ትናንት ወደ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ መውረዳቸውን ያረጋገጡት ደቡብ ፖሊስ እና መከላከያ በሽረ እና ወልዋሎ ጨዋታ ዙሪያ ያላቸውን ቅሬታ በደብዳቤ ለፌዴሬሽኑ ገልፀዋል፡፡
ደቡብ ፖሊስ ትናንት በሜዳው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር 1-1 በመለያየቱ በመጣበት ዓመት ወደ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዳግም ተመልሷል፡፡ ክለቡ ወደ ከፍተኛ ሊጉ ቢመለስም ‘በዕኩል ሰአት መደረግ ሲገባው ፌዴሬሽኑ ያለ አግባብ የሽረን ጨዋታ ጠዋት 4:00 ላይ አከናውኗል፡፡ በጨዋታው ላይ የተሰሩ አስነዋሪ ጉዳዮችም አሉ።’ በሚል ሽረ ወልዋሎን 2-1 በረታበት ጨዋታ ላይ የነበረውን ክስተት በመጥቀስ ደብዳቤ እንዳስገባ የስፖርት ክለቡ ፕሬዝዳንት ኮማንደር ዳንኤል ገዛኸኝ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ ኮማንደሩ በደብዳቤው ላይ የሰፈረውን ሀሳብ ሲያስረዱ ‘ፌድሬሽኑ ስህተት ሰርቷል ፤ ከ28ኛው ሳምንት ጀምሮ ሁሉም ጨዋታዎች በዕኩል ሰዓት ይደረጋሉ ቢልም የሽረን ጨዋታ ብቻ ለይቶ አጫውቷል። በጨዋታው ላይም ወደ 70ኛው ደቂቃ ላይ ደጋፊዎች ሜዳ ውስጥ በመግባት እየመራ ከነበረው ወልዋሎ ውጤት በጉልበት ለመውሰድ በማስፈራራት አሸንፈው ወጥተዋል። ይህን ፌድሬሽኑ ባስቀረፀው ምስል መሠረት ተመልክቶ ውሳኔ ይስጠን’ የሚል ይዘት አለው ብለዋል፡፡
ሌላኛው ቅሬታውን ለፌዴሬሽኑ ያስገባው መከላከያ ነው። የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ ፕሬዝዳንት ኮሎኔል ደረጀ መንግስቱ በተመሳሳይ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ክለቡ ያስገባው ደብዳቤ ላይ የሰፈረውን ሀሳብ እንዲህ በማለት ገልፀውታል። “ትናንት የተደረገው የወልዋሎ እና ሽረ ጨዋታ አግባብ አይደለም። ጨዋታው በተመሳሳይ ጊዜ ይደረጋል ቢባልም ያ ባለመሆኑ እኛን ጎድቶናል ፤ ውድቀትም ሆኖናል። ውድቀታችን በዚህ ነው ባንልም ቅሬታን እናቅርብ ብለን እንጂ የተለየ ውሳኔ እንደማይኖር ጠንቅቀን እናውቃለን። ነገር ግን የተደረገው ነገር አግባብ አይደለም። 1ኛ ወልዋሎ እየመራ ባለበት ሰዓት ደጋፊዎች ወደ ሜዳ ገብተው ጨዋታው እንዲቋረጥ ሆኗል። 2ኛ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ጨዋታው 20 ደቂቃ ከቀረው ሰዓት ጀምሮ እስኪጠናቀቅ ክለቡን አልመራም ነበር፤ ይህ ጉዳይ መጣራት አለበት። 3ኛ ፌዴሬሽኑ ለህጉ ሲል ያስቀረፀውን ምስል በደንብ ተመልክቶ ፍትሀዊ ውሳኔ ሊሰጠን ይገባል።”
የክለቦቹን ቅሬታ ተከትሎ ፌዴሬሽኑ የሚሰጠውን ምላሽ በቀጣይ ይዘን የምንመለስ ይሆናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡