ሪፖርት | መቐለ 70 እንደርታ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ አነሳ

መቐለ 70 እንደርታ በአማኑኤል ገብረሚካኤል እና ኦሴይ ማውሊ ግቦች ታግዞ ድሬዳዋ ከተማን በማሸነፍ የሊጉን ዋንጫ ለመጀመርያ ጊዜ አንስቷል።

በፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ኮሎኔል ዐወል አብዱራሂም እና ሌሎች የፌደሬሽኑ የበላይ ኃላፊዎች አማካኝነት የተጀመረው ጨዋታው ከወትሮው በተለየ አስደናቂ ድባብ እና የደጋፊዎች ድጋፍ ነበር የጀመረው። በጥሩ ፍጥነት እና በጥሩ ጨዋታ ፍሰት በታጀበው ጨዋታ ሙከራ በማድረግ ቀዳሚ የነበሩት እንግዶቹ ድሬዎች ሲሆኑ ግብ ለማግኘትም ተቃርበው ነበር፤ ሙከራው በኤርምያስ ኃይሉ አማካኝነት የተደረገ ሲሆን አጥቂው ከመስመር ይዞ ገብቶ ቢመታም ሶፈንያስ ሰይፈ አድኖታል።

በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች የድሬዳዋ ከተማ ፈጣን የማጥቃት አጨዋወት ከመመከት አልፈው ለማጥቃት ያልደፈሩት መቐለዎች ከሰባተኛው ደቂቃ ገደማ በኃላ በነበረው የጨዋታ ክፍለ ግዜ ሙሉ ብልጫ ወስደው መጫወት ችለዋል። በሁለቱም አጥቂዎች መሰረት ያደረገ አጨዋወት የተከተሉት ባለሜዳዎቹ በአጋማሹ በርካታ ሙከራዎች ማድረግ ቢችሉም ሁሉም በሳምሶን አሰፋ እጅግ ድንቅ ብቃት ጎል ከመሆን ተርፈዋል። ከነዚህም አማኑኤል ገ/ሚካኤል በረጅሙ የተላከለት ኳስ ወደ ግብነት ከመቀየሩ በፊት ሳምሶን አሰፋ ደርሶ በድንቅ ብቃት ያዳነው ፣ ማውሊ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር መቶ በድጋሜ ሳምሶን አሰፋ ያዳነው እና ያሬድ ብርሃኑ እና ክዌኩ አንዶህ አንድ ሁለት ተጫውተው ወደ ሳጥን ያሻገሩት ኳስ ማውሊ ከማግኘቱ በፊት ሳምሶን አሰፋ ወጥቶ ያዳነው ከታዩት ሙከራዎች እጅግ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

ከላይ ከተጠቀሱት ሙከራዎች ውጭም ባለሜዳዎቹ የተሻለ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም ሃይደር ሸረፋ አክርሮ መቶት ሳምሶን አሰፋ ተፍቶ ወደ ውጭ ያወጣው ሙከራ እና ሚካኤል ደስታ መቶት ገናናው ረጋሳ ጨርፎ ወደ ውጭ ያወጣው ሙከራ ምዓም አናብስትን መሪ ለማድረግ የተቃረቡ ነበሩ። አርባ አምስቱ ደቂቃዎች አልቀው በተሰጡ ጭማሪ ደቂቃዎችም ባለሜዳዎቹ መቐለዎች የተሰጣቸው ፍፁም ቅጣት ምት ተጠቅመው በኦሴይ ማውሊ አማካኝነት ግብ በማስቆጠር መሪ መሆን ችለዋል።

በጣት የሚቆጠሩ ሙከራዎች የታዩበት እና በልብ አንጠልጣይ ሁነቶች ታጅቦ የተካሄደው ሁለተኛው አጋማሽ ምንም እንኳ እንደ መጀመርያው አጋማሽ በርካታ ሙከራዎች ባያስመለክትም ጥሩ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። አማረ በቀለ ከርቀት ባደረገው ሙከራ የጀመረው ጨዋታው ረጃጅም ኳስ ምርጫቸው ባደረጉት ድሬዎች ብልጫ ነበር የጀመረው። ብርቱካናማዎቹም ጥቂት የማይባሉ መከራዎች አድርገዋል፤ ከነዚህም ሃብታሙ ውልዴ ያደረገው አደገኛ ሙከራ እና ገናናው ረጋሳ ያደረጋት ለግብ የቀረበች ሙከራ ይጠቀሳሉ።

በሃምሳ አራተኛው ደቂቃ መቐለዎች ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት በአማኑኤል ገብረሚካኤል አማካኝነት አስቆጥረው መሪነታቸው ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችለዋል። ከጎሉ በኃላ በርካታ ቅያሪዎች ያደረጉት ድሬዎችም ከስልሳኛው ደቂቃ በኃላ በተሻለ ጫና ፈጥረው በመጫወት በሰባ ዘጠነኛው ደቂቃም ማራኪ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ጎሏ በኤልያስ ማሞ የተቆጠረች ስትሆን አማካዩ የሶፈንያስ ሰይፈ ቦታ አያያዝ አይቶ ነበር ከርቀት ያስመዘገባት።

ሜዳ ውስጥ ከሚታየው እንቅስቃሴ ይልቅ የደጋፊዎች ልብ አንጠልጣይ ስሜት እና ልዩ የድጋፍ ስሜት ገኖ የታየበት የመጨረሻው አስር ደቂቃ በሙከራ የታጀበ አልነበረም። ውጤቱ በዚ መጠናቀቁ ተከትሎም በአዲስ መልክ በ2000 የተመሰረተውና በ2010 ወደ ሊጉ ያደገው መቐለ 70 እንደርታ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ቻምፒዮን ሆኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡