የፌዴሬሽኑ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ቅጣት የመቐለ 70 እንደርታ ቅሬታ

” በተለያየ ምክንያት የካስ ውሳኔ ዘግይቶ የሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ በዝግ አድርገን በካስ የጠየቅነው ውሳኔያችን በጎ ምላሽ ካገኘ ለክስ ማስያዣ ያወጣነው አንድ ሺ የስዊዝ ፍራንክ ጨምሮ እስከ ሁለት ሚልዮን የሜዳ ገቢ ካሳ እንጠይቃለን”

ከሁለት ሳምንት በፊት ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ መቐለ 70 እንደርታን አንድ ጨዋታ በዝግ እና የገንዘብ ቅጣት መቅጣቱን ይታወሳል፤ ከቅጣቱ በኃላም ቡድኑ ውሳኔውን ተቃውሞ ቅጣቱ በእግድ እንዲቆይ ለፌዴሬሽኑ ደብዳቤ ማስገባቱ ቢታወስም እስካሁን ድረስ የጨዋታው እጣ ፈንታ በውል አልታወቀም፤ ፌደሬሽኑም ስለ ጉዳዩ በይፋ ያለው ነገር የለም።

በዝግ እንዲካሄድ ስለተወሰነው ጨዋታ እጣ ፈንታ እና ስለ ቅጣቱ ከሶከር ኢትዮጵያ ረዘም ያለ ቆይታ ያደረጉት የመቐለ 70 እንደርታ የስራ አስፈፃሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ልባርጋቸው ምሕረቱ ቅጣት ተግባራዊ የሚሆንበት አግባብ እንደሌለ ገልፀው ጉዳዩ ወደ ካስ እንደመሩት እና መልስ እየተጠባበቁ እንደሆኑ ገልፀዋል።

” ይህን ውሳኔ በእግድ እንዲቆይ ጠይቀናል። ጨዋታውም ለደጋፊዎች ክፍት ይሆናል ብለን እንጠብቃለን ፤ ጉዳዩ ወደ እግር ኳስ ገላጋይ ፍርድቤት (Cas , Court of Arbitration for Sport) ወስደነዋል፤ ካስም ክሳችን እንደደረሰው በደብዳቤ አረጋግጦልናል። የፈጀውን ግዜ ፣ ገንዘብም ጉልበትም ይፍጅ ትክክለኛው ውሳኔ እስኪሰጠን በህጉ መሰረት እንከራከራለን የፌደሬሽኑ ውሳኔም እናስቀይረዋለን” ብለዋል።

” እንደሚታወቀው ደደቢት ከ ፋሲል ነበር ጨዋታው። ይህ ማለት ደሞ ቡድናችን በዛ ዕለት ሜዳ ውስጥ አልነበረም። ሲቀጥልም የዲሲፕሊን ኮሚቴ ውሳኔው ከመወሰኑ በፊት የዳኛው እና የኮምሽነር ሪፖርት አይቶአል የሁለቱን ሪፖርት ግን የተለያየ ነበር ፤ የኮምሽነሯ በሜዳው የመቐለ መለያ የለበሱ የመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊዎች ናቸው የሚል ነው መረጃው ምንም የተጨበጠ ማረጋገጫ ሳይኖረው ነው የተቀመጠው የዳኛው ሪፖርት ደሞ የመቐለ 70 እንደርታ መለያ የለበሱ ተመልካቾች ነው የሚለው ተመልካች እና ደጋፊ ይለያያል እና የሁለቱም እርሰ በርሱ የሚጣረስ ነው” ብለዋል።

” ለዲስፕሊን ኮሚቴ ሜዳ ውስጥ የነበሩት የመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊዎች ስለመሆናቸው ምንም ማረጋገጫ አልተሰጠውም፤ በመሰረቱም እነሱ በርግጠኝነት የመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊዎች ስለመሆናቸው የሚገልፅ የተጨበጠ ማስረጃ የለም ሊኖርም አይችልም። ማልያ ስላደረገ ብቻ የአንድን ክለብ ደጋፊ ነው ማለት አይቻልም።

” የዲስፕሊን ኮሚቴ በአንቀፅ 62 ተራ ቁጥር 2 መሰረት ደደቢትን ጥፋተኛ ነው ብሎ ቡድኑ ላይ ቅጣት ሲወስን ደደቢትም ቅጣቱን አምኖ ተቀብሏል ስለ ቅጣቱ ክብደት ካነሳው ጥያቄ ውጭ ስለዚ በዳዩ አምኖ ቅጣቱን ከተቀበለ በኃላ ቅጣቱ ወደ ክለባችን የሚዞርበት ምክንያት የለም ” ብለዋል።

ይህ ጉዳይ በይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ የመታየት የህግ አግባብ የለም ያሉት አቶ ልባርጋቸው ምሕረቱ ውሳኔ እንደሚሽሩት ገልፀው ቡድናቸው አለአግባብ በዝግ ተጫውቶ በዓለም አቀፍ እግር እግርኳስ ገላጋይ ፍርድ ቤት በውሳኔው የሚያሸንፍ ከሆነ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚልዮን እስከ ሁለት ሚሊዮን የስቴድየም ገቢ እና ለክስ ማስፈፀምያ ያወጡት ወጪ ካሳ እንደሚጠይቁ ገልፅዋል።

” ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ውሳኔው ከመወሰኑ በፊት የመቐለ እና የፋሲል የነጥብ መቀራረብ እና ተፎካካሪነት በማየት ብቻ ነው ደጋፊው የመቐለ ነው ብሎ የደመደመው ፤ ይህ ደሞ በጣም ስህተት ነው ይህ የተጨበጠ ማስረጃ ሊሆን አይችልም ይግባኝ ባዩ ቡድን እኛን ለማስቀጣት የሸረበው ሴራ ነው። ሌላ እምናነሳው ትልቅ ሃሳብ ደሞ ‘ በአንቀፅ 90 ቁጥር 2 እና አንቀፅ 97 ተራ ቁጥር 4 ሐ ‘ መሰረት ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ይህንን ውሳኔ የማየት ስልጣን የለውም።

” ካስ የክስ ደብዳብያችን እንደደረሰው ገልፆልናል ይህም ለፌደሬሽኑ አረጋግጠናል በተለያየ ምክንያት የካስ ውሳኔ ዘግይቶ የሊጉ የመጨረሻ ጨዋታ በዝግ አድርገን በካስ የጠየቅነው ውሳኔያችን በጎ ምላሽ ካገኘ ለክስ ማስያዣ ያወጣነው አንድ ሺ የስዊዝ ፍራንክ ጨምሮ እስከ ሁለት ሚልዮን የሜዳ ገቢ ካሳ እንጠይቃለን ” ብለዋል።

ከደቡብ ፖሊስ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ለደጋፊዎች ክፍት ይሆናል ብለው እንደሚጠብቁ የተናገሩት አቶ ልባርጋቸው ምሕረቱ ካስ በህጉ ውሳኔው እንደሚሽረው እርግጠኛ እንድሆኑ ይናገራሉ። ” ይህ ውሳኔ በእግድ እንዲቆይ ጠይቀናል ስለዚ ደጋፍያችን ወደ ሜዳ ይገባል ብለን እንጠብቃለን ጉዳዩም ወደ ካስ ወስደነዋል የፈጀው ገንዘብ ፣ ጊዜ እና ጉልበት ይፍጅ እስከ መጨረሻው ትክክለኛው ውሳኔው ለማግኘት እንሰራለን ውሳኔውም ይሻራል ”

መቐለ 70 እንደርታ የእግድ ደብዳቤ ማስገባቱንም ይሁን የቀጣዩ ጨዋታ እጣ ፋንታ ይፋ ያላደረገው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በጉዳዩ ዙርያ ዝምታውን ይሰብራል ተብሎ ሲጠበቅ እንደ አቶ ልባርጋቸው ምሕረቱ አገላለፅ ግን ጨዋታው ለደጋፊዎች ክፍት የሚሆንበት ዕድል የሰፋ እንደሆነ ተናግረዋል ።

የመቐለ እና ደቡብ ፖሊስ የ28ኛ ሳምንት ጨዋታ ነገ 9:00 በመቐለ ይደረጋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡