ቅዱስ ጊዮርጊስ ከቡድኑ ውስጥ ከነበሩት አምስት የውጪ ዜጎች መካከል ከሦስቱ ጋር በስምምነት መለያየቱን አስታውቋል።
የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ ኢሱፉ ቦውራሀና ከክለቡ ከለቀቁት ተጫዋቾች አንዱ ነው። ቶጓዊው የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች በመጀመርያው ዙር በጥቂት ጨዋታዎች ላይ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ከመቀመጡ ውጪ በአንድም ጨዋታ ላይ ሳይሰለፍ የቀረ ሲሆን በሁለተኛው ዙር በተሻለ ሁኔታ በርከት ያሉ ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ አገልግሎት መስጠት ችሎ ነበር።
ሀምፍሬይ ሚዬኖ ሌላው ክለቡን የለቀቀ ተጫዋች ነው። ኬንያዊው አማካይ ከጎር ማሂያ ፈረሰኞቹን የተቀላቀለው በግማሽ የውድድር ዓመት ሲሆን እምብዛም ተፅዕኖ መፍጠር ሳይችል ቀርቷል።
ጋናው ሪቻርድ አርተር ሦስተኛው ተሰናባች ሆኗል። እንደ ሚዬኖ ሁሉ በውድድር ዓመቱ አጋማሽ ክለቡን የተቀላቀለው አርተር በአጥቂ ስፍራ ቀዳሚ ተመራጭ የነበረ ቢሆንም በሊጉ አንድም ጎል ማስቆጠር አልቻለም።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2011 የውድድር ዓመት በአጠቃላይ ካስፈረማቸው 7 የውጪ ዜጎች አሁን የቀሩት ፓትሪክ ማታሲ (ኬንያ/ግብ ጠባቂ) እና ኤድዊን ፍሪምፖንግ (ጋና/ተከላካይ) ብቻ ሲሆኑ ካሲሙ ታይሰን እና አሌክስ ኦቶርማል በውድድር ዓመቱ አጋማሽ መሰናበታቸው ይታወሳል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡