ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ዛሬ 10:00 ላይ በቅሎ ቤት በሚገኘው የክለቡ ፅህፈት ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። በመግለጫው ላይ አቶ ነዋይ በየነ (ም/ሊቀመንበር)፣ አቶ ሰለሞን በቀለ (ስራ አስኪያጅ) እና አቶ ታፈሰ ሰለሞን (የቡድን መሪ) እንዲሁም የሚዲያ አካላት ተገኝተዋል።
ጋዜጣዊ መግለጫው በዋናነት ያተኮረው ቅዳሜ ባልተደረገው የ28ኛ ሳምንት እና ነገ ይደረጋል በተባለው የ29ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዙርያ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ከወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ጋር መካሄድ የነበረበት ጨዋታ አስመልክቶ የቡድን መሪው አቶ ታፈሰ “ጨዋታው መቅረቱን የሰማነው ከመገናኛ ብዙሀን ነው። በጨዋታ ቅድመ ስብሰባ ላይ የጨዋታው ኮሚሽነር ከፀጥታ ስጋት ጋር በተያያዘ ጨዋታውን ማድረግ እንደማይቻል በመግለፅ በዝግ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ መጫወት አልያም ጨዋታውን ወደ አዳማ ከተማ በመውሰድ እንዲካሄድ ቢገልፁልንም ይህን ለክለባችን ደጋፊዎች ሆነ ለክለባችን ክብር ሲባል እንደማንቀበል በመግለፅ ከስብሰባው ወጥተናል። ” ብለዋል። አቶ ሰለሞን በቀለ በበኩላቸው “የሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኮሎኔል ዐወል ትናንት ጠርተው ጨዋታውን እንድናደርግ እና የወልዋሎ ጨዋታን ወደ ፊት በሚገለፅ ቀን በተስተካካይ መርሐግብር ጨዋታው እንደሚደረግ ገልፀውል። የእኛ አቋም ጨዋታውን ለማድረግ እንደምንቸገር እና አስቀድመን ተስተካካይ ጨዋታውን ማድረግ እንደሚገባን በደብዳቤ ሆነ በቃል አስቀድመን አሳውቀን ወጥተናል።” ብለዋል።
አቶ ነዋይ በየነ በበኩላቸው ከወልዋሎ የሚደረገውን ጨዋታ ሳያከናውኑ ነገ የሚደረገውን ጨዋታ ማድረግ እንደማይችሉ አቋማቸውን ገልፀዋል። “በእግርኳሳዊ ሂሳብ ስሌት በዋንጫው ፉክክር ውስጥ እንገኛለን። ለውድድሩ ክብር መስጠት ይገባል። የፀጥታ ስጋት እንዳለ ይነግሩናል እንጂ የሚሰጡን ማረጋገጫ የለም። ስለሆነም ተስተካካይ ጨዋታውን መቼ እንደምናደርግ ሳይገለፁ ሰኔ 30 ውድድሩ እንደሚያልቅ እየገለፁልን ነው። በዚህም መሠረት እኛ አንጫወትም ሳይሆን እንጫወታለን ነው ጥያቄያችን። በተደጋጋሚም ጥያቄያችንን ለፌዴሬሽኑ በደብዳቤ ብናቀርብም ምላሹ ተገቢ ባለመሆኑ የክለባችን አቋም ተስተካካይ ጨዋታውን ሳንጫወት የምናደርገው ሌላ ጨዋታ አይኖርም ነው” ብለዋል።
በማስከተል ከጋዜጠኞች የተለያዮ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን ምላሽም ተሰጥቶባቸዋል።
በ29ኛው ሳምንት ፋሲል ከነማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ በነገው ዕለት ጎንደር ላይ እንዲካሄድ መርሐ ግብር ቢወጣም ቅዱስ ጊዮርጊስ የወሰደውን አቋም ተከትሎ ወደ ስፍራው እስካሁን እንዳላቀና ታውቋል።
በተያያዘ ዜና የሊግ ኮሚቴው ሁሉም ጨዋታዎች በተያዘላቸው መርሐ ግብር መሠረት እንደሚካሄዱ የገለፀ ሲሆን በጉዳዩ ዙርያ መቐለ 70 እንደርታ እና ሲዳማ ቡና ያቀረቡትን ቅሬታ እንደማይቀበል ገልጿል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡