ሲዳማ ቡና ደደቢትን 3-1በማሸነፍ ከመሪዎቹ ያለውን የአንድ ነጥብ ርቀት አስጠብቆ ወደ መጨረሻው ሳምንት አምርቷል።
በባለሜዳዎቹ ደደቢቶች ሙሉ ብልጫ የጀመረው ጨዋታው ጥቂት ሙከራዎች እና ሳቢ ያልሆነ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። ሙልጌታ ዓምዶም ከመሃል ሜዳ የተሻገረለት ኳስ ተጠቅሞ ባደረገው ለግብ የቀረበ ሙከራ ጥቃታቸው የጀመሩት ሰማያዊዎቹ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ከተጋጣምያቸው በተሻለ ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ነበራቸው። ከነዚህም መካከል አሌክሳንደር ዓወት ከፉሴይኒ የተላከለተን ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ሙከራ እና መድሃኔ ብርሃኔ ከርቀት መቶት ግብ ጠባቂው የተቆጣጠረው እንዲሁም አቤል እንዳለ ያደረገው ግሩም ሙከራ ተጠቃሽ ናቸው።
በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ አጀማመር ያልነበራቸው እና ዘግይተው ወደ ጨዋታው ቅኝት የገቡት ሲዳማዎች እንደ ተጋጣምያቸው በርካታ ዕድሎች ባይፈጥሩም ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ከማድረግ ግን አልቦዘኑም። አዲስ ግደይ ብቻው ከሐድሽ በርኸ ተገናኝቶ ያመከነው ኳስ እና ዮሴፍ ዮሃንስ ከርቀት መቶት ሐድሽ በርኸ ያዳነው ኳስም ይጠቀሳሉ። በሰላሳ ዘጠነኛው ደቂቃም ይገዙ ቦጋለ ግብ በማስቆጠር ቡድኑ እየመራ ወደ ዕረፍት እንዲያመራ አስችሏል።
የሲዳማዎች የበላይነት በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ግብ የታየው ገና ጨዋታድ እንደተጀመረ ነበር። ያብስራ ተስፋየ ፉሴይኒ ኑሁ በሳጥን እስጥ መጠለፉን ተከትሎ የተሰጠው ፍፁም ቅጣት ምት ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ግብ ካስቆጠሩ በኃላ ጥሩ መነቃቃት ያሳዩት ደደቢቶች ከግቡ በኃላም በአሌክሳደር ዓወት አማካኝነት መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። አጥቂው አቤል እንዳለ ያሻማለትን ኳስ በግንባር በመግጨት ነበር ሙከራው ያደረገው።
ሲዳማ ቡናዎችም በሐብታሙ ገዛኸኝ አማካኝነት ሁለት ጥሩ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገው ነበር። በተለይም አጥቂው አክርሮ መቶ ኃይሉ ገብረየሱስ ከግቡ መስመር በግንባር የመለሰው ኳስ ለግብ የቀረበ ነበር። በስልሳኛው ደቂቃም ይገዙ ቦጋለ ከአዲስ ግደይ የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑ በድጋሜ መሪ እንዲሆን አስችሏል።
በደደቢቶች በኩል ተቀይሮ የገባው ቢንያም ደበሳይ የተሻገረለትን ኳስ ጨርፎ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት አጋጣሚ እጅግ ለግብ የቀረበ ሲሆን
ከዚ ውጭ ሚካኤል ሃሲሳ አክርሮ መቶ አግዳዊ የመለሰበት አጋጣሚም ሌላ ጥሩ አጋጣሚ ነበር።
ሲዳማ ቡናዎች መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ግዜ አልቆ በተሰጠው ተጨማሪ ደቂቃ በአዲስ ግደይ እና ዳዊት ተፈራ ጥሩ ተግባቦት የተፈጠረው ጥሩ ዕድል በአዲስ ግደይ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው የጎል መጠናቸው ወደ ሦስት ከፍ በማድረግ ጨዋታውን 3-1 አሸንፈዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡