በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 30ኛው ሳምንት በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የነበረው ሲዳማ ቡና ወልዋሎን በመርታት ሊጉን በሁለተኝነት አጠናቋል፡፡
በመጨረሻው ሳምንት ቻምፒዮኑን ከሚለዩ ጨዋታዎች መካከል አስቀድሞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ወልዋሎን ዛሬ ያስተናገደው ሲዳማ ቡና የፋሲልን እና መቐለን ነጥብ መጣል እየተጠባበቀ ጨዋታውን ዛሬ አድርጓል፡፡ በክብር እንግድነት አቶ ታምሩ ሳሙኤል (የሲዳማ ዞን ም/አስተዳደር) እና ዘሪሁን ቀቀቦ (የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ስራ አስፈፃሚ እና የብሔራዊ ሜዲካል ኮሚቴ ሰብሳቢ) ከፌድሬሽኑ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ጨዋታውን አስጀምረውታል፡፡
ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ በመራው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች በረጅሙ ከመሀል ሜዳ ተጫዋቹ ግርማ በቀለ ተነስተው ለመስመር አጥቂዎቹ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና አዲስ ግደይ በሚደርሱ ኳሶች ከአጥቂው ይገዙ ቦጋለ ጋር በቅብብል ወደ ወልዋሎ ግብ በተደጋጋሚ መድረስ ችለዋል፡፡ ወልዋሎች በበኩላቸው የሚቆራረጡ ቅብብሎች የበዙበትና ወደ ሦስተኛው የሲዳማ የመከላከል ወረዳ ሲደርሱ ይነጠቁ ስለነበር ፍሬያማ ሊሆንላቸው አልቻለም፡፡ 10ኛው ደቂቃ አማካዩ አበባየሁ ዮሀንስ የመታትን እና አብዱላዚዝ ኬይታ በቀላሉ የያዘበት ኳስ የመጀመሪያዋ ሙከራ ሆናለች፡፡
21ኛው ደቂቃ የወልዋሎው ተከላካይ ደስታ ደሙ በራሱ የግብ ክልል ሳጥን ውስጥ አዲስ ግደይ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘችውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ አዲስ አስቆጥሮ ሲዳማን መሪ አድርጓል፡፡ ከግቧ በኃላ በመልሶ ማጥቃት የተጫወቱት ወልዋሎዎች 24ኛው ደቂቃ በደስታ ደሙ አማካኝነት ክፍት አጋጣሚ አግኝተው ተጫዋቹ ቢመታውም መሳይ አያኖ ያዳነበት ምናልባትም ወልዋሎዎች አቻ ሊያደርጋቸው የሚያስችል ሂደት ነበር፡፡ ለሲዳማ ልዩነት ፈጣሪ የሆነ እንቅስቃሴን ሲያደርግ የነበረው ሀብታሙ ገዛኸኝ በቀኝ መስመር ተደጋጋሚ ጥቃቶችን እና ጫናዎችን በተጋጣሚው ተከላካይ ሲያደርስ ተስተውሏል፡፡ 26ኛው ደቂቃ ላይም ከተጫዋቹ የተነሳውን ኳስ አበባየው ከርቀት መትቶ ለጥቂት የወጣችበት ተጨማሪ የሲዳማ ሙከራ ነበረች፡፡
ሁለተኛው አጋማሽ በጣለው ከባድ ዝናብ ታጅቦ የተደረገ ሲሆን ሜዳው ኳስን በዝናብ ምክንያት ያፈጥን ስለነበረ ከጥቂት ማራኪ ቅብብሎች ውጪ እንደመጀመሪያው አጋማሽ የተረጋጋ እንቅስቃሴን መመልከት አልቻልንም፡፡ በእንቅስቃሴ ተመጣጣኝ ቢመስልም አሁንም ወደ ግብ በመድረሱ የተሻሉት ሲዳማዎች ናቸው፡፡ በተለይ አማካዩ አበባየሁ ከርቀት የሚመታቸው ኳሶች ለግብ ጠባቂዎቹ ፈታኝ የነበሩ ሲሆን አብዛኞቹ ኢላማቸውን ያልጠበቁ በመሆናቸው በቀላሉ ሲወጡ ነበር፡፡ ሀብታሙ ገዛኸኝ ፋታ የለሽ ፈጣን እንቅስቃሴን በማድረስ ለቡድን ጓደኛው አዲስ ግደይ ማድረስ ቢችልም አዲስ ግደይ ሊጠቀማቸው ግን አልቻለም፡፡
70ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ገዛኸኝ ባደረገው ድንቅ እንቅስቃሴ በግራ በኩል ወደ ግብ ያሻገራትን አዲስ ግደይ ለማግባት ሲሞክር አምልጣው ከጀርባው የነበረው ተቀይሮ የገባው አዲሱ ተስፋዬ አስቆጥሯት የሲዳማን ግብ ከፍ አድርጓል፡፡ 79ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ገዛኸኝ ሰጥቶት ዳዊት ተፈራ ከሳጥን ውጪ ግሩም ግብ ከመረብ አሳርፎ ሲዳማ ቡና 3-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል ፡፡ ሲዳማ ቡናም ፋሲል ከነማ ከሽረ ጋር 1-1 በመለያየቱ ከቻምፒዮኑ መቐለ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ 58 ነጥብን በመያዝ በሁለተኝነት አጠናቋል፡፡
በስተመጨረሻም የእለቱ የክብር እንግዳ አቶ ታምሩ ሳሙኤል እና ዘሪሁን ቀቀቦ ከሌሎች እንግዶች ጋር በመሆን ሁለተኛ ለወጣው ሲዳማ ቡና የብር ሜዳሊያን ከሰጡ በኃላ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡