በውድድሩ እጅግ በርካታ ተጠባቂ ጨዋታዎች ያሉት እና ከወዲሁ “የሞት ምድብ” የተሰኘው ይሄ ምድብ ሞሮኮ ፣ አይቮሪኮስት፣ ደቡብ አፍሪካ እና ናሚቢያን የያዘ ነው። ምድቡ በማጣርያው ጥሩ ተፎካካሪ የነበሩ፣ የስብስብ ደረጃቸው የላቀ እና የውድድሩን ዋንጫ ያነሳሉ ተብለው የተጠበቁ ሦስት ሃገራትን የሚያገናኘው ይህ ምድብ ከሌሎች ምድቦች የተለየ ትኩረት እየተሰጠው ይገኛል።
🇲🇦 ሞሮኮ
የተሳትፎ ብዛት – 17
ምርጥ ውጤት – የውድድሩ አሸናፊ (1976)
ፈረንሳዊው ውጤታማ አሰልጣኝ ሄርቬ ሬናርድ ከቀጠሩ በኃላ ወደ ቀድሞ ዝናቸው እየተመለሱ የሚገገኙት ሞሮኮዎች ዋንጫውን ለማንሳት ከተገመቱት ቡድኖች ውስጥ ይገኙበታል።
የባለፈው ውድድር አሸናፊ ካሜሩን ፣ ማላዊ እና ኮሞሮስ ከነበሩበት ምድብ ‘ B ‘ ካሜሩንን በግብ ክፍያ በመብለጥ ምድቡን በበላይነት ያጠናቀቀችው ሞሮኮ በዚ ሰዓት ማራኪ እግር ኳስ ከሚጫወቱ የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች በቀዳሚነት ትጠቀሳለች።
ስብስቡ በዚ ዓመት በየክለቦቻቸው የደመቁ እንደነ ሐኪም ዚያች እና ናስር ማዛሮ የመሳሰሉ ተጫዋቾችን የያዘ ሲሆን ምንም እንኳ አስፈሪ እና ባለ ብዙ አማራጭ የማጥቃት ክፍል ቢኖረውም በሜህዲ ቤናሽያ የሚመራው የተከላካይ ክፍላቸው ግን ከሌሎች የቡድኑ ክፍሎች ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ጥራት ያለው ክፍል ነው።
ሞሮኮዎች በአያክስ አምስተርዳም ድንቅ ዓመት ያሳለፉት ሃኪም ዝየቺ እና ናስር ማዛሮ ላይ ተስፋ ጥለው ወደ ፈርዖኖቹ ሃገር ሲያመሩ በሳዑዲ ዓራብያ ሊግ በሠላሳ አራት ጎሎች የሊጉ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ የጨረሰው ዓብዱረዛቅ ሐምዱላህን ትተው ወደ ውድድሩ አምርተዋል። የበርካኔው ተቀዳሚ ግብ ጠባቂያቸው ዓብደላ ሐሚድ በጉዳት በማጣታቸውም በአናስ ዝንቲ ተክተዋል።
ከበርካታ ዓመታት በኃላ በብዙ ተመልካቾች ለዋንጫ የታጩት ሞሮኮዎች በአቋም መለኪያ ጨዋታ በአርጀንቲና፣ ጋምቢያ እና ዛምቢያ በሜዳቸው ተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች መሸነፋቸው ከወዲሁ ብዙ ሞሮካውያን አሳስቧል።
🇨🇮 አይቮሪኮስት
የተሳትፎ ብዛት – 23
ምርጥ ውጤት – ሁለት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ (1992፣ 2015)
ወርቃማው ትውልድ ካበቃ በኋላ ትልቅ የሆነ የትውልድ ክፍተት አጋጥሟት የነበረችው አይቮሪኮስት ከባለፉት ሁለት ዓመታት ስብስቧ በጥራት በእጅጉ የሚልቅ ስብስብ ይዛ ትገኛለች።
በማጣርያው በምድብ ‘ H ‘ ጊኒን ተከትላ ወደ ውድድሩ ያለፈች ሲሆን እንደባለፉት ዓመታት ሁነኛ የዋንጫ ተፎካካሪ ትሆናለች ተብሎ ባይጠበቅም ባለፈው የውድድር ዓመት ከክለቦቻቸው ጋር ድንቅ ዓመት ያሳለፉት እና በዚህ የዝውውር መስኮት የበርካታ ትላልቅ ክለቦች ትኩረት ስበው የሚገኙት የሊሉ ኒኮላስ ፔፔ እና የክሪስታል ፓላሱ ዊልፍሬድ ዛሃን መያዛቸው ግን የበርካቶች ትኩረት ስበዋል።
በኢብራሂም ካማራ የሚመሩት ዝሆኖቹ በማጣርያው ጨዋታዎች ባልተለመደ መልኩ ተቸግረው የታዩ ሲሆን ከቀላሉ ምድብም እንደባለፉት ግዜያት በቀላሉ ለማለፍ ተቸግረው ጊኒን ተከትለው ነበር ወደ አፍሪካ ዋንጫው ያለፉት።
🇿🇦 ደቡብ አፍሪካ
የተሳትፎ ብዛት – 9
ምርጥ ውጤት – አንድ ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ (1996)
ከሃገር ውስጥ ሊግ በርካታ ተጫዋቾች በማስመረጥ ቀዳሚ የሆኑት ባፋና ባፋናዎች በሞት ምድቡ ላለመሞት ጠንካራ ፉክክር ይጠብቃቸዋል።
ናይጄርያ፣ ሊቢያ እና ሲሸልስ በነበሩበት ምድብ ‘F’ ጠንካራ ፉክክር በማድረግ ከመሪዋ ናይጀርያን በአንድ ነጥብ ዝቅ ብለው ምድቡን ያጠናቀቁት ደቡብ አፍሪካዎች ከባለፉት አፍሪካ ዋንጫዎች የተሻለ ጉዞ ለማድረግ ከወዲሁ ተስፋ ቢሰንቁም ከጠንካራው ምድብ ማለፍ ግን ቀላል እንደማይሆንላቸው የታወቀ ነው።
በማጣርያው ጠንካራ የማጥቃት ክፍል የነበራቸው ባፋና ባፋናዎች እጅግ በርካታ ግቦች በተቆጠሩበት ምድብ አስር ግቦች አስቆጥረው ከመሪዋ ናይጀርያዊ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብለው ነበር ያጠናቀቁት።
ከሃገር ውጭ ሊግ ስድስት ተጫዋቾች ብቻ ወደ ስብስባቸው ያካተዩት ስትዋርት ቤክሳተር በማጣርያው እራት ግቦች ያስቆጠረው ፔርሲ ታው በስብስባቸው ሲያካትቱ ሳይጠበቅ ክረሚት ኤረስመስ፣ ቤን ሞተሽዋሪ እና ፎርቹን ማካሪንጌን ከስብስባቸው ውጭ አድርገዋል።
🇳🇦 ናሚቢያ
የተሳትፎ ብዛት – 2
ምርጥ ውጤት – የምድብ ጨዋታዎች
ሁለተኛ ተሳትፎዋን የምታደርገው ናሚቢያ ከሞት ምድብ ዝቅተኛ ግምት ተሰጥቷት ወደ ውድድሩ ትገባለች። ዛምቢያ ፣ ጊቢ ቢሳውና ሞዛምቢክ ከነበሩበት ምድብ ጊኒ ቢሳውን ተከትለው በስምንት ነጥብ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ያልፉት ናሚቢያዎች የውድድሩ ተሳተፊ ቡድኖች ወደ ሃያ አራት ከፍ ማለቱ ተጠቅመው በውድድሩ ከበርካታ ዓመታት በኃላ ከሚሳተፉት ቡድኖች ውስጥ ናቸው።
የድሬዳዋ ከተማው አጥቂ ኢታሙና ኬይሙኔ የያዙት ናሚቢያዎች ባለፈው ሳምንት በዱባይ በተካሄደው አቋም መለኪያ ጨዋታ ጋናን አሸንፈው በጥሩ የማሸነፍ መንፈስ ነው ወደ ትልቁ ውድድር የሚገቡት።
“ልባሞቹ ተፋላሚዎች” ዘጠኝ ተጫዋቾች ብቻ ከሃገር ውስጥ ሊጋቸው የመረጡ ሲሆን በእንግሊዙ ብላክበርን ሮቨርስ የሚጫወተው ተስፈኛው የ21 ዓመት ተጫዋች ርያን ሲማሲኩ እና የጀርመን ዝርያ ያለው አንጋፋው ማንፈርድ ስታርኬ ተስፋ አድርገው ወደ ውድድሩ ይገባሉ።
የምድቡ ተጠባቂ ጨዋታ – ሞሮኮ ከ አይቮሪኮስት
ሁለት ጠንካራ የማጥቃት ክፍል ያላቸው ቡድኖች የሚያገናኘው ይህ ጨዋታ ከሌሎች የምድቡ ጨዋታዎች በተሻለ ጥሩ ፉክክር እና ማራኪ ጨዋታ ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል። በሐኪም ዚያች እና ናስር ማዛሮ የሚመራ ጥሩ የማጥቃት ክፍል ያላቸው ሞሮኮዎች በጨዋታ ብልጫ ጎል በማስቆጠሩ ረገድ ጥሩ ቢሆኑም በኒኮላስ ፔፔ ፣ ዊልፍሬድ ዛሃ እና ማክስዌል ኮርኔት የሚመራው አይቮሪኮስት ጠንካራ የማጥቃት ክፍል ለመመከት እንደሚቸገሩ የታወቀ ነው።
በምድቡ የሚጠበቅ ኮከብ ተጫዋች፡ ሐኪም ዚያች እና ኒኮላስ ፔፔ
በርካታ ተስፈኛ ወጣቶችን የያዘው ምድብ አራት ከወዲሁ ብዙ አዳዲስ ኮከቦች ለእግር ኳስ ተመልካቹ ያስመለክታል ተብሎ ሲጠበቅ ዘንድሮ ከአያክስ ጋር የደመቀው እና ከሁለት ዓመት በፊት ከሆላንድ ይልቅ ሞሮኮን ያስቀደመው ሃኪም ዚያች ልዩነት እንደሚፈጥር ይገመታል። የአይቮሪኮስቱ ተስፈኛ አጥቂ ኒኮላስ ፔፔ ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት የሚጠበቅ ሌላው ኮከብ ነው።
የምድብ ጨዋታዎች
እሁድ ሰኔ 16 ቀን 2011
ሞሮኮ 11:30 ናሚቢያ
ሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2011
አይቮሪኮስት 11:30 ደቡብ አፍሪካ
ዓርብ ሰኔ 21 ቀን 2011
ሞሮኮ 2:00 አይቮሪኮስት
ደቡብ አፍሪካ 5:00 ናሚቢያ
ሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2011
ደቡብ አፍሪካ 1:00 ሞሮኮ
ናሚቢያ 1:00 አይቮሪኮስት