‹‹ በሜዳችን የምናደርገውን ጨዋታ አሸንፈን ወደ አለም ዋንጫው አንድ እግራችንን እናስገባለን ›› አሰልጣኝ አስራት አባተ

 

የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ አስራት አባተ ዛሬ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ስለ ካሜሩን ቆይታቸው ፣ ቡድናቸው ስላገኘው ልምድ እና ስለ መልሱ ጨዋታ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ለእናንተ ለአንባብያን በሚመች መልኩም እንዲህ አቅርበነዋል፡-

 

የካሜሩን ቆይታቸው…

“በካሜሩን የነበረን ቆይታ ጥሩ ነበር፡፡ አጠቃላይ ወጪያችን በካሜሩኖች ሊሸፈን ቢገባውም በራሳችን ወጪ ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል አርፈናል፡፡

“ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር የተደረገበትና በተለይም ልምድ ለሌላቸው የኛ ተጫዋቾች ከባድ ነበር፡፡ በተለይም በመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች መረጋጋት አልቻልንም ነበር፡፡ ያም ቢሆን ቀስ በቀስ ጨዋታውን በመቆጣጠር 1-0 መምራት ችለን ነበር፡፡ በሁለተኛው ግማሽ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት በመጠቀምና በጨዋታው መገባደጃ አካባቢ ተጨማሪ ግብ በማስቆጠር አሸንፈውናል፡፡ ከግቦች በተጨማሪም በርካታ ሙከራዎች አድርገው ነበር፡፡ በአጠቃላይ ጨዋታው ጥሩ ነበር፡፡ ተጫዋቾቼም በጨዋታው እንቅስቃሴ ራሳቸውን ሲያሻሽሉ ነበር፡፡”

 

ልምድ እና ፈተናዎች…

“የመጀመርያ ኢንተርናሽናል ጨዋታ መሆኑ ነው አስቸጋሪ የሆነብን፡፡ በቡድናችን ያሉት አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች እንኳን በኢንተርናሽናል በሃገር ውስጥ ውድድሮች ያልተጫወቱ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ በክለብ ያልታቀፉ የአካዳሚ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ የጨዋታ ልምድ የሌላቸው መሆኑ በጣም አስቸጋሪ አድርጎብን ነበር፡፡ የዝግጅታችን ጊዜ አጭር መሆን እና በዝግጅት ወቅት ተጫዋቾች ወደ ክለቦች እንዲሄዱ መደረጉም ለጨዋታው ስናደርግ የነበረው ዝግጅት ላይ ተጽእኖ ፈጥሮብን ነበር፡፡”

 

ስለመልሱ ጨዋታ….

“ይህን እናደርጋለን ብለን ባንድ ጊዜ ማሰብ አንችልም፡፡ ያለንበት የእድሜ እርከን ነገሮችን ለማስተካከል ወሳኝነት አለው፡፡ ሆኖም አንድ ነገር በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ የምንጫወተው ሃገራችን ላይ ነው፡፡ ያለን እድልም ይህ 90 ደቂቃ ነው፡፡ ለማሸነፍ ከፍተኛ ስራ ይጠብቀናል፡፡ ከተጫዋቾቼ ጋርም ልናሸንፍበት የሚያስችለንን ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡

“ካሜሩን ጠንካራ ቡድን ነው፡፡ እንዲሁ በቀላሉ የሚሸነፍ ቡድን አይደለም፡፡ ነገር ግን በሜዳችን የምናደርገውን ጨዋታ አሸንፈን ወደ አለም ዋንጫው አንድ እግራችንን እናስገባለን፡፡ ”

 

የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ከ10 ቀን በኋላ ከጥር 15 ቀን 2008 ካሜሩን ጋር የመልስ ጨዋታውን የሚያደርግ ሲሆን አሸንፎ ወደ ተከታዩ ዙር የሚያልፍ ከሆነ የጅቡቲ እና ግብፅ አሸናፊን ይገጥማል፡፡ የአሰልጣኝ አስራት አባተ ቡድን ይህን ጨዋታ ካሸነፈ በሴፕቴምበር 2017 ጆርዳን ለምታስተናግደው የአለም ከ17 አመት በታች ሴቶች ዋንጫ ከሚያልፉ 3 የአፍሪካ ቡድኖች አንዱ ይሆናል፡፡

ያጋሩ