ድሬዳዋ ከተማ የእግድ ውሳኔ ተላለፈበት

ድሬዳዋ ከተማ ሶስት ተጫዋቾችን በማሰናበቱ ፌድሬሽኑ ያለ አግባብ ነው ውሳኔው በሚል ከሁለት ጊዜ በላይ ደመወዛቸው እንዲከፍል በደብዳቤ ቢጠይቅም ተግባራዊ ባለማድረጉ ፌዴሬሽኑ የእግድ ውሳኔ ክለቡ ላይ አስተላልፏል፡፡

ድሬዳዋ ከተማ በመጋቢት ወር መጀመሪያ አጥቂዎቹን ዮናታን ከበደ እና ሀይሌ እሸቱ ተከላካዩ ወሰኑ ማዜን ከክለቡ ቀሪ ኮንትራት እያላቸው ማሰናበቱ ይታወሳል፡፡ ሆኖም የተሰናበቱት ሶስቱም ተጫዋቾች ቀሪ የስድስት ወራት የውል ኮንትራት እያለን ያለ አግባብ ተሰናብተናል በሚል ለፌዴሬሽኑ ቅሬታን በወቅቱ ያሰማሉ፡፡ ሆኖም ፌድሬሽኑ ጉዳዩን ከተመለከተ በኃላ ተጫዋቾቹ ያቀረቡት ቅሬታ ተገቢ ነው በማለት በ10 ቀን ውስጥ ለተጫዋቾቹ ይከፈል የሚል ደብዳቤን ለክለቡ መጀመሪያ ቢልክም ክለቡ ጋዜጣዊ መግለጫን በመስጠት አግባብ አደለም በሚል በመቃወም ለይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ይግባኝ ማለቱም ይታወሳል፡፡

ፌዴሬሽኑ በመጀመሪያው ደብዳቤ ባለመመራቱ ተጨማሪ ደብዳቤ ፌድሬሽኑ ለድሬዳዋ በመላክ ከ20 ቀን በፊት ማስጠንቀቂያ አዘል ደብዳቤን በድጋሚ ቢልክም የተጫዋቾቹን ደመወዝ ተፈፃሚ ባለማድረጉ ምክንያት የዲሲፕሊን ኮሚቴ ለሶስተኛ ጊዜ ደብዳቤን በመፃፍ ድሬዳዋ ከተማን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ከሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ከዛሬ ጀምሮ ማገዱን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችሁ መረጃ ይጠቁማል፡፡

ድሬዳዋ መታገዱን የሚገልፅ ደብዳቤ ይህን ይመስላል👇


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡