ዛሬ የተደረጉ ጨዋታዎችን ተከትሎ ወደ ከፍተኛ ሊጉ የሚወርዱት ሁለት ቀሪ ክለቦች ታውቀዋል።
ዛሬ የተከናወኑት የ29ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የሊጉን ቻምፒዮን መለየት ባይችሉም በሌላኛው ፅንፍ በነበረው ፉክክር ደደቢትን ተከትለው ፕሪምየር ሊጉን የተሰናበቱ ሁለት ክለቦች ሊታወቁባቸው ችለዋል። ረፋድ አራት ሰዓት ላይ የመውረድ ስጋት ከነበረባቸው ክለቦች አንዱ የነበረው ስሑል ሽረ መቐለ ላይ ወልዋሎ ዓ/ዩን 2-1 ማሸነፉን ተከትሎ ከበታቹ የነበሩት መከላከያ እና ደቡብ ፖሊስ የመትረፍ ተስፋቸውን ለሠላሳኛው ሳምንት ለማሳደር ከዛሬ ጨዋታዎቻቸው ውጤት ይዘው የመውጣት ግዴታ ውስጥ ገብተው ነበር። ነገር ግን ዕኩል ዘጠኝ ሰዓት ላይ ባደረጓቸው ጨዋታዎች መከላከያ በመቐለ 70 እንደርታ 2-1 ሲሸነፍ ደቡብ ፖሊስ ደግሞ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር 1-1 በመለያየቱ ሁለቱም ክለቦች 29 ነጥብ ላይ በመቆም ከሽረ ጋር የነበራቸውን ልዩነት ማጥበብ ሳይችሉ ቀርተዋል።
በዚህም መሰረት በ1997 ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደገው አንጋፋው መከላከያ ከ14 የውድድር ዓመታት በኋላ፤ 2002 ላይ ከወረደ በኋላ ዘንድሮ ወደ ሊጉ ብቅ ማለት ችሎ የነበረው ደቡብ ፖሊስ ለከርሞው በሊጉ እንደማንመለከታቸው እርግጥ ሆኗል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡