የአሰልጣኞች አሰተያየት | ደቡብ ፖሊስ 1-1 ኢትዮጵያ ቡና

ሀዋሳ ላይ ደቡብ ፖሊስ ከ ኢትዮጵያ ቡና 1-1 ከተለያዩበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥተዋል።

“ልናገረው ከምችለው በላይ አዝኛለሁ፤ ግን ይህ እግር ኳስ ነው” ገብረክርስቶስ ቢራራ (ደቡብ ፖሊስ)

በኳስ ቁጥጥር ወደ ጎል በመድረስ የተሻልን ነበርን የ፤ ግን ወደ ጎል መቀየር አቃተን። ወደ ጎል ባለመቀየራችን ደግሞ ይሄ ውጤት ተከስቷል። ሁሉም ነገር ገና ነው። የሽረው ጨዋታ ላይ የተከሰቱ ነገሮችን ሰምተናል። እሱ ጨዋታ በደንብ በምስል መታየት ይኖርበታል። ያ ነገር ውሳኔ የሚሰጥበት ይመስለኛል፡፡ የወረድንም ቢሆንም እስከመጨረሻው ጥሩ ለመጫወት እንሞክራለን፤ የቻልነውንም ጥረናል፡፡ ቡድኔ ጥሩ ነበር የተንቀሳቀሰው።

እንግዲህ የሽረ ጨዋታ ጠዋት መደረጉ አግባብ አይደለም። ፌዴሬሽኑ በተመሳሳይ ሰዓት ይደረጋል ብሎ ግን ሳይደረግ ቀረ። ተጫዋቾቼ ያን ውጤት ስለሰሙ ጫና ውስጥ ገብተው በርካታ አጋጣሚን አግኝተን ከመጎጎታቸው የተነሳ ማስቆጠር አልቻሉም።

የሊጉ መቆራረጥ ዋጋ አስከፍሎናል። አስራ አምስት እና ሀያ ቀን ቆይተህ ድጋሚ ወደ ጨዋታ መሄድ እንደ ቅድመ ውድድር ዝግጅት ነው የሚሆንብህ። እዚህ ደረጃ ላለ ቡደን ይሄ አስቸጋሪ ነው። ለሌሎቹ ራሳቸውን ቀድመው ላዳኑ ቡድኖች ምንም ችግር የለውም። እኛ ግን ውጥረት ነበረብን፡፡

ልናገረው ከምችለው በላይ አዝኛለሁ ግን እግር ኳስ ነው። ግን ይህ ክለብ በዚሁ አይነት የጨዋታ ሂደት ከቀጠለ በቀጣዩ ዓመት በድጋሚ ይመለሳል፡፡

“በሜዳቸው እንደመጫወታቸው የነሱ እንቅስቃሴ ጫና አሳድሮብናል ” ገዛኸኝ ከተማ (ኢትዮጵያ ቡና)

ስለጨዋታው

የጨዋታው እንቅስቃሴ ጥሩ ነው። ደቡብ ፖሊስ ከነበረበት ጫና አኳያ ከባድ እና ፈታኝ ነበር። በሜዳቸው እንደመጫወታቸው የነሱ እንቅስቃሴ ጫና አሳድሮብናል። ሆኖም ጥሩ ጨዋታ ነበር፡፡ ያው ደረጃ ይዞ ከመጨረስ ውጪ እኛ ጫና የለብንም ነበር። ጥሩ ግን ተጫውተናል ኳስ ለመያዝ ሞክረናል። ማስቀጠል ግን አልቻልንም ወጣ ገባ የሚል ነገር ነበረን፡፡ ”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡