በኢትዮጵያ ፕሪምየር የ30ኛ ሳምንት የመጨረሻ ሳምንት ደደቢትን ያስተናገደው ሀዋሳ ከተማ 5-2 በመርታት ሦስተኛ ተከታታይ ድል አስመዝግቦ ዓመቱን ደምድሟል፡፡
ዛሬ ረፋድ 4:00 በተጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ክፍለ ጊዜ በፍጥነት በማጥቃት ተደጋጋሚ ተሳትፎ ሲያደርጉ የነበሩት ባለሜዳዎቹ ገና በጊዜ ግብ ሲያስቆጥሩ በነፃነት ሲጫወቱ የነበሩት ደደቢቶች የተከላካይ ክፍል ክፍት በመሆኑ ለመጋለጥ ችሏል፡፡ 6ኛው ደቂቃ ብሩክ በየነ በግራ አቅጣጫ የግል ክህሎቱን ተጠቅሞ የሰጠውን ኳስ ሄኖክ ድልቢ ከሳጥን ጫፍ ከርቀት አክርሮ መረብ ላይ አሳርፎ ሀዋሳን መሪ አድርጓል፡፡ ደደቢት ወደ አቻ ለመመለስ ብዙም ደቂቃ አልጠበቀም፤ 8ኛው ደቂቃ አቤል እንዳለ በረጅሙ አሻግሮለት ቢኒያም ደበሳይ የሀዋሳን የተከላካይ ክፍል መዘናጋት ተመልክቶ ለደደቢት አስቆጥሮ 1-1 መሆን ችለዋል፡፡
ጎል ካገቡ በኋላ ወደ መነቃቃት የገቡት ሰማያዊ ለባሾቹ አቤል እንዳለ መሪ ሊያደርጋቸው የሚችል እድልን ቢያገኙም ሶሆሆ ሜነሳ መልሶበታል፡፡ በሀዋሳዎች በኩል በግራ መስመር መልካም የሚባል እንቅስቃሴ የነበረው ፈጣኑ መስፍን ታፈሰ ያሻገረውን ኳስ እስራኤል ፊት ለፊት ከግብ ጋር ተገናኝቶ የግቡ አግዳሚ መልቦበታል፡፡ ከጥቂት አፍታ በኋላ ደግሞ 20ኛው ደቂቃ ላይ ፍቅረየሱስ መሀል ለመሀል በደደቢት ተከላካዮች አሾልኮ የሰጠውን መስፍን ታፈሰ አስቆጥሮ ሀዋሳን ዳግም መሪ አድርጓል።
በጎሎች ተንበሽብሾ የዋለው ጨዋታው ተጨማሪ ጎል ለማግኘት አልተቸገረም። ቶሎ ቶሎ ወደ ደደቢት የግብ ክልል ሲደርሱ የነበሩት ባለሜዳዎቹ ብሩክ በየነ ብቻውን ግብ አስቆጠረ ሲባል ተረባብርበው ኳሱን ካስጣሉት በኋላ በአቤል እንዳለ አማኝነት የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ የተፈጠረችውን ኳስ መሉጌታ አንዶም ከመረብ አሳርፏት ደደቢትን አቻ በማድረግ 2-2 መሆን ችለዋል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ 1 ደቂቃ ሲቀረው አቤል ከማዕዘን አሻምቶ ያብስራ በቄንጠኛ ሁኔታ መትቶ ለጥቂት ብረት ነክቶ የወጣችበት ኳስ ደደቢትን ወደ መሪነት የምታሸጋግር እድል ብትሆንም ሳይሳካ 2-2 እረፍት ወጥተዋል፡፡
በሁለተኛ አጋማሽ ደደቢቶች የሚያሳዩት እንቅስቃሴ ከተመልካቹ አድናቆት ያገኘ ቢሆንም በቀላሉ ረጃጅም ኳስ በሚጫወተው ሀዋሳ የሙከራ ብልጫ ተወስዶባቸዋል፡፡ 55ኛው ደቂቃ እስራኤል እሸቱ የሰጠውን ኳስ ብሩክ በየነ አስቆጥሮ የግብ መጠኑን ወደ ሦስት ከፍ አድርጎታል፡፡ 71ኛው ደቂቃም ዳንኤል ደርቤ እና ቸርነት አውሽ ባደረጉት ቅብብል ከቸርነት እግር ስር የደረሰውን ኳስ መስፍን ታፈሰ ለራሱ 2ኛ ለቡድኑ አራተኛ እንዲሁም ከተስፋ ቡድን ከሁለት ወር በፊት ካደገ በኋላ ለክለቡ ባደረገው አምስት ጨዋታ አምስተኛ ግብ አስቆጥሯል፡፡ 79ኛው ደቂቃ ከአስጨናቂ ሉቃስ የደረሰውን ኳስ ቸርነት አውሽ አስቆጥሮ መሪነታቸውን ወደ 5-2 ከፍ አድርጓል፡፡
ሀዋሳዎች 80ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ በየነ በመጎዳቱ ተጠባባቂ ወንበር ላይ የነበረው ሁለተኛ ግብ ጠባቂያቸውን አላዛር መርኔን ወደ ሜዳ በተጫዋችነት ያስገቡ ቢሆንም ተጫዋቹ በሜዳ ላይ የቆየው 7 ደቂቃ ብቻ ነበር። የደደቢቱን ዳዊት ወርቁ በተኛበት በመማታቱ የእለቱ ዳኛ አዳነ ወርቁ በቀጥታ ቀይ ካርድ አስወጥተውታል፡፡ ጨዋታውም በሀዋሳ 5-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ ነጥቡን 44 አድርሶ የውድድር ዘመኑን ሲያጠናቅቅ ደደቢት በ13 ነጥቦች እና 47 የግብ እዳ በፕሪምየር ሊጉ ከታዩ ደካማ ቡድኖች የሚመደብ ውጤት አስመዝግቦ ውድድሩን ቋጭቷል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡