2002 የአፍሪካ ዋንጫ ሁለተኛ ደረጃ ከያዙበት ዓመት ውጭ ሞላላው ዋንጫ ለማንሳት ያልታደሉት ሴኔጋላውያን ዋንጫውን ያመጣልናል ብለው ከወዲሁ ተስፋ አድርገውበታል። ካሊዱ ኩሊባሊ፣ ሪያድ ማህሬዝ እና ቪንስንት ዋንያማም ሌሎች የምድቡ ከዋክብት ናቸው።

የምድቡ ጨዋታዎች

እሁድ ሰኔ 16 ቀን 2011

ሴኔጋል 2:00 ታንዛንያ

አልጄርያ 5:00 ኬንያ

ሐሙስ ሰኔ 20 ቀን 2011

ሴኔጋል 2:00 አልጄርያ

ኬንያ 5:00 ታንዛንያ

ሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2011

ታንዛንያ 4:00 አልጄርያ

ሴኔጋል 4:00 ኬንያ