የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 30ኛ ሳምንት ሲጠቃለል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2011 የውድድር ዘመን መደበኛ ጨዋታዎች ዛሬ ፍፃሜያቸውን ሲያገኙ መቐለ 70 እንደርታ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የሊጉ አሸናፊ መሆን ችሏል። የ30ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን በዚህ መልኩ አጠቃለን አቅርበንላችኋል።

መቐለ ላይ ድሬዳዋ ከተማን ያስተናገደው መቐለ 70 እንደርታ 2-1 በማሸነፍ ሊጉን በቀዳሚነት አጠናቋል። ኦሴይ ማዊሊ በ45ኛው፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል በ55ኛው ደቂቃዎች በፍፁም ቅጣት ምቶች የመቐለን ጎሎች ሲያስቆጥሩ ኤልያስ ማሞ የድሬን ብቸኛ ጎል በ78ኛው ደቂቃ ማስቆጠር ችሏል።

በድሉ በመታገዝ መቐለ 70 እንደርታ በ59 ነጥቦች የሊጉ ቻምፒዮን ሲሆን አማኑኤል ገብረሚካኤል በ18 ጎሎች የቡድኑ እና የሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ አጠናቋል። ድሬዳዋ በአንፃሩ በ35 ነጥቦች 12ኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ ናሚቢያዊው ኢታሙኑዋ ኬሙይኔ በ7 ጎሎች የቡድኑ ከፍተኛ ጎል አግቢ ሆኗል።

ሲዳማ ቡና በሜዳው ወልዋሎን ገጥሞ 3-0 ቢያሸንፍም በመቐለ ማሸነፍ ምክንያት ቻምፒዮን መሆን ሳይችል ቀርቷል። አዲስ ግደይ በ21ኛው ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ምት ቀዳሚውን ጎል ሲያስቆጥር በ70ኛው ደቂቃ አዲሱ ተስፋዬ ሁለተኛውን አክሏል። በ79ኛው ደቂቃ ደግሞ ዳዊት ተፈራ የማሳረጊያዋን ጎል ማስቆጠር ችሏል።

ሲዳማ ቡና ከመቐለ በአንድ ነጥብ አንሶ በ58 ነጥቦች ዓመቱን በሁለተኝነት ሲያጠናቅቅ አዲስ ግደይ እንደቡድኖቹ ሁሉ ከመቐለው አማኑኤል በአንድ ጎል አንሶ በ17 ጎሎች ሊጉን በሁለተኛ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት አጠናቋል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ወልዋሎ በ37 ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ሪችሞንድ አዶንጎ በ4 ጎሎች የቡድኑ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኗል።

ሊጉን እየመራ የመጨረሻውን ጨዋታ ሽረ ላይ ያደረገው ፋሲል ከነማ ከስሑል ሽረ ጋር 1-1 ተለያይቶ ውድድሩን በ3ኛነት አጠናቋል። ሙጂብ ቃሲም ገና በአራተኛው ደቂቃ ፋሲል ከነማን ቀዳሚ ሲያደርግ በ74ኛው ደቂቃ ሐብታሙ ሸዋለም ከፍፁም ቅጣት ምት ሽረን አቻ አድርጓል።

በውጤቱ መሠረት ፋሲል ከነማ በ57 ነጥቦች ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ ሙጂብ ቃሲም በ16 ጎሎች የሊጉ ሦስተኛ የቡድኑ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ አጠናቋል። ሽረ በ34 ነጥቦች 13ኛ ደረጃን ይዞ ሲያገባድድ በግማሽ ዓመት ቡድኑን የተቀላቀለው አይቮሪያዊው ሳሊፉ ፎፋና በ11 ጎሎች የቡድኑ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ መሆን ችሏል።

ጅማ ላይ ደቡብ ፖሊስን የገጠመው ጅማ አባ ጅፋር 3-2 አሸንፎ የውድድር ዓመቱን በድል ቋጭቷል። በ35ኛው ደቂቃ የተሻ ግዛው ባስቆጠረው ጎል ደቡበ ፖሊሶች መሪ በመሆን ወደ እረፍት ቢያመሩም ማማዱ ሲዲቤ በ61ኛው ደቂቃ ባለሜዳዎቹን አቻ አድርጓል። ተከላካዩ ተስፋዬ መላኩ በ85ኛው ደቂቃ ጅማን ወደ መሪነት ከፍ ሲያደርግ በ87ኛው ዘንድሮ በጅማ ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው ማሊያዊው ማማዱ ሲዴቤ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ 3ኛ ጎል አስቆጥሮ የጅማን መሪነት አስተማማኝ አድርጓል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጭማሪ ደቂቃ ሲቀሩት ኪዳኔ አሰፋ ለደቡብ ፖሊስ ብቸኛዋን ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በጅማ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በውጤቱ ጅማ አባ ጅፋር 46 ነጥቦችን ሰብስቦ በ5ኛ ደረጃ የውድድር ዘመኑን ሲያጠናቅቅ ማማዱ ሲዴቤ በ12 ጎሎች የቡድኑ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ አጠናቋል። ደቡብ ፖሊስ በአንፃሩ በ29 ነጥቦች 15ኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ ኄኖክ አየለ በ12 ጎሎች የቡድኑ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ ጨርሷል።

አዲስ አበባ ስታድየም ላይ አስቀድሞ መውረዱን ያረጋገጠው መከላከያ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያደረገውን ጨዋታ 4-3 ማሸነፍ ችሏል። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተሻሉ የነበሩት መከላከያዎች ፍቃዱ ዓለሙ ገና በአራተኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ግብ መምራት ቢጀምሩም በ21ኛው ደቂቃ አቡበከር ናስር በጥሩ ቅብብል የተገኘችውን ኳስ አስቆጥሮ ኢትዮጵያ ቡናን አቻ አድርጓል፤ በ30ኛው ደቂቃ ላይ አስራት ቱንጆ ወደ መሀል ያሻገራትን ኳስ የመከላከያው ተከላካይ ምንተስኖት ከበደ ቆርጦ በራሱ ግብ ላይ በማስቆጠር ቡናን መሪ ቢያደርግም ተመስገን ገ/ኪዳን ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ዳግም ሁለቱን ቡድኖች አቻ ማድረግ ቢችልም አማኑኤል ዮሐንስ ኢትዮጵያ ቡና መሪ ሆኖ ወደ መልበሻ ቤት እንዲያመሩ ያስቻለች ግብ አስቆጥሯል፡፡

ከእረፍት መልስ ጨዋታው እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ክፍትና በሁለቱም በኩል በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎች የተስተናገዱበት ነበር ፤ በዚሁም ተቀይሮ የገባው ሠመረ አረጋዊ በ72 እንዲሁም ፍቃዱ ዓለሙ በ75ኛ ደቂቃ ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች በመታገዝ መከላከያ 4-3 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ ቡና በ39 ነጥቦች 9ኛ ደረጃን ሲይዝ (የወልዋሎ ተስተካካይ ጨዋታ ውጤት ለውጥ ሊያስከትል ይችላል) አቡበከር ናስር በ11 ጎሎች የቡድኑ ከፍተኛ ጎል አግቢ በመሆን አጠናቋል። መከላከያ በአንፃሩ በ32 ነጥቦች 14ኛ ሆኖ ሲጨርስ ምንይሉ ወንድሙ በ11 ጎሎች የቡድኑ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ መሆን ችሏል።

ወደ አዳማ ያመራው ባህር ዳር ከተማ አዳማ ከተማን 3-0 አሸንፎ በጣፋጭ ድል ዓመቱን ቋጭቷል። የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሲል ዳንኤል ኃይሉ ከቅጣት ምት ባስቆጠረው ጎል የመጀመርያውን አጋማሽ በ1-0 መሪነት ያጠናቀቁት ባህር ዳሮች በሁለተኛው አጋማሽ 60ኛው ደቂቃ ላይ ጃኮ አራፋት፣ 85ኛው ደቂቃ ደግሞ ፍቃዱ ወርቁ ባስቆጠሯቸው ጎሎች አሸንፈው ወጥተዋል።

በድሉ በመታገዝ ባህር ዳሮች በ41 ነጥቦች 8ኛ ደረጃን ይዘው ሲያጠናቅቁ ፍቃዱ ወርቁ በ6 ጎሎች የቡድኑ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኗል። አዳማ ደግሞ በ31 ነጥቦች 11ኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ የመጨረሻ ጨዋታዎች በጉዳት ያመለጡት ዳዋ ሆቴሳ በ8 ጎሎች የቡድኑ ከፍተኛ ጎል አግቢ ሆኗል።

4:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ሊደረግ የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለመገኘቱ ድቻ በፎርፌ 3-0 አሸናፊ ሆኗል። በውድድር ዓመቱ ሦስተኛ ፎርፌ ያገኘው ወላይታ ድቻ በ41 ነጥቦች 7ኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ ባዬ ገዛኸኝ በ8 ጎሎች የቡድኑ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ አጠናቋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ46 ነጥቦች 4ኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ ገሚሱን የውድድር ዓመት በጉዳት ያልተጫወተው ሳላዲን ሰዒድ እና አቤል ያለው በጣምራ በ5 ጎሎች የቡድኑ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ መሆን ችለዋል።

በተመሳሳይ 4:00 ላይ ሀዋሳ ላይ ደደቢትን የገጠመው ሀዋሳ ከተማ 5-2 አሸንፏል። በመጀመርያው አጋማሽ ሀዋሳ ከተማ በኄኖክ ድልቢ እና መስፍን ታፈሰ ጎሎች ሁለት ጊዜ ቢመራም ደደቢት በቢንያም ደበሳይ እና ሙሉጌታ አምዶም ጎሎች አቻ ሆኖ ወደ እረፍት አምርተዋል። ከእረፍት መልስ አይለው የገቡት ሀዋሳዎች በመስፍን ታፈሰ ተጨማሪ ጎል እንዲሁም በብሩክ በየነ እና ቸርነት አውሽ ጎሎች 5-2 አሸንፈዋል።

ሀዋሳ ከተማ በድሉ ተጠቅሞ ነጥቡን 44 አድርሶ 6ኛ ደረጃን በመያዝ ሲያጠናቅቅ አማካዩ ታፈሰ ሰለሞን በ9 ጎሎች የቡድኑ ከፍተኛ ጎል አግቢ ሆኖ አጠናቋል። ደደቢት በአንፃሩ በ13 ነጥቦች ከሳምንታት በፊት ግርጌ ላይ ሆኖ መጨረሱን ሲያረጋግጥ በግማሽ ዓመት ቡድኑን የተቀላቀለው ኑሁ ፉሴይኒ በ4 ጎሎች የቡድኑ ከፍተኛ ጎል አግቢ ሆኖ አጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡