የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) በ2020 ካሜሩን ላይ ይስተናገዳል፡፡ ለዚሁ ውድድር በቅድመ ማጣሪያው ከጅቡቲ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ በአዳማ ከተማ ዝግጅቱን ጀምሯል።
አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ እና ረዳቶቻቸው ጥሪ ካደረጉላቸው 23 ተጫዋቾች መካከል ሙጂብ ቃሲም በፓስፖርት ጉዳይ በዛሬው ልምምድ ላይ ካለመገኘቱ በቀር የተቀሩት 22 ተጫዋቾች ተገኝተዋል። ከ10:30 የጀመረው የዛሬው ልምምዳቸው ለ45 ደቂቃ የቆየ ሲሆን ቀለል ያለ ከኳስ ጋር ያተኮረ ልምምድ ሰርተዋል።
ብሔራዊ ቡድኑ ለአንድ ሳምንት በአዳማ በሚኖረው ቆይታ የተለያዩ የልምምድ መርሐ ግብሮችን በማውጣት ዝግጅቱን እየሰራ የሚቆይ ሲሆን ምናልባትም በኢትዮጵያ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ የፊታችን እሁድ ተፋላሚ የሚሆኑት ፋሲል ከነማ እና ሀዋሳ ከተማ ከብሔራዊ ቡድን ጋር በዝግጅት ላይ የሚገኙ ተጫዋቾቻቸውን የጨዋታው ቀን ሲቃረብ ሊወስዷቸው እንደሚችሉ ሰምተናል።
ብሔራዊ ቡድኑ ሐምሌ 19 የመጀመርያ ጨዋታውን ወደ ጁቡቲ በማቅናት ከተጫወተ በኋላ በሳምንቱ የመልሱን ጨዋታ ድሬዳዋ ላይ እንደሚያደርግ ሲታወቅ የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታውን በድል የሚያጠናቅቅ ከሆነ መስከረም ወር ላይ ከሩዋንዳ ጋር የሚጫወት ይሆናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡