* ዓርብ በጀመረው የአፍሪካ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች የመጀመርያ ምሽት ሴኔጋል እና ቤኔን ወደ ቀጣይ ዙር ሲያሳልፉ ተጠባቂዋ ሞሮኮ እና ዩጋንዳን ከውድድር ውጭ ሆነዋል። የሞሮኮ እና የቤኒን ጨዋታ በተሰጠው መለያ ምት አሸናፊነቱ ወደ ቤኒን አምርቷል። አንጋፋው ስቴፈን ሲሲኞ ሀገሩ ታላቋን ሞሮኮ ስታሸንፍ ደምቆ ያመሸ ሲሆን የጨዋታው ኮከብም ተብሏል።
ሴኔጋል በሳድዮ ማኔ ብቸኛ ግብ ዩጋንዳን 1-0 አሸንፋ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍዋን አረጋግጣለች። ሳዲዮ ማኔ የሃገሩንን የማሸነፍያው ግብ በ15ኛው ደቂቃ አስቆጥሮ ፍፁም ቅጣት ምት ሲያመክንም የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተመርጧል።
* ሁለተኛው ቀን የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ቻምፒዮኗ ካሜሩን እና አዘጋጅዋ ግብፅ ከውድድር አሰናብቷል። በደጋፊዎቿ ፊት ዝቅተኛ ግምት የተሰጣት ደቡብ ኣፍሪካን አስተናግዳ ሽንፈት ያስተናገደችው ግብፅ ራስዋ ባዘጋጀች ድግስ በግዜ ለመሰናበት ተገዳለች፤ ለደቡብ አፍሪካ ብቸኛዋ የማሸነፍያ ግብ በ85ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ቴንቢንኮሲ ሎርች ነው። የጎሉ ባለቤት ሎርች የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጧል።
በሌላ ተጠባቂ ጨዋታ ናይጀርያ የወቅቱ ቻምፒዮኗ ካሜሩንን 3-2 በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍፃሜ ማለፏን አረጋግጣለች። ለናይጀርያ ኦድዮን ኤግሃሎ (2) እና አሌክስ ኢዎቢ ግቦቹ ሲያስቆጥሩ ለካሜሩን ክሊንቶን ንጄ እና ባሆከን አስቆጥረዋል። በውድድሩ ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው ኦዲዮን ኢግሀሎ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጧል።
* የአፍሪካ ዋንጫው የጥሎ ማለፍ ዙር ሦስተኛ ዕለት ዛሬ በሁለት ጨዋታዎች ሲቀጥል 1:00 ላይ ክስተቷ ማዳጋስካር ምድቧን በጥሩ ሦስተኝነት ያጠናቀቀችው ኮንጎን ትገጥማለች። 4:00 ላይ ደግሞ አልጄርያ ከ ጊኒ ይጫወታሉ።
* የብዙ ክለቦች ትኩረት የተነፈገው የሴካፋ ክለቦች ዋንጫ ትላንት በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሲጀምር ተጋባዡ ግሪን ኤግልስ እና ኤፒአር አሸንፈዋል። የዛምቢያው ተጋባዥ ቡድን ግሪን ኤግልስ የሱማሊያው ሄጋን 2-1 ሲያሸንፍ በሁለተኛው ጨዋታ የዩጋንዳው ፕሮላይን እና የሩዋንዳው ኤፒአር ያገናኘው ጨዋታ በኤፒአር አሸናፊነት ተጠናቋል። ውድድሩ ዛሬም ሲቀጥል የታንዛንያው አዛም እና የሩዋንዳው ሙኩራ በሁየ ስቴድየም ያገናኛል።
* ከሰርዮቪች ሚሉቲን “ሚቾ” የተረከቡትን ውጤታማ ቡድን በማስቀጠል ላለፉት ሁለት ዓመታት ከዩጋንዳ ጋር የቆዩት ሰባስቲያን ዴሳብር ከቡድኑ ጋር በጋራ ስምምነት መለያየታቸው ተገልጿል። ከዚህ በፊት በኢስማዒልያ ፣ ኤሴክ ሜሞሳ እና ዋይዳድ አትሌቲክን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ክለቦች በዋና አሰልጣኝነት የመሩት እኚህ ወጣት አሰልጣኝ በቅርብ ቀናት ስማቸው ከግብፅ ክለቦች ጋር እየተነሳ መቆየቱ ይታወሳል። በሌላ ዜና ሜክሲካዊ የግብፅ አሰልጣኝ ሃቭየር አግዌሬም ከሃላፊነታቸው ተነስተዋል።
* በቀጣይ ላለባቸው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች በዝግጅት የሚገኙት ደቡብ ሱዳኖች ካሜሩናዊ አሹ ኮፕሪፓን ባሶንግ በዋና አሰልጣኝነት ቀጥረዋል። የጀርመን እና ካሜሩን ጥምር ዜግነት ያላቸው እኚህ አሰልጣኝ ከፌደሬሽኑ ጋር የሁለት ዓመት ውል የተፈራረሙ ሲሆን ደቡብ ሱዳን በአህጉሪቱ እንደ ምሳሌ የሚጠቀስ እግር ኳስ እንዲኖራት እንደሚጥሩ ገልፀዋል። ብሄራዊ ቡድኑ ደቡብ ሱዳናዊው ጀምስ እዝቅኤልን በምክትል አሰልጣኝነት ቀጥሯል።
* የቤኒን ደጋፊዎች ከትልቁ ድል በኃላ በነበረው የደስታ አገላለፅ ጉዳት ደረሰባቸው። ከትላንት በስቲያ ሞሮኮን አሸንፈው ወደ ሩብ ፍፃሜ ያለፉት የቤኒን ደጋፊዎች ከድል በኋላ በኮተኑ ከተማ በነበራቸው ከመስመር ያለፈ የደስታ አገላለፅ አስራ ሶስት ሰዎች ላይ ከበድ ያለ ጉዳት ሲደርስ በአንድ ሰው ላይ የሞት አደጋ ደርሷል። ፍሪሶንስ የተባለ የቤኒን ሬድዬ ከድል በኃላ የነበረው የደስታ አገላለፅ እና የከተማው እንቅስቃሴ አደገኛ እንደነበር ገልፅዋል።