ሪፖርት | ባህር ዳር ከተማ ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ ተጋርቷል

የ28ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ መደረግ ሲጀምሩ ባህር ዳር ላይ ባህር ዳር ከተማ በሜዳው ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ ተጋርቷል።

እምብዛም ደጋፊዎች ባልተገኙበት ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ባህር ዳሮች በአንፃራዊነት ተጭነው ሲጫወቱ ድቻዎች ደግሞ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው በመከላከል ጨዋታቸውን አከናውነዋል።

ባለሜዳዎቹ በ27 ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ከተጠቀሙበት 11 ተጫዋቾች አምስት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም ግብ ጠባቂው ምንተስኖት አሎን ጨምሮ ቴዎድሮስ ሙላቱ፣ ዜናው ፈረደ፣ ፍቃዱ ወርቁ እና እንዳለ ደባልቄን በማሳረፍ ሀሪስተን ሄሱ፣ አስናቀ ሞገስ፣ ኤሊያስ አህመድ፣ ወሰኑ ዓሊ እና ጃኮ አራፋትን አስገብተዋል። ተጋባዦቹ በበኩላቸው በ27ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ፎርፌ ካገኙበት የጅማ አባጅፋሩ ጨዋታ በፊት ካከናወኑት የፋሲል ከነማ ጨዋታ ሁለት ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም እሸቱ መና እና ባዬ ገዛኸኝን በኃይሌ እሸቱ እና ፀጋዬ ብርሃኑ በመተካት ለጨዋታው ቀርበዋል።

ጨዋታው በተጀመረ በ5ኛው ደቂቃ በፈጣን የመስመር ላይ የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ተጋባዦቹ የግብ ክልል የደረሱት ባህርዳሮች ሳላምላክ ተገኝ ከቀኝ መስመር ባሻማው እና አስናቀ ሞገስ በሞከረው ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ጥረው ነበር። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ያሰቡ የሚመስሉት ወላይታ ድቻዎች ጥሩ ሙከራ በአ/ሰመድ ዓሊ አማካኝነት ሰንዝረው ግብ ጠባቂው ሀሪስተን ሄሱ አድኖባቸዋል። በደቂቃ ልዩነት ዳግም ኳስ ያገኙት ድቻዎች በረከት ወልዴ ከርቀት አክርሮ በሞከረው ሙከራ እጅጉን ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር።

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ኳስ በመቀባበል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ አስበው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ባህር ዳሮች በ11ኛው ደቂቃ በመሰረቱት ጥሩ ኳስ የመጀመሪያ ግብ ለማስቆጠር ጥረው የግቡ ቋሚ መልሶባቸዋል። በተቃራኒው በእነዚህ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ዲቻዎች እምብዛም ወደ ባህርዳሮች የግብ ክልል ሲደርሱ አልተስተዋለም። ድቻዎች ምንም እንኳን በራሳቸው ኳስ መስርተው ለማጥቃት ባይችሉም በሚያገኟቸው አንዳንድ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች እና የቆሙ ኳሶች ግብ ሲፈልጉ ተስተውሏል። በዚህም በ12ኛው ደቂቃ ደጉ ደበበ በሞከረው የቅጣት ምት እና ኃይሌ እሸቱ በ23ኛው ደቂቃ አክርሮ በመታው ኳስ ወደ ግብ ቀርበው ነበር። የጣና ሞገዶቹ የበላይነታቸውን በጎል ለማሳመር ተጭነው መጫወታቸውን ቀጥለው በ19ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥረዋል። ተስፋዬ አለባቸው ግርማ ዲሳሳ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የቅጣት ምት የመሃል ሜዳ ተጨዋቹ ዳንኤል ኃይሉ መትቶ ግብ አስቆጥሯል።

ብልጫ ወስደው ሲንቀሳቀሱ የታዩት የአሰልጣኝ ጳውሎስ ተጨዋቾች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በ27ኛው ደቂቃ በወሰኑ ዓሊ አማካኝነት ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሰባት ደቂቃ ሲቀረው ወደ ባህር ዳሮች የግብ ክልል ያመሩት ድቻዎች የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። የባህር ዳር ተጨዋቾችን እና ደጋፊዎች ደስተኛ ያላደረገው የፍፁም ቅጣት ምቱን አ/ሰመድ ዓሊ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን አቻ ቢያደርግም ጨዋታው ለአራት ደቂቃዎች ተቋርጧል። ውሳኔውን በመቃወም አቤቱታ ያሰሙት የባህር ዳር ተጨዋቾች ዳኛው ላይ ቅሬታ ቢያሰሙም ጨዋታው ከአራት ደቂቃ መቋረጥ በኋላ ጀምሯል። በተሰጠባቸው የፍፁም ቅጣት ምት የተደናገጡ የሚመስሉት ባህር ዳሮች ግቡ ከተቆጠረባቸው በኋላ ተቀዛቅዘው ታይተዋል። በተቃራኒው የተነቃቁ የሚመስሉት ዲቻዎች ወደ መልበሻ ክፍል ከማምራታቸው አንድ ደቂቃ በፊት ጥሩ አጋጣሚ በኃይሌ እሸቱ አማካኝነት ፈጥረው መክኖባቸዋል።

በእረፍት ሰዓት የባህር ዳር ከተማ ደጋፊዎች ማኅበር ለወላይታ ድቻ ስፖርት ክለብ፣ ለክለቡ ደጋፊዎች ማኅበር እና አሁን በድቻ ለሚገኘው የቀድሞ ተጫዋቻቸው ኃይማኖት ወርቁ ስጦታ አበርክተዋል።

በመጨረሻዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች ተቀዛቅዘው የነበሩት የጣናው ሞገዶቹ ከእረፍት መልስ እጅጉን በርትተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። ጨዋታው እንደ ተጀመረም ጥሩ ሙከራ በኤሊያስ አህመድ አማካኝነት ሞክረው ወቶባቸዋል። ከስምንት ደቂቃዎች በኋላም ዳግም ወደ ወላይታ ድቻዎች የግብ ክልል በመድረስ ሙከራ ሰንዝረዋል። በዚህ ደቂቃ የተሰጠውን የቅጣት ምት የመሃል አጥቂው ጃኮ አራፋት በጥሩ ሁኔታ ቢመታውም ግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት አምክኖበታል። ባህር ዳሮች ለማጥቃት ትተውት የሚወጡትን ሰፊ ሜዳ በፍጥነት በመጠቀም ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎችን ሲፈጥሩ የታዩት የጦና ንቦቹ ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል። በዚህም በ57ኛው ደቂቃ ፀጋዬ ብርሃኑ በጥሩ አቋቋም ያገኘውን ኳስ ሲሞክር ተከላካዮች ተረባርበው ያወጡበት እንዲሁም በ60ኛው ደቂቃ በረከት ወልዴ በሞከረው ነገር ግን መረብ ላይ ባላረፈው ኳስ የባህር ዳርን ግብ ፈትሸዋል።

ከፍተኛ የአጨራረስ ችግር ሲታይባቸው የነበሩት ባህር ዳሮች ወደ መሪነት ለመቀየር ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ጨዋታው ቀጥሏል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ 15 ደቂቃዎች ሲቀሩት ግርማ ዲሳሳ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ቢመታውም ኳስ እና መረብ ማገናኘት አልቻለም። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ የግቡ ባለቤት ዳንኤል ኃይሉ በድጋሚ ከቅጣት ምት ግብ ለማስቆጠር ቢጥርም የዲቻዎች ግብ ጠባቂ ታሪክ ጌትነት እንደምንም አምክኖበታል። በጥብቅ የመከላከል አደረጃጀት ሲጫወቱ የነበሩትን ድቻዎች ማስከፈት ያልቻሉት ባህር ዳሮች በጭማሪ ደቂቃ ወሰኑ ከሞከረው የግምባር ኳስ ውጪ ምንም ሙከራ ሳይሰነዝሩ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡