አዳማ ከተማ ራሱን ከኢትዮጵያ ዋንጫ አገለለ

በኢትዮጵያ ዋንጫ ባህርዳር ከተማን 3-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ሩብ ፍፃሜውን የተቀላቀለው አዳማ ከተማ ራሱን ከኢትዮጵያ ዋንጫ ማግለሉ ተረጋግጧል።

በኢትዮጵያ ዋንጫ በሩብ ፍፃሜው ከፋሲል ከነማ ጋር የፊታችን እሁድ ሐምሌ 7 ቀን በጎንደር ዐፄ ፉሲል ስታዲየም ጨዋታውን እንዲያደርግ መርሐግብር የወጣለት ቢሆንም በበጀት እጥረት ምክንያት ወደ ጎንደር እንደማያቀና ታውቋል።

በኢትዮጵያ ዋንጫ ያለፉትን ዓመታት ጀምሮ ራሳቸውን ከውድድር የሚያገሉ ክለቦች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን በዘንድሮ ዓመት አዳማ ከተማን ጨምሮ ድሬደዋ ከተማ፣ ስሑል ሽረ እና ደቡብ ፖሊስ ራሳቸውን ከውድድሩ ማግለላቸው ይታወሳል።

በተያያዘ ዜና ኢትዮጵያ ቡናም ከኢትዮጵያ ዋንጫ ራሱን ማግለሉን በደብዳቤ ለፌዴሬሽኑ ያስገባ ቢሆንም አሁን በደረሰን መረጃ አቋሙን በመቀየር በውድድሩ ላይ እንደሚሳተፍ እና አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ ተጫዋቾቹን ለጨዋታው እንዲያዘጋጅ መነገሩን ለማወቅ ችለናል።

በግማሽ ፍፃሜው ፋሲል ከነማ ከ መቐለ 70 እንደርታ የሚያገናኘው ጨዋታ ካለው የፀጥታ ስጋት አኳያ በገለልተኛ ሜዳ ለማድረግ ፌዴሬሽኑ እያሰበ መሆኑን ሰምተናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡