የአሰልጣኞች ገፅ | ካሣሁን ተካ [ክፍል ሁለት]

የሀገሪቱ ውጤታማ እና አንጋፋ አሰልጣኞችን የሥራ ህይወት፣ ተሞክሮ እና አስተሳሰብ በሚዳስሰው በዚህ ገፅ ተረኛ እንግዳችን ካሣሁን ተካ ናቸው። ከቀድሞው ተጫዋች እና አሰልጣኝ ጋር በክፍል አንድ ከስልጠና ህይወታቸው ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን አንስተን ቆይታ ማድረጋችን የሚታወስ ነው። በዛሬው የክፍል ሁለት መሰናዶ ደግሞ ቴክኒካዊ ጎኖችን እያነሳን ቆይታ እናደርጋለን። መልካም ቆይታ!


በ1996 ዓ.ም. ህዳር ወር <ዜና ስፖርት> በተሰኘ ጋዜጣ የ<እንግዳችን> አምድ ላይ በሰጠኸው ቃለ መጠይቅ ” ተጫዋቾቻችን ያለ Playing-System የመጡ በመሆናቸው አዳዲስ ነገር ስታቀርብላቸው ለመቀበል ይቸገራሉ፡፡” የሚል አስተያየት ሰንዝረህ ነበር፡፡ ምን ማለትህ ይሆን? ዘርዘር አድርገህ ብታብራራልን…

★ በሃገራችን በአብዛኛው ወደ እግርኳሱ ዓለም የምንመጣው ከመንደር ወይም ከትምህርት ቤት በመሆኑ ተጫዋቾቻችን ካደጉ በኋላ ተገቢና ምቹ የሆነ ስልጠና ለመስጠት አስቸጋሪ ነው፡፡ በዚያ ላይ ድሮ በተግባራዊ ልምምድ ላይ የተካኑ መምህራን አልነበሩንም፡፡ ዘመናዊውን አሰለጣጠን ለመከተል መሰረታዊ የሆኑትን ትምህርቶች ማወቅ አለብን፡፡ ለምሳሌ፦ አሜሪካኖች የ አላቸው፡፡ የዚህን ፕሮግራም የልምምድ መርኃግብር (Training Scheme) ይዘት ለውጠው (Grass Root Level) የሚል አንድ (Topic) ከፍተዋል፡፡  በዋናነት ‘ቡድን እንደምን ይገነባል?’ የሚለውን ወሳኝ ጥያቄ መስመር ሊያስይዙ ይሞክራሉ፡፡ ከታች ጀምረው 4-ለ-4፣ 5-ለ-5፣ 7-ለ-7፣ 9-ለ-9 ይሉና 11-ለ-11 ላይ ይደርሳሉ፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ በየእርከኑ ዘላቂ ቡድን እየተገነባ ይሄዳል፡፡ ስለዚህ ለተጫዋቾች በክለብ ደረጃ የቡድን ፎርሜሽን እና ታክቲካዊ ስራዎች ሲሰጡ ግርታ አይፈጠርም፡፡ ምክንያቱም ተጫዋቾቹ በቡድን ግንባታ አጠቃላይ ሒደት ውስጥ አልፈውበት አድገዋልና፡፡ በተጠናው ስርዓት አንድ የመሃል አማካይ ከሚወጣው ሚና ጋር ገና ከቡድን ግንባታ ጅምር አንስቶ ጥልቅ መስተጋብር ሲያበጅ ያድጋል፡፡ ተከላካዩና አጥቂውም እንዲሁ ኃላፊነታቸውን እየተላመዱ ይመጣሉ፡፡ በመከላከል አደረጃጀት (Defensive Organisation) ስር የተለያዩ ተከላካዮች የጎንዮሽ መስመራቸውን (Allignment of The Defence Line) በጥንቃቄ እያጤኑ እንዴት እንደሚከላከሉ ለማወቅ ቢፈልጉ ቀደም ብለው ስለተማሩት አይከብዳቸውም፡፡

እግርኳስ በግብር ይውጣ የሚካሄድ ጨዋታ አይደለም፤ ይልቁንም ከቀለም ትምህርት (Academy) ጋር የተገናኘ ነው፡፡ በአዕምሯዊ ንቃት ደካማ ሆኖ እግርኳስን በሚፈለገው ደረጃ መጫወት አዳጋች ይሆናል፡፡ (Football tactic is a Mathematics.) ታክቲክ እኮ በሒሳብ ትምህርት ንዑሳን አርዕስቶች ይታገዛል፡፡ በእያንዳንዱ የተጫዋቾች የሜዳ እንቅስቃሴ ውስጥ የተለያዩ ጎነ-ሶስት ምስሎችን (Triangles) እናያለን፡፡ የኳስ ቅብብሎቹ የሚከወኑት በምናባዊ መስመሮቹ (Imaginary-Lines) ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ‘ተጋጣሚ ቡድን እነዚህን መስመሮች በምን ዘዴ መቁረጥ አልያም ለሁለት መክፈል (Bisect ማድረግ) ይችላል? እንዴትስ ይተገብረዋል?’ ለሚለው ጥያቄ ገቢራዊ ምላሽ ለመስጠት ከላይ በገለጽኩት ቅደም ተከተል ያልሄድን በመሆኑ እኛ ጋር ያለውን ችግር  ለማስረዳት ፈልጌ ያነሳሁት ሐሳብ ነው፡፡

ከዓመታት በፊት ተጫዋቾች ከኳስ ውጪ ስለሚኖራቸው ሚና (Off-the ball Movement) እና ሌሎች ዘመናዊ የታክቲክ መርሆዎች አብዝተህ ትሰብክ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ ብዙም ያልተለመዱና የማይሰሙ ጉዳዮችን እንድትዳስስ ያስቻሉህን እነዚያን ግንዛቤዎች እንዴት አዳበርካቸው?

★ እኔ ብዙውን ጊዜ ለመሻሻል ስል የራሴን ጥረት አደርጋለሁ፡፡ ስልጠና ማለት እንዲሁ ዝም ብሎ ጥብቅ ህግጋት በያዘ መመሪያ (Doctrine) ተመስርቶ የሚካሄድ መሆን የለበትም፡፡ አንድ ባለሙያ ኮርሶችን ሲሰጥ (Conduct ሲያደርግ) በተለያዩ ሃሳቦች ዙሪያ የሚያቀርብልህ ጥቂት ናሙናዎችን (Samples) ነው፡፡ እነዚያን  ግብዓቶች አስፍተህ፣ ዘርዘር አድርገህ፣ የተለያዩ መጻህፍትን አገላብጠህና የራስህን ግኝቶች አካተህ የምታሰፋው አንተ ነህ፡፡ ስልጠና አንድ ቦታ ላይ የሚያበቃ ጉዳይ ሳይሆን በውስጡ በርካታ ሒደቶችን የሚያሳልፍ መስክ ነው፡፡ አውሮፓ ውስጥ በታክቲካዊ ሃሳቦች፣ በልምምድ ዓይነቶችና ይዘቶች ዙሪያ መጻህፍትን የሚጽፉ ሰዎች በየትኛውም ዘይቤ ያልታሰሩ ህጻናትን ያጤናሉ፡፡ እነዚያ ልጆች ማንም የማያስበውን ድርጊት በእንቅስቃሴያቸው ሲከውኑ ይታያሉ፡፡ ምክንያቱም ልጆቹ እንዳሻቸው ለመጫወት ነጻ ናቸው፡፡ ስለዚህ ጸሃፊዎቹ እነርሱ ጋር ካዩት ተነስተው ያውጣጡና መጽሃፍቱን ያዘጋጃሉ፡፡

በነገራችን ላይ ልምምዶችን ማንም ሰው ማዘጋጀት ይችላል፡፡ እኔ የሆነ ክለብ ሲጫወት ተመልክቼ ለቡድኑ የሚሆን ስልጠና ማዘጋጀት አያቅተኝም፡፡ ያ የሚሆነው ግን ነገሮችን በጥልቀት በማሰብና በማንበብ ነው፡፡ ያኔ ከኳስ ውጪ ስላለው የተጫዋቾች እንቅስቃሴ ስናገር ጎን ለጎን አሰልጣኞችን ቋንቋ በአግባቡ እንዲማሩ እመክር ነበር፡፡ እዚህ አዳዲስ ትምህርቶችን በአማርኛ መስጠት ቢቻልም ተደራሽነቱ ውስን ይሆናል፡፡ የውጪ ዜጎች ሲመጡ እንዴት ትናገራለህ? እንዴትስ ትጠይቃለህ? የመጣንበት መንገድ አስቸጋሪ ነው፡፡ በትርጁማን ስትማር ተርጓሚው የአስተማሪውን መልዕክት በአግባቡ ያስተላልፋል ወይ? አጠያያቂ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ቃል በቃል ሊሄድልህ አይችልም፡፡ አሰልጣኞቻችን ቋንቋ ቢያጠኑ መጻህፍትን ማንበብ ይችላሉ፤ በዚህ ዘመን ደግሞ Online ብዙ ነገሮችን የማግኘት እድል ይሰጣል፤ እኔ ሁሌም ‘ተማሩ!’ ባይ ነበርኩ፡፡ አብዛኞቹ አሁን እየቆጫቸው ‘ያኔ እንዲያ ስትለን…’ የሚሉ አሰልጣኞች አጋጥመውኛል፡፡ ቋንቋ እኮ ተራ ነገር ነው፤ ምንም Puzzle የለውም፤ Geometry ወይም Trigonometry አይደለም፡፡ ለምን ያን ያህል እንቸገርበታለን? ለምን እንደሆነ ባይገባኝም ትምህርት ቤትና ትምህርት እንፈራለን፡፡ ሁሌም፣ በየትም ስፍራ ትምህርት አለ፤ አሁን እኮ እኛ ስናወራ እየተማማርን ነን፡፡ አሰልጣኞቻችን ጠዋት ልምምድ ያሰራሉ፤ ቀሪውን ጊዜ ምንድን ነው የሚያደርጉት? አላውቅም፡፡ ከውጪ ተጋባዥ ኢንስትራክተሮች ሲመጡ ፌዴሬሽኑ ምርጫዎችን ለማካሄድ መስፈርቶችን አውጥቶ የቋንቋ ጉዳይ ሲነሳ ‘እኛ እንዳንማር ነው፤ ምቀኝነት ነው፤ እንዳናድግ ነው፤ …’ የሚሉ ቅሬታዎችን ማቅረብ የተለመደ ነው፡፡ ያኔ ለዘብተኛ ሆነህ ታስገባቸዋለህ፤ ከዚያ አንድ ቦታ ላይ ይቆማሉ፡፡ ይህ ዋናው ችግር ነበር፡፡ እኔ ያሉኝን ነገሮች በሙሉ በማንበብ ነው ያገኘሁት፡፡ ለማስተማር እንኳን ውጪ ሃገር ስሄድ ከእነርሱ ተምሬ እመጣለሁ፡፡ ጥያቄዎችን አነሳለሁ፤ ከምላሾቻቸው ብዙ ነገሮችን አገኛለሁ፡፡

“Economical Football”ስ ባንተ አረዳድ ምን ማለት ይሆን…

★ ይህን አጨዋወት ለመተግበር ተጫዋቾች በአንድ ንክኪ የሚደረጉ ቅብብሎችን ይሰለጥናሉ፡፡ ጨዋታ ንክኪ ሲበዛበት ያዳከማለል፡፡ የአጨዋወት  ዘዴዬ ከሆነ ማንም አይነካኝም፤ ኳሱን የሙጥኝ ስል ግን ራሴ ላይ ችግሮችን እጋብዛለሁ፡፡ አካላዊ ጉሽሚያና ጥልፊያም ይከሰታል፤ በተነካሁ ቁጥር እየዛልኩ እመጣለሁ፡፡ በቃ ድካምን ለማስወገድ . በአንድ ንክኪ የሚጫወቱ ልጆች ካሉኝ ተመልካችን የሚስብና ፍሰቱ ያማረ ጨዋታ እተገብራለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ይህ የጨዋታ መንገድ (Economical Football) በተለያዩ የሜዳ ክፍሎች ላይ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾችን በቁጥር በልጦ ለመገኘት(Out Number ለማድረግ) ያስችላል፡፡

በአንድ ወቅት ‘በእኛ ሃገር እግርኳስ፥ ኳሱ ወደ ካታንጋ ከሄደ ሁሉም አማካዮች ወደዚያው፥ ወደ ጥላፎቅም ከሆነ እንዲሁ ወደዚያው አቅጣጫ ይተማሉ፡፡’ ብለህ ነበር፡፡ በኛ ሀገር ሁሉም ተጫዋቾች በአንድ ጊዜ ኳሱን ሊይዙ እንደማይችሉ እያወቁ ያንን ለምን ያደርጋሉ?

★ ተጫዋቾቻችን ስለ Playing-Pattern ማወቅ አለባቸው፡፡ አንተ በተመደብክበት ቦታ (Position) እና በተሰጠህ ሚና (Role) ልትጫወት ትችላለህ፤ ጓደኛህ ደግሞ ያንተን የሜዳ ላይ ኃላፊነት ሊረዳ ይገባል፡፡ ሁሉም ተጫዋች ከጎኑ ያለውን የቡድን አጋር እያስተዋለ መጫወት ይኖርበታል፡፡ ሁሌም ጨዋታ ሲጀምር የተከላካይ ክፍል ተጫዋቾች  በአንድ መስመር (Line) ላይ ሆነው ይታያሉ፤ በሒደት የደጋን ቅርጽ (Curve) መስራት ይጀምራሉ፤ በእንቅስቃሴ ሁለቱ የመሃል ተከላካዮች ለመስመር ተከላካዮቹ ሽፋን ይሰጣሉ፤ ሁለቱ የተከላካይ አማካዮች ደግሞ ወደኋላ ተስበው ይጫወታሉ፤ … የማይቆመው እንቅስቃሴ ፍሰቱን ይቀጥላል፡፡ (The Pattern continues) በዘመናዊ እግርኳስ ከፍተኛ የቦታ ክፍተት እና የጊዜ እጥረት አለ፡፡ (In modern football space and time are the big scarcity የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡) በአሁኑ ወቅት ሜዳ ላይ ክፍተቶችን ማግኘት እጅግ አዳጋች ሆኗል፡፡ አስተውላችሁ ከሆነ ተጫዋቾች በሜዳው ስፋት (Width) ኳስ ለመቀበል ሲሄዱ ከድንበሩ ሁሉ ይወጣሉ፡፡ ከዚህ የሜዳ አጠቃቀም የግል ችሎታን እንረዳለን፡፡ እኛ ጋር ኳስ ይሄዳል፤ እኛም በመንጋ አብረን እንነዳለን፤ ለምን? ሁሉም ተጫዋች እኮ የየራሱ ድርሻ አለው፡፡ ለዚህ’ኮ ነው ጨዋታችን መልክ የማይኖረው፡፡

የችግሩ መሰረታዊ ምክንያት ምንድን ነው?

★ ስልጠናው (Coaching) ነዋ! ታክቲካዊ ልምምዶችን ስታሰራ “ያንተ ኃላፊነት (Duty) ይሄ ነው፡፡ እገሌ ኳስ ሲይዝ በዚህ መልኩ ትንቀሳቀሳለህ፤ እሱ ሳይኖር እዚህ ትመጣለህ፤ ከኋላ እገሌ ላንተ ከለላ ይሰጥሃል…ወዘተረፈ፡፡ ” እያንዳንዷን ጥቃቅን መሳይ ጉዳዮች በዝርዝር ማስረዳት አለብህ፡፡ ለእኔ  እዚህ ሃገር ፍጹም ስህተት የሆነ አንድ ስያሜ አለ፡፡ <ተመላላሽ ተጫዋች>! ይህ መጠሪያ መዓት ተጫዋቾችን አጥፍቷል፡፡ እኔ በሜዳው ቁመት መቶ ሜትሩን ዝም ብዬ እየሮጥሁ የምመላለስ ከሆነ ተጨማሪ ልምምድ መስራት ሊኖርብኝ ነው? እንዴ አካል’ኮ ይዝላል፡፡ ለምን Exhaustion ውስጥ እገባለሁ? የመስመር ተከላካዩ ወደፊት ሮጦ በሄደ ጊዜ አማካዩ አልያም ከጎኑ ያለው የመሃል ተከላካይ እርሱ እስኪመጣ ቦታውን ተክቶ ቢጫወት መልካም ይሆናል፡፡ የመስመር ተከላካዩ የኮሪደሩ ተጫዋች ስለሆነ ብቻ ያለ ሌሎች የቡድን አጋሮቹ እገዛ እነዚያን ሁሉ ሜትሮች እየከነፈ እንዲውል መፍቀድ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ስህተቱ ከስያሜው (Terminology) ይጀምራል፤ ለብዙ ተጫዋቾች መክሰምም መንስኤ ሆኗል፡፡ ሃኪሞች የራሳቸው የሆነ የ ቋንቋ እንዳላቸው ሁሉ እግርኳስ የራሱ ቋንቋ አለው፡፡ <ተመላላሽ> የሚለው ስም ከየት እንደመጣ አላውቅም፡፡ ለምሳሌ “Defensive Midfielders” ሲል የሚናው ባለቤቶች “በዋናነት ይከላከላሉ፤ በመሃለኛው ክፍልም የአማካይነት ድርሻቸውን ይወጣሉ፡፡ ወደኋላ ሲያፈገፍጉ ተከላካይ ክፍሉን ያግዛሉ፤ ወደ መደበኛ ቦታቸው ሲመለሱ ደግሞ በተለምዷዊ ተግባራቸው ይቀጥላሉ፡፡” ማለት ነው፡፡ እነዚህን መሰረታዊ ሚናዎች ለተጫዋቾቻችን ማስተማር ያስፈልጋል፡፡

እንደሚታወቀው የቅብብሎች የተመጠነ (Precise) እና ለታሰበለት ተጫዋች በተሳካ ሁኔታ የሚደርስ (Accurate) መሆን ከተጠና እንቅስቃሴ ጋር ይያያዛል፡፡ በእግርኳሳችን ልኬታቸውን የጠበቁ ቅብብሎች የማይታዩት በስልጠናው ምክንያት ነው? ወይስ ከተጫዋቾቹ የግል ብቃት ጋር ግንኙነት አለው?

★ ሁሌም እንደ አሰልጣኝ እቅድ ታወጣለህ፡፡ ለምሳሌ እኔ አጫጭር ቅብብሎች ላይ የተመረኮዘ፣ ኃይልና ጉልበትን የሚቆጥብ እንዲሁም በአብዛኞቹ የሜዳ ክፍሎች ተቃራኒ ቡድን ላይ የቁጥር ብልጫ የሚያስገኝ ጨዋታ እየተገበርኩ ለመጫወት ካሰብኩ ለተጫዋቾቼ የምፈጥረው የልምምድ መርኃግብር የምፈልገውን ሊያስገኘኝ የሚችል መሆን ይኖርበታል፡፡ ይሄን በቃል ሳይሆን በተግባር ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ “አንድ ተጫዋች በአንድ የልምምድ ፕሮግራም (Training Session) 1500 ጊዜ ከኳሱ ጋር ንክኪ ማድረግ ይኖርበታል፡፡” ይላል የስልጠናው መርህ፡፡ ይህንን እንዴት አድርገህ ታሳካዋለህ? ቡድንህን 11-ለ-11 ከፋፍለህ ብታጫውት አንዱ ተጫዋች ኳስ ስንት ጊዜ ይደርሰዋል? በደንብ ማሰብን ይጠይቃል፡፡ በትንሽ የሜዳ ክፍል ላይ የሚሰሩና መጠነኛ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት የታክቲክ ግንዛቤ መፍጠሪያ ጨዋታዎች (Minor Tactical Games) አሉ፡፡ በእነዚህ ዘዴዎች ሃያ ሁለቱን ተጫዋቾች አካተህ ማሰራት የምትችልባቸው የስልጠና መንገዶች ይገኛሉ፡፡ ከኳስ ጋር ብዙ ንክኪዎች በፈጠርክ ቁጥር ከቀላሉ ወደ ከባዱ ስራ መሄድ ትችላለህ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ሜዳ ገብተህ ስትጫወት ቅብብሎችን በቀላሉ የተሳኩ ታደርጋለህ፤ ኳስ እንዳገኘህ ለመልቀቅ አትሸበርም፡፡ ምቾት እየተሰማህ ለጓደኛህ ታቀብላለህ፡፡ ኳሱ እግርህ ስር እያለ ሁሉም ይንቀሳቀሳል፤ ቅብብል የምትፈጽምባቸው አማራጮች ስለሚሰፉም እየሰጠህ ትሄዳለህ፤ ትቀበላለህ፤ ትሰጣለህ…. በቃ ይህ የምትሰጠው ልምምድ ውጤት ነው፡፡ እንደ አሰልጣኝ ልምምዶችን የመፍጠርና የማሻሻል ብቃት ከሌለህ የምታፈራው ያልበቃ ተጫዋች ነው፡፡ ሁለቴ ይቀባበልና ከዚያ ሲጠልዝ ታየዋለህ፡፡ ስለዚህ አሰልጣኞች ይህን እውቀት ሊያዳብሩ ይገባል፡፡

አሰልጣኞቹ የሚሰጡት ስልጠና ቀድመው ከተማሩት የአጨዋወት ስርዓት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ይኖረው ይሆን?

★ ይህን ለመበየን የልምምዱን መዋቅር ማየት ይኖርብናል፡፡ ለምሳሌ “በዚህ ዓመት 4-3-3 ፎርሜሽንን እጠቀማለሁ፡፡” ብለህ ከተነሳህ ቀድመህ ለመረጥከው ሲስተም የሚሆኑ ተጫዋቾችን ትመርጥና በእቅድህ ውስጥ ታስገባለህ፡፡ እንበልና ጥሩ የግራ እግር ተጫዋች ካለህ በግራው መስመር ተካላካይ፣ አማካይ አልያም የመስመር አጥቂ ሆኖ እንዲጫወት ልታዘጋጀው ትችላለህ፡፡ በመሃለኛው የሜዳ ክፍልም የተለያየ አጨዋወት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች መያዝ የግድ ይልሃል፡፡ ጉልበተኛና ፈጣን፣ የፈጠራ ክህሎቱ ላቅ ያለ፣ የጨዋታውን ሒደት በአግባቡ የሚያነብ ተጫዋች ያስፈልግሃል፡፡ ታዲያ እነዚህን ግብዓቶች እንዴት ታሟላለህ? ኃላፊነቱ የአሰልጣኙ ይሆናል፡፡

እንደሚታወቀው በአውሮፓ የተጫዋቾች ዝውውር ወቅት አንድ አሰልጣኝ ተጫዋች ሲገዛ “ክፍተት አለብኝ፡፡” ብሎ ለሚያስብበት ቦታ እንጂ ዝም ብሎ ገበያ ላይ ስለዋለ ወይም ርካሽ ስለሆነ አይደለም፡፡ ተጫዋቾቹ በጣም ውድ ቢሆኑ እንኳ ስለሚፈልጓቸው እና ስለሚያስፈልጓቸው ያዛውሯቸዋል፡፡ እኛ ሃገር ግን አሰልጣኞች በመጀመሪያ ተጫዋቾች ይመርጣሉ፤ ሰብስበው ልምምድ ያሰሯቸዋል፤ ከዚያ ወደ ሲስተም ይሄዳሉ፡፡ ይህ ስህተት ነው፡፡ በመጀመሪያ ተጫዋቾቹ የሚመረጡበት መስፈርት ይቀመጣል፡፡ የመሃል አማካይ ስመርጥ ቁመቱን፣ በግንባር የመግጨት አቅሙን፣ እንከን አልባ ቅብብሎች የማሰራጨት ብቃቱን፣ ለተከላካዩ ክፍል ከለላ የመስጠት ችሎታውን፣ ወደፊት እየሄደ የማጥቃት ሒደቱን ለማገዝ ያለውን ፍላጎት፣…    በማየት ምርጫዬን አከናውናለሁ፡፡ የመሃል አጥቂው የያዛቸው ክህሎቶችስ ምን ምን ናቸው? ያለ ኳስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ፣ ወደ አማካዮቹ ተጠግቶ የማጥቃት ፍሰቱን የማስቀጠል ተነሳሽነቱ፣ ግብ አነፍናፊነቱ፣… ሌሎችንም በዝርዝር አስቀምጦ ውሳኔ ላይ ይደረሳል፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ልምምዱ ዓይነት ትገባለህ፡፡ እኛ ጋር ግን የቅደም ተከተል ችግር ይስተዋላል፡፡

ከፎርሜሽኖች ጋር በተያያዘ 1982 ዓ.ም አካባቢ “3-5-2 ፎርሜሽንን በኢትዮጽያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተለየ መልክ የተገበርኩት እኔ ነኝ፡፡” ብለሃል? ከዚያ ቀደም ይህ የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር ጥቅም ላይ አልዋለም ነበርን? አንጋፋዎቹን የሃገራችን እግርኳስ ባለሙያዎችን ስናወራ በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ ጀርመናዊው የወቅቱ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ፒተር ሸንግተር 3-5-2ን እንደተጠቀመ ነግረውናል፡፡

★ እኔ እ.ኤ.አ.1990 ገደማ ወደ ምዕራብ ጀርመን ሄድኩ፡፡ በዚያን ጊዜ የጀርመን ብሄራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ነበር፡፡ ኼነፍ በሚባል የስልጠና ማዕከል (Training College) ውስጥ ለስድስት ሳምንታት ያህል ቆየሁ፡፡ ያኔ ብሄራዊ ቡድናቸው ደግሞ እኛ የነበርንበት ቦታ ላይ ለአንድ ሳምንት ያህል አርፎ ነበር፡፡ እናም እኛ በእነርሱ የልምምድ ሰዓት የሚያደርጉትን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ የመከታተል እድል አገኘን፡፡ እኛ የተቀመጥንበት ሆስቴል ውስጥ በመገኘታቸውም ተግባራዊ ስልጠናዎቻቸውን የመቃረም አጋጣሚው ተፈጠረልን፡፡ በዓለም እግርኳስ ሦስት የልምምድ ዓይነት መኖሩን ያወቅሁት እዚያ ነው፡፡ ጠዋት ከ12:00 ሰዓት በፊት ይነሳሉ፤ የዙር ሩጫ (Laps) ይሮጡና በየ15 ደቂቃው ይቆማሉ፡፡ አካላቸውን ያፍታታሉ፤ …. በተደጋጋሚ ይህን እንቅስቃሴ ያደርጉና ሲጨርሱ ወደ ቁርስ ይሄዳሉ፡፡ ከቁርስ በኋላ እረፍት ወስደው በድጋሚ ወደ 5:00 ሰዓት አካባቢ ይወጣሉ፡፡ የመስፈንጠር (Sprinting)፣ ብርታት የማሳደግ (Indurance)፣ አካላዊ ጥንካሬን የማጎልበት (Strength)፣ … ሌሎችንም ልምምዶች ያካሂዳሉ፡፡ ታዲያ ሁሉም ልምምዶቻቸው ላይ ኳሱ አብሮ ይኖራል፡፡ እሱ ነዋ የሚያነሳሳቸው! ተጫዋቹን ዝም ብለህ ‘ሩጥ!’ ብቻ ብትለው ይሰላቻል፡፡ ከኳስ ጋር ሲሆን ግን የተሻለ ይሰራሉ፡፡ በዚህ መልኩ ለሰባ ደቂቃ ብቻ  ይለማመዱና ወደ ሆቴላቸው ለምሳ ይገባሉ፡፡ የሚገርመው ምሳ ሲመገቡ ቢራ እንደ አምቦ ውሃ እንዲጠጡ ይፈቀድላቸዋል፤ ታዲያ ሁለት-ሁለት ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ረዘም ያለ እረፍት ይወስዳሉ፡፡ ወደ አመሻሽ በ11:00 ሰዓት ይወጡና ቴክኒካል ነገሮች ላይ የሚያዘነብሉ ስልጠናዎችን ይማራሉ፡፡ ተሻጋሪ ኳሶች (Crossing)፣ ቅብብሎች (Passing) ፣ በሜዳው ስፋት የመጫወትን ስልት (Width-Play) እና ታክቲካዊ ስራዎችን ይተገብራሉ፡፡ በዚህኛው የልምምድ መርኃግብራቸው ትልቅ አጽንኦት የሚቸሩት ለቅብብሎች ነው፡፡ በነገራችን ላይ ቅብብል በተጫዋቾች መካከል የሚኖር የመግባቢያ ድልድይ ነው ፡፡ (Passing is a means of communication.) አንድ ኢትዮጵያዊ ተጫዋች ደቡብ አሜሪካ ወይም ስፔን ቢሄድ ከዚያ ሃገር ተጫዋቾች ጋር ሜዳ ላይ የሚወዳጀው በቅብብል ነው፡፡ አቀብለኸው ስትሮጥ መልሶ ሊያቀብልህ ይፈልግሃል፤ Double Pass መሆኑ ገብቶታል ማለት ነው፡፡ ሁልጊዜም ለቅብብሎች ያላቸው ስሜት ይገርመኝ ነበር፡፡ በቃ ምን ልበልህ የተወሰነ ቦታ ያከቡና Pass, Pass, Pass…..Pass…

እነርሱን ከማየቴ በፊት ስልጠና የምሰጠው ሙሉ ሜዳ ላይ ነበር ፡፡ እዚህ ከመጣሁ በኋላ ግን ሁሉንም ነገሮች በሳጥኑ ውስጥ መጨረስ ጀመርኩ፡፡ እኔ ያሰለጠንኳቸው ልጆች ያውቃሉ፤ ‘ከኳስ ጋርና ያለ ኳስ እንዴት መጫወት ይቻላል?’ የሚለውን እንዲያጠኑ እታትር ስለነበር ስለ ኳስ ንክኪ (Ball Contact) እስኪሰለቻቸው ድረስ አሰርቼያቸዋለሁ፡፡ በኮሌጁ የነበሩት ጀርመናዊያን  ኢንስትራክተሮቻችን ደግሞ በብሄራዊ ቡድናቸው ዙሪያ ከእነርሱ የሚደበቅ ነገር አልነበረም፡፡ እርስ በእርሳቸው ጥሩ ወጃጅነት መስርተዋል፤ የቡድኑ አሰልጣኞች ሲመጡ በጋራ ሆነው ቡና ሲጠጡ አልያም ቢራ ሲጎነጩ እጅግ እንደሚከባበሩ እናያለን፡፡ አንድ አሰልጣኝ ለብሄራዊ ቡድኑ ሲመረጥ ከአጠቃላይ የሃገሪቱ ክፍል ድጋፍ ይደረግለታል፤ እንደ እኛ ሃገር ለብቻ ነጥሎህ ሲሰድብህ አይውልም፡፡ እናም በ3-5-2 ፎርሜሽን አተገባበር የተደነቅሁት የዚያኔ ነው፡፡

በእርግጥ ሆላንድ ባሸነፈችው የዩሮፒያን ሻምፒዮና ላይ  ራሺያን የመሳሰሉ ሃገራት ፎርሜሽኑን ይጠቀሙ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሲስተሙ በርካታ አተገባበሮች (Variable Methods) ነበሩት፡፡ ‘በ3-5-2 ሁለቱ የመስመር ተጫዋቾች ልክ እንደ መሃል አማካይ ሲንቀሳቀሱ ሶስቱ የመሃል ተከላካዮች ምን ዓይነት ሚና ይኖራቸዋል?’ የሚለው ጥያቄ ሲነሳ ብዙ ታክቲካዊ ምላሾች ይሰጣሉ፡፡ እኔ ያኔ ለየት ያለ አቀራረብ ያለውን የዚህ ፎርሜሽን አጠቃቀም ይዤ መጣሁና ካይሮ የጠፉ ተጫዋቾችን ያካተተው የወጣት ቡድን ላይ ሞከርኩት፡፡ ያ ቡድን  ለፖርቹጋሉ የአለም ወጣቶች ዋንጫ ማለፍ የሚችል አቅም ይዞ ነበር፡፡ በጣም የሚገርመው ለውድድሩ ለማለፍ ዛምቢያን ጨዋታው ሊጠናቀቅ አስር ደቂቃ እስኪቀረው ድረስ 2-0 መርተን ነበር፡፡ በጣም አስደናቂ ቡድንም ሰርተን አሳይተናል፡፡ ብዙዎቹ ተጫዋቾች የሚገርም ችሎታን ተክነዋል፤ ዮሃንስ የሚባል ኤርትራዊ ልጅ፣ ከመሃል ሜዳ ተነስቶ ጥሩ ጥሩ ግብ የሚያስቆጥረው ሰለሞን (አሁን አሜሪካ ይገኛል፡፡)፣ …. ሌሎቹም ነበሩ፡፡

“አንዳንድ ጊዜ እግርኳስ በምርጥ የተጫዋቾች ትውልድ ይታገዛል፡፡” የሚል አባባል አለ፡፡ እኔም ያ አጋጣሚ ሳይደርሰኝ አልቀረም፡፡ በእነዚያ ልጆች ብሄራዊ ቡድኑን ሁሉ አሸንፈናል፡፡ ስለ 3-5-2 ለተጫዋቾቹ ሳስተምር በደንምብ ይረዱኝ ነበር፡፡ እንዲያውም አንድ ጊዜ ናዝሬት (አሁን አዳማ) ከዋናው ብሄራዊ ቡድን ጋር ስንጫወት የተጋጣሚያችን አማካዮች 4-3-3ን ይዘው ስለገቡ በመሃል ሜዳው ላይ የተጫዋቾች ቀጥተኛ ፍልሚያ 5-ለ-3 እየሆነ የቁጥር ብልጫ ሲወሰድባቸው “ኧረ ትርፍ ናቸው! እንዴ ተቸገርን እኮ!” እያሉ ወደ አሰልጣኞቻቸው ሲጮሁ ትዝ ይለኛል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ብሄራዊ ቡድኖችና ክለቦች ዘመናዊውን 3-5-2 መጠቀም የቀጠሉት፡፡ ከዚያ ቀደም በኢትኮባ እያለሁ 4-4-2ን እመርጥ ነበር፡፡ ያ ቡድንም ይህን ፎርሜሽን ከማንም በተሻለ ተገብሯል፡፡ እኔ በምጠቀመው 4-4-2 ሲስተም ውስጥ ነጻ ሚና ተሰጥቶት እንደፈለገ ሜዳውን የሚያካልለው ተጫዋቼ (Floating Player) ክፍሌ ቦልተና ነበር፡፡ እርሱ ሁሌም በየትኛውም ቦታ ለቡድን አጋሮቹ የቁጥር ብልጫ እንዲወስዱ ይረዳቸዋል፡፡ የሚደንቅ ብርታት ነበረው፡፡ ዓለምሰገድ፣ ፔሌ፣ ታሪኩ መንጀታ…. እነዚህ ሁሉ የእኔ ልጆች ነበሩ፡፡ በነገራችን ላይ ታሪኩ መንጀታ በአንድ የውድድር ዓመት አርባ ጎሎችን ያገባው ዝም ብሎ አይደለም፤ ሲስተሙን በተለየ መንገድ ያለ እንከን ስለምንተገብር እንጂ፡፡ የኋላ መስመር ተጫዋቾች እንኳ ብዙ ግቦች ያስቆጥሩ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ልትማር ወደ ውጪ ስትሄድ ይዘህ ከምትመጣው እና ተግባር ላይ ከምታውለው ስርዓት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፡፡

ተጫዋቾቻችን የላቁ አሰልጣኞች ቢያገኙ እውነት የሚሰጣቸውን (Technical Assignment) እና (Tactical Task) የመቀበል ፍላጎትና ወደ ተግባር የመለወጥ አቅም አላቸውን? የሚባለውን ያህል ባለ ክህሎት ተጫዋቾችስ ሞልተውናል?

★ ቅዳሜና እሁድ በከተማችን መንደሮች ውስጥ  ዞር ዞር ስትሉ መሰረታዊ ክህሎቶችን የሚያሟሉ ተጫዋቾችን ማግኘት ከባድ አይሆንም፡፡ ድሪብል ሲያደርጉ፣ ጥሩ ቅብብሎችን ሲከውኑና አብዶዎችን ሲሰሩ አዎንታዊ ብቃት ታይባቸዋለህ፡፡ ነገርግን ይህ ሁሉ ችሎታ በሙያተኛ እየታገዘ የጎለበተ አይደለም፡፡ እነዚህ ልጆች ተገቢ ስልጠና እያገኙና በቀለም ትምህርት እየታገዙ ቢያድጉ ትልቅ ደረጃ ይደርሳሉ፡፡ በቅርቡ የአያክስን ቡድን አይተናል፡፡ ተጫዋቾቹ ኳስ ብቻ አይሰለጥኑም፤ የአካዳሚ ትምህርትም ይማራሉ፡፡ ቋንቋ፣ ጂኦግራፊ፣ የሒሳብ ትምህርት፣… ብዙ ነገሮችን ይወስዳሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች አዕምሯዊ አቅምህን ያሳድጋሉ፡፡ የ እውቀቱ ካለህ ለማጥቃት ወደ ፊት ስትሄድ አጭሩ መንገድ (The Shortest Line) ወይስ ቀጥተኛው የሜዳ ቁመት (Straight Line)? በተፈጥሮ ከሚዳብር ግንዛቤ (Common Sense) በመነሳት ውሳኔ መስጠት ይቻላል፡፡ ፈረንጆቹ (Soccer starts from head!) ይላሉ፡፡ሃሳቡ ከአዕምሮ ይጀምርና ወደ እግር ይወርዳል፡፡ ምንም እንኳ ተጫዋቾቻችን  በታክቲክ ግንዛቤ ብዙ ቢቀራቸውም እንደምንም ተጭነናቸው አንዳንድ ነገሮችን ልናሳያቸው እንችላለን፤ ይሁን እንጂ አካዳሚን እና ኳሱን አብረህ ስታስኬድ ነው የመግባባቱ መጠን የሚጨምረው፡፡ በዚህ ሁኔታ ቀላል የሆነውን ችግር ሊፈቱ የሚችሉበትን ዘዴ ራሳቸው እንዲፈጥሩ ማድረግ ይቻላል፡፡ እኛ ጋር ስርዓቱ አልተዘረጋም፤ ስለዚህ የምትፈልገውን ማሰራት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ችግሩ ሁለቱም ጋር (ተጫዋቾችም፥ አሰልጣኞችም) ጋር እንዳለ ይሰማኛል፡፡

ከዚህ በፊት በቴሌቪዥን የሰጠኸው ቃለመጠይቅ ላይ ” ወጥ የሆነ የስልጠና ሲስተም ባለመኖሩ ተጫዋቾች ከአንዱ አሰልጣኝ ወደ ሌላው ሲሄዱ ይደናገራሉ፡፡” የሚል ንግግር አድርገህ አድምጠናል፡፡ ብዙዎች በተደጋጋሚ የሚያነሱት ጥያቄ ይመስለናል፡፡ ይህ ሐሳብ ግርታ እና የአረዳድ ችግር የሚፈጥር በመሆኑ <ወጥ የሆነ የስልጠና ስርዓት> ምንድን ነው? ልንልህ ነው፡፡ 

★ ሰዎች በግልጽ መረዳት ያለባቸው ነገር ወጥ የሆነ የስልጠና ስርዓት ማለት አንድ ዓይነት የልምምድ መርኃግብር፣ ተመሳሳይ <ድሪል>፣ ተደጋጋሚ የታክቲክ ትግበራ ማለት እንዳልሆነ ነው፡፡ በእግርኳሳችን የሚታየው የልምምድ መዋቅር (Training Pattern) የተዘበራረቀ ነው፡፡ የተወሰነው ጠዋት ይሰራል፤ ሌላው ከሰዓት በኋላ ይለማመዳል፡፡ አንዳንዱ ከልምምድ ውጪ የሚያሳልፈው ጊዜ /እረፍቱ/ ይበዛል፡፡ በነገራችን ላይ ልምምድ መደበኛ የመሆን ባህሪ (Norm) ያስፈልገዋል፡፡ ተጫዋቾቹ’ኮ እግርኳስ የሙሉ ሰዓት ሙያቸው ነው፡፡ (They are Professionals!) ለምን በቀን ሶስቴ አይሰሩም? “ፈር የያዘ የስልጠና ፕሮግራም ይኑር፡!” ማለት “የልምምዱ ይዘቶች በሙሉ ተመሳሳይ ይሁኑ!” ማለትም አይደለም፡፡ የ ዓይነቶች በቡድንህ እንደሚገኙ ተጫዋቾች የአጨዋወት ባህሪ እና እንደ አሰልጣኙ ፍልስፍና ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ እኔ ጋር ያሉት ተጫዋቾች ይበልጡን ተፈጥሯዊ ክህሎታቸውን የማበልጸግ (Skill Development) ስራ የሚያስፈልጋቸው ከሆነ እዚህኛው ክፍተት ላይ አተኩራለሁ፡፡ ቅደም ተከተሉ ተጠብቆ በቀን ሦስት ጊዜ ልምምድ ማድረግ የግድ ሲያስፈልግ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ በሒደት ስልጠናው በተጫዋቾች ችሎታ ላይ ያመጣውን ለውጥ እያጤኑ ግምገማ ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ (Training Scheme) በእቅድ (Plan) አንድ አይነት መሆንን እንጂ በልምምዱ ዓይነት (Exercise Type) መመሳሰልን አይጠይቅም፡፡ ጆዜ ሞውሪንሆ እና ፔፕ ጓርዲዮላ የሚያሰሩት የልምምድ ይዘት ይለያያል፡፡ ነገርግን ሁለቱም የሚፈተኑባቸው (challenge) ሁኔታዎች አሉ፡፡ አውሮፓ ውስጥ በአካል ብቃት (Physical Fitness) ዙሪያ ወቀሳ የሚቀርብባቸው ተጫዋቾች አሉ እንዴ? እዚህ ግን በጣም ብዙ! በቅብብሎች ስኬታማነት የሚነቀፍስ? እዚያ የለም፡፡ እኛ ጋርስ? መዓት ነው፡፡ ለምን? ከዚያ ተነስተን ነው የስልጠናው መሰረታዊ እቅድ ወጥ ይሁን የምንለው፡፡ የስልጠና ልዩ ልዩ መሆን ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ አንድ አሰልጣኝ በቀን ሦስቴ የማሰራት ግዴታ ቢጣልበት ወደ ማንበብና መፍጠር ያመራል፡፡ ነገ ለተጫዋቾቹ ስለሚሰጠው  ትምህርት መጨነቅ ይጀምራል፡፡

የተለመደና አሰልቺ (Routine) አይሆንም ለማለት ነው?

★ በትክክል! ሁሌ እየመጣህ <ኮን> ተክለህ “ሩጥ!” ብትለኝ ስንቴ ነው ያንን የማደርግልህ? ጠዋት ይህን አሰርተኸኝ ከሰዓት ይህንኑ የምደግመው ከሆነ ለምን እመጣለሁ? አልመጣም፡፡ ስለዚህ እቅድህ በራሱ እንድትማርና እንድትጠይቅ ይገፋፋሃል፡፡ ይህን ለማለት ነው ወጥነትን የምንወተውተው፡፡

ይቀጥላል…

(በቀጣይ ሳምንት ስለ አሰልጣኞቻችን የሚያተኩረውን ክፍል ይዘን እንቀርባለን)