አስቀድሞ አዳማ ላይ በ08:00 እንዲደረግ መርሐ ግብር ወጥቶለት የነበረ ቢሆንም በድንገት ትናንት ማምሻውን በስልክ ጥሪ በተደረገ ለውጥ ወደ ቢሸፍቱ ተለውጦ ዛሬ 04:00 ተካሂዷል። ሀዋሳ ከተማም በመለያ ምቶች ወደ ግማሽ ፍፃሜው ተሸጋግሯል።
04:00 ላይ ይጀምራል ተብሎ የታሰበው ጨዋታ ለ30 ደቂቃ ያህል ሊዘገይ ችሏል። ምክንያቱ ደግሞ ሜዳውን ለጨዋታ ለማዘጋቸት ሲባል ምቹ ያልሆኑ የሜዳው ክፍሎችን ለማስተካከል በአካፋ እና በዶማ በመቆፈር የወሰደው ጊዜ ነበር።
እጅግ አሰልቺ እና ደካማ እንቅስቃሴ ተመልክተን በተጠናቀቀው በዚህ ጨዋታ ለጎል የቀረቡ ሙከራዎችን የተመለከትንባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት ነበሩ። በ2ኛው ደቂቃ በወላይታ ድቻ በኩል አብዱልሰመድ ዓሊ በጥሩ ሁኔታ ያቀበለውን ቸርነት ጉግሳ ከሀዋሳው ግብ ጠባቂ ሶሆሆ ሜንሳህ ጋር ብቻውን ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው፣ 13ኛው ደቂቃ እሸቱ መና ከርቀት አክርሮ የመታውን ግብጠባቂው ሶሆሆ ሜንሳህ ያዳነበት የመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃ ዲቻዎች የፈጠሩት መልካም የጎል አጋጣሚ ነበር።
ተዳክመው የቀረቡት ሀዋሳዎች ከሶሆሆ ሜንሳህ መልካም እንቅስቃሴ ውጭ ብዙም ቅርፅ የሌለው እንቅስቃሴ ነበር ሲያሳዩን የነበረው። ወጣቱ መስፍን ታፋሰ በግሉ ጥረት ለማድረግ ቢሞክርም እንቅስቃሴው የተሳካ ነበር ማለት ግን አይቻልም።
የአጋማሹ የመጨረሻ ለጎል የቀረበ ሙከራ የተመለከትነው በወላይታ ድቻ በኩል በ32ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኃይሌ እሸቱ በጥሩ ሁኔታ በግንባሩ ቢገጨውም የሀዋሳው ተከላካይ አክሊሉ አውጥቶበታል። ትርጉም አልባ እንቅስቃሴ በሜዳ ላይ እየተመለከትን የቀጠለው ጨዋታ 36ኛው ደቂቃ የወላይታ ድቻው ቸርነት ጉግሳ እና የሀዋሳው አስጨናቂ ሉቃስ ሜዳ ላይ በፈጠሩት ግብግብ ፌደራል ዳኛ ኢያሱ ፈንቴ ሁለቱንም ተጫዋቾች በቀይ ካርድ ከሜዳ አስወግደዋቸዋል።
ከእረፍት መልስ ከመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ እጅግ በወረደ መልኩ መደበኛ ያልሆነ ውድድር በሚመስል መልኩ ጨዋታው ቀጥሎ ምንም አይነት የጎል ሙከራ ሳይደረግበት በተጫዋች ቅያሪ ፣ መድረሻ የሌለው ረጃጅም ኳስ በዝቶበት መደበኛው ክፍለ ጊዜ 0-0 በመጠናቀቁ ጨዋታው ወደ መለያ ምት አምርቷል። የሀዋሳው ግብጠባቂ ሶሆሆ ሜንሳህ ባዳነው መለያ ምት እና ራሱ ባስቆጠረው የመጨረሻ የመለያ ምት ጎልም ሀዋሳ ከተማ 8-7 አሸንፎ ግማሽ ፍፃሜውን ተቀላቅሏል።
ሀዋሳ ከተማ በግማሽ ፍፃሜው ሐምሌ 11 ቀን በቅርቡ ፌዴሬሽኑ በሚያወጣው ዕጣ በሚለይ ቦታ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የሚጫወት ይሆናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡