ካፍ የ2022 የዓለም ዋንጫ ማጣርያ አካሄድን ይፋ አደረገ

በ2022 በካታር አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የዓለም ዋንጫ ከአፍሪካ የሚያልፉ ሀገራትን ለመለየት የሚደረገው የማጣርያ ውድድር አካሄድን ካፍ ይፋ አድርጓል።

ከ2014 የዓለም ዋንጫ ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያለው ይህ የማጣርያ ውድድር አካሄድ የቅድመ ማጣርያ፣ የምድብ እና የመለያ ጨዋታ ዙሮችን ያካተተ ነው።

– በዚህ የማጣርያ ውድድር 26 ከፍ ያለ የፊፋ ደረጃ ያላቸው ቡድኖች በቅድመ ማጣርያው የማይሳተፉ ሲሆን በቀጥታ ወደ ምድብ ድልድል ያመራሉ።

– ቀሪዎቹ 28 ቡድኖች ባላቸው የፊፋ ወቅታዊ ደረጃ መሠረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ 14 ቡድኖች ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙ 14 ቡድኖች ጋር በቅድመ ማጣርያ ተጫውተው አሸናፊ 14 ብሔራዊ ቡድኖች ወደ ምድብ ድልድል ያመራሉ።

– በድምሩ 40 ብሔራዊ ቡድኖች (26 በቀጥታ፣ 14 በቅድመ ማጣርያ የገቡት) በ10 ምድቦች ተከፋፍለው የሚወዳደሩ ይጫወታሉ።

– ከየምድቡ ቀዳሚ ደረጃ ይዘው የሚያጠናቅቁ 10 ሀገራት እንደየደረጃቸው ከፍተኛው ከ ዝቅተኛው ጋር በሚደረግ ድልድል እርስ በርስ የመለያ ጨዋታ ተጫውተው አሸናፊዎቹ 5 ብሔራዊ ቡድኖች የካታሩን ትኬት የሚቆርጡ ይሆናል።

– ኢትዮጵያ ለማሻሻል ብዙም ትኩረት የማትሰጠው የፊፋ ደረጃ በማጣርያዎች (በተለይም በቅድመ ማጣርያዎች) ድልድል ላይ ያለው ሚና ከቀላል የሚባል አይደለም። ሀገራችን በአሁኑ ሰዓት 44ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን ምናልባትም ከ40 በታች ባሉ ደረጃዎች ውስጥ ብትገኝ እጅግ ዝቅተኛ ከሆኑ ሀገራት ጋር የማጣርያ ጨዋታዋን ለማድረግ ትደለደል ነበር። ሆኖም አሁን ያለችበት ደረጃ የዝቅተኛው ጎራ ውስጥ የሚካተት በመሆኑ ከ27-40ኛ ደረጃ ካሉ ሀገራት ማለትም በአፍሪካ ዋንጫ የተካፈሉት ቡሩንዲ፣ ናሚቢያ፣ አንጎላ እና ታንዛኒያን ጨምሮ ሩዋንዳ፣ ኢኳቶርያል ጊኒ፣ ቶጎ፣ ጋቦን እንዲሁም ጎረቤቷ ሱዳንን በቅድመ ማጣርያ ዙር ልታገን ትችላለች።

– ኢትዮጵያ በ2014 የዓለም ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ ሶማሊያን አሸንፋ ወደ ምድብ በመግባት እስከ መለያ ጨዋታ መድረሷ የሚታወስ ሲሆን በ2018 ቅድመ ማጣርያ በኮንጎ ሪፐብሊክ ተሸንፋ ወደ ምድብ ሳትገባ ቀርታለች።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡