ከወዲሁ የብዙዎች ትኩረት ከሳቡት ምድቦች አንዱ የሆነው ይህ ምድብ ሶስት በተመሳሳይ ጥሩ ወቅታዊ ብቃት የሚገኙት ሃገሮች እና እንግዳዋ ማውሪታንያ የያዘ እንደመሆኑ ተመጣጣኝ ፉክክር እና ማራኪ እንቅስቃሴ ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
🇹🇳 ቱኒዚያ
የተሳትፎ ብዛት – 19
ምርጥ ውጤት – አንድ ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ (2004)
ግብፅ፣ ኒጀር እና እስዋቲኒ (የቀድሞ ስሟ ስዋዚላንድ) ከነበሩበት ምድብ ‘ F ‘ በበላይነት አጠናቃ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ያለፈችው ቱኒዝያ በውድድሩ ማራኪ እግር ኳስ ያሳያሉ ተብለው ከሚጠበቁት ሃገራት አንዷ ናት። እንደሌሎች ለዋንጫ የታጩት ቡድኖች በትልቅ ደረጃ የደመቁ ኮከኮች ባትይዝም በዚህ ዓመት እና ባለፉት ሁለት ዓመታት በአፍሪካ ውድድሮች ከክለቦቻቸው ጋር ጥሩ ስኬት ያላቸው በርካታ ተጫዋቾች የያዘች ሃገር ናት።
ከዚ ውጭ በፈረንሳዩ ጂዦ ጥሩ ዓመት ያሳለፈው እና በማጣርያ ጨዋታዎች ለሃገሩ አራት ግቦች ያስቆጠረው ናይም ስሊቲ ይዛ ወደ ውድድሩ ያቀናችው ቱኒዚያ እንደ ቡድን የሚጫወት ጥሩ ቡድን ብትይዝም ግብ ማስቆጠር ላይ ያላት ትልቅ ክፍተት የቡድኗ ደካማ ጎን ነው። በዚህም የቡድኑ የግብ ማስቆጠር ኃላፊነት በአጥቂው ናይም ስሊቲ እና ጥቂት ተጫዋቾች የተንጠለጠለ ነው።
ሳይጠበቅ የአልአህሊው የመስመር ተከላካይ ዓሊ ማሎልን ጥለው ወደ ውድድሩ ያመሩት አሰልጣኝ አልያን ዠሬስ ዋሂብ ካዝሪ ፣ ናይም ስሊቲ እና ከፈረንሳይ ሴንትኢትየን የመረጡት ኮከብ ግብአስቆጣርያቸው ዋህቢ ካዝሪ ወሳኝ ተጫዋቾቻቸው ናቸው።
ለአፍሪካ ዋንጫው አምስት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ያደረጉት የካርቴጅ ንስሮች በመጀመርያው ጨዋታ በአልጄርያ ከደረሰባቸው ሽንፈት ውጭ ታላቋ ክሮሺያን ጨምሮ ብሩንዲ እና ኢራቅን አሸንፈዋል።
ቱኒዝያዎች ከአፍሪካ ዋንጫው በዕድሜ ትንሹ ቡድን ይዘው ወደ ውድድሩ ያመራሉ ፤ የቡድኑ አማካይ ዕድሜም 24 ነው።
🇲🇱 ማሊ
የተሳትፎ ብዛት – 10
ምርጥ ውጤት – ሁለተኛ ደረጃ (1972)
ብሩንዲ፣ ደቡብ ሱዳን እና ጋቦን ከነበሩበት ቀላል ምድብ ‘ C’ በቀላሉ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ያለፉት ማሊዎች ባላቸው ለውድድሩ እንግዳ የሆነ ስብስብ ቀላል ግምት ቢሰጣቸውም በማጣርያው ምንም ሽንፈት ያላጋጠመው ስብስባቸው ከብዙዎች ግምት ውጭ ጥሩ ጉዞ የማድረግ ዕድሉ የሰፋ ነው።
ከዋናው ብሄራዊ ቡድን በታች ባሉት ብሄራዊ ቡድኖች በአህጉራዊ እና ዓለማቀፋዊ ውድድሮች ጥሩ ስም ያላቸው ማሊዎች በ2012 እና 2013 የተካሄዱት የአፍሪካ ዋንጫዎች በተከታታይ ሶስተኛ ደረጃ ይዘው መጨረሳቸው ይታወሳል።
ከሃገር ውስጥ ሊጋቸው ሶስት ተጫዋቾች ብቻ በመጨረሻው ስብስብ ያካተቱት ማሊዎች በስፖርቲንግ ሊዝበን የሚጫወተው አብዱላይ ዲያቢ እና አንጋፋው የቀድሞ የሌስተር እና ዋትፎርድ ተከላካይ ሞላ ዋጉ ከቡድናቸው የሚጠበቁ ተጫዋቾች ናቸው።
🇦🇴 አንጎላ
የተሳትፎ ብዛት – 8
ምርጥ ውጤት – ሩብ ፍፃሜ
ከረጅም ጊዜያት በኃላ ወደ ጥሩ ብቃት መጥተው በማጣርያው ምድባቸውን በበላይነት አጠናቀው ወደ አፍሪካ ዋንጫው ያለፉት አንጎላዎች በውድድሩ ጥሩ ጉዞ ያደርጋሉ ተብለው ከሚገመቱ ቡድኖች ውስጥ ናቸው።
ቡርኪናፋሶ ፣ ቦትስዋና እና ማውሪታንያ ከነበሩበት ምድብ ‘ i’ በበላይነት አጠናቀው ወደ አፍሪካ ዋንጫው ያለፉት አንጎላዎች በማጣርያው ላይ ጠንካራ የማጥቃት ክፍል ከነበራቸው ቡድኖች መካከል ይጠቀሳሉ።
በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኙት በስራቨን ቫሲለቪች የሚመሩት አንጎላዎች ወደ ንዋኮቾት አምርተው በማውሪታንያ ከተሸነፉበት የማጣርያው ጨዋታ ውጭ በስድስት የመጨረሻ ጨዋታዎች ሽንፈት አለማስተናገዳቸው በቡድኑ በጥሩ ጎኑ የሚነሳ ነው።
አብዛኞቹ የብሄራዊ ቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች ከሃገራቸው ትላልቅ ክለቦች ያካተቱት አንጎላዎች የላዝዮው አንጋፋ ተከላካይ ባርቶሚዮ ጃሲንቶ ካሲንጋ እና ትውልደ ፖርቹጋሉ የስፖርቲንግ ሊዝበን ቀኝ መስመር ተከላካይ ቡርኖ ሚግዌል ቦይላቮ ጋስፐር የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች ናቸው።
🇲🇷 ማውሪታንያ
የተሳትፎ ብዛት – የመጀመሪያ ተሳትፎ
ምርጥ ውጤት – የመጀመሪያ ተሳትፎ
ከዚህ በፊት በእግር ኳስ ዙርያ ብዙም ስማቸው የማይነሱት ማውሪታንያዎች በአህጉሪቱ ትልቅ ውድድር ሲሳተፉ የመጀመሪያቸው ነው።
በማጣርያው ጨዋታዎች ሦስት ጥሩ ግምት የሚሰጣቸው ሃገራት አንጎላ ፣ ቡርኪናፋሶ እና ቦትስዋናን በማሸነፍ የማጣርያ ጉዟቸውን ቀላል ያደረጉ ሲሆን ከስድስት ተጫዋቾች በስተቀር ሙሉ ቡድናቸው ከሃገር ውጭ በሚጫወቱ ተጫዋቾች አዋቅረው ወደ ግብፅ አምርተዋል።
በምድብ ‘ i ‘ ከ አንጎላ ፣ ቡርኪናፋሶ እና ቦትስዋና ተደልድለው አንጎላን ተከትለው በሁለተኝነት ወደ ውድድሩ ለመጀመርያ ጊዜ ያለፉት የችንጉቲ አናብስት ባለፈው ዓመት የካፍ የዓመቱ ምርጥ ቡድን ተብለው መሸለማቸው የሚታወስ ነው። እንደ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሃገራት በርካታ ተጫዋቾች ከፈረንሳይ ሊጎች የመረጡ ሲሆን የኦግዜሩ ዓብዱል ባ እና የቫላዶሊዱ ሃከን አል ዒድ የቡድኑ ኮከብ ተጫዋቾች ናቸው።
ማውሪታንያዎች ወደ ግብፅ ከማምራታቸው በፊት ካደረጓቸው ሶስት ጨዋታዎች በጋና እና ቤኒን ሽንፈት ሲደርሳቸው ማዳጋስካርን 3-1 አሸንፈዋል።
የምድቡ ተጠባቂ ጨዋታ፡ ቱኒዚያ ከ አንጎላ
ሁለት የማጣርያው ምድባቸውን በበላይነት ያጠናቀቁ ቡድኖችን የሚያገናኘው ይህ ጨዋታ በምድቡ የሚጠበቅ ፍልሚያ ነው። በቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ አጥቂ ማኑቾ የሚመራ ጥሩ የማጥቃት ክፍል ያላቸው አንጎላዎች ከጥሩ ፍሰት ያለው እግርኳስ ከሚጫወቱት ቱኒያዎች የሚያደርጉት ይህ ጨዋታ የምድቡ የመጀመሪያው መርሐ ግብር ነው።
ከምድብ የሚጠብቅ ኮከብ ተጫዋች፡ ናይም ስሊቲ
በብዙ የእግር ኳስ ስሙ የገነነ ኮከብ እና በዚህ ዓመት በትልቅ የአውሮፓ ክለቦች የደመቀ ተጫዋች የሌለው ምድብ አምስት ኮከቡ በማጣርያው ሳይጠበቅ የቱኒዝያ የጎል አንፍናፊ የነበረው የ26 ዓመቱ ናይም ስሊቲ ነው። በፈረንሳዩ ዲዦ የሚጫወተው ይህ የአጥቂ አማካይ በማጣርያ ጨዋታዎች በስሙ አራት ግቦች ማስቆጠር ችሏል። ከሱ በተጨማሪም ሌላው የሃገሩ ልጅ ዋህቢ ካዝሪ ሌላው የሚጠበቅ ተጫዋች ነው።
የምድቡ ጨዋታዎች
ሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2011
ቱኒዚያ 2:00 አንጎላ
ማሊ 5:00 ማውሪታኒያ
ዓርብ ሰኔ 21 ቀን 2011
ቱኒዚያ 11:30 ማሊ
ቅዳሜ ሰኔ 22 ቀን 2011
ማውሪታኒያ 11:30 አንጎላ
ማክሰኞ ሰኔ 22 ቀን 2011
ማውሪታኒያ 4:00 ቱኒዚያ
አንጎላ 4:00 ማሊ