ወጣቶችን በማሳደግ የሚታወቁ የሊጉ ክለቦች አንዱ የሆነው አዳማ ከተማ ከተስፋ ቡድን ሁለት ተጫዋቾችን አሳድጓል፡፡
በምክትል አሰልጣኙ አስቻለው ኃይለሚካኤል ተመሳሳይ የውጤት ቀውስን ይዞ እስከ 29ኛ ሳምንት የሊጉ ጉዞ 35 ነጥቦችን ሰብስቦ ከወራጅ ቀጠናው ለጥቂት በማምለጥ በደረጃ ሰንጠረዡ 11ኛ ላይ ይገኛል፡፡ ዘንድሮ ክለቡ የተፈታተነውን ለተጫዋቾች ደሞዝ የመክፈል ችግርም በወጣት ተጫዋቾች ለመቅረፍ ያለመ ይመስላል።በዚህም ገና ከወዲሁ ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ ለቀጣዩ የውድድር ዘመን ሶሬሳ ሹቢሳ እና ታዬ ጋሻውን ማሳደጉን ሥራ አስኪያጁ አቶ አንበሴ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡
ዱሬሳ በዘንድሮው የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ ለአዳማ ከተማ በርካታ ግቦችን ሲያስቆጥር የነበረ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች ሲሆን ታዬ ጋሻው በተከላካይ ስፍራ ይጫወታል። አዳማ ከአራት ወራት በፊት በተመሳሳይ ከ20 ዓመት ቡድኑ ብሩክ ቦጋለ እና ዳግም ታረቀኝ የተባሉ ተጫዋቾችን ማሳደጉ ይታወሳል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡