አንደኛ ሊግ | በሁለት ተጫዋቾች ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላለፈ

በአንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ላይ የዲሲፕሊን ግድፈት አሳይተዋል በተባሉት ሱሉልታ ከተማ እና ሰሎዳ ዓድዋ ተጫዋቾች ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላለፈ።

ከአንደኛ ሊግ ወደ ከፍተኛ ሊግ የሚያድጉ ስድስት ቡድኖች ለመለየት በባቱ (ዝዋይ) ላይ በ18 ቡድኖች መካከል የማጠቃለያ ውድድር ከሐምሌ 7 ጀምሮ እየተካሄደ እንደሆነ ይታወቃል። ከተደረጉ ጨዋታዎች መካከል ሰሎዳ ዓድዋ ከ መተሐራ ስኳር ያለ ጎል በአቻ ውጤት በተጠናቀቀበት ጨዋታ ሀፍቶም ገ/እግዚአብሄር የተባለ የሰሎዳ ዓድዋ ተጫዋች የረዳት ዳኛውን ውሳኔ በመቃወም ለመማታት በሞመከሩና የዳኛን እጅ በመጠምዘዝ ሰዓቱን መበጠሱ በዳኛ የታዛቢ ሪፖርት የተገለፀ በመሆኑ ተጫዋቹ ለፈፀመው ጥፋት 3 ወር ከማንኛውም እግርኳስ እንዲታገድ እና አስር ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል ተወስኖበታል።

በሌላ በኩል ደግሞ ሱሉልታ ከተማ ቡሌ ሆራን 3-2 በረታበት ጨዋታ ላይ ፍሬዕዝራ መንግስቱ የተጋጣሚ ቡድን አመራሮችን አፀያፊ ስድብ በምልክት በመሳደቡ በቀይ ካርድ ከሜዳ ከመወገዱ ባሻገር በውድድሩ የዲሲፕሊን መመርያ መሠረት ሦስት ጨዋታ እና ሦስት ሺህ ብር እንዲከፍል ቅጣት ተላልፎበታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡