የሀገሪቱ ውጤታማ እና አንጋፋ አሰልጣኞችን የሥራ ህይወት፣ ተሞክሮ እና አስተሳሰብ በሚዳስሰው በዚህ ገፅ ከቀድሞው ተጫዋች እና አሰልጣኝ ካሣሁን ተካ ጋር በሁለት ክፍል ከስልጠና ህይወታቸው እና ከቴክኒክ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን አንስተን ቆይታ ማድረጋችን የሚታወስ ነው። በዛሬው የመጨረሻ ክፍል መሰናዶ ደግሞ ስለ አሰልጣኞች እና አሰልጣኝነት እያነሳን ቆይታ እናደርጋለን።
ከአንጋፋዎቹ በኋላ በመጡት የአሰልጣኞች ትውልድ እና በእናንተ መካከል ሰፊ ልዩነት ያለ ይመስላል፡፡ እናንተ ከሉቻኖ ቫሳሎ፣ መንግስቱ ወርቁ እና ሸዋንግዛው አጎናፍር የመሳሰሉ ቀደምት ባለሙያዎች ልምድ በመውሰድ እና የእነርሱን ፈለግ በመከተል በአጨዋወት፣ በሥነምግባር፣ በተጫዋቾች አያያዝ… በሌሎችም ጉዳዮች ብዙ ትምህርቶችን ወርሳችኋል፡፡ እነዚህ አዎንታዊ ጎኖቻችሁ ወደ ቀጣዩ የአሰልጣኞች ትውልድ ያልተላለፉት ለምንድን ነው? ንፉግ ሆናችሁ ይሆን?
★ ንፉግ እንኳ አይደለንም፡፡ እኛ በአጼ ኃይለሥላሴ ጊዜ ኳስ የተጫወትን ነን፡፡ ያኔ ጨዋታው የሚዘወተረው በትምህርት ቤቶች መካከል በሚካሄዱ ውድድሮች ነው፡፡ በአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች፣ በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች እና በኮሌጆች የሚታዩት ፉክክሮች የተጋጋሉ ነበሩ፡፡ ስለዚህ ለት/ቤት መጫወት እንደ ትልቅ ጀብድና ክብር ይታያል፡፡ እኔ በልጅነቴ መሃንዲስ መሆን እፈልግ ነበር፡፡ ወደ እግርኳስ ምን እንደሳበኝ አላውቅም፡፡ ይሁን እንጂ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ‘ <ማትሪክ> ባላልፍ በእግሬ የምበላ ሰው ነኝ፡፡’ እያልኩ እዘባበት ነበር፡፡ ሰፈሬ ኮካኮላ ጋር ዳርማር አካባቢ ስለሆነ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ሽመልስ ሃብቴ ተማርኩ፤ ከዚያ አንድ ኳስ የሚወድ የቡድናችን ደጋፊ ገና 11ኛ እና 12ኛ ክፍል ሆኜ አርባ ብር ያሰጠኝ ጀመር፡፡ ይህ ብር ያኔ እኔን ከሁሉ ከፍ አደረገኝ፡፡ እናም በአውቶቡስ የምሄደውና ትልቅ ሆቴል የምመገበው እኔ ሆንኩ፡፡ አስር የሸዋ ዳቦ በ25 ሳንቲም በሚሸጥበት ዘመን በ1.25 ወር መሉ መኖር ትችላለህ፡፡ በክለብ ቆይታዬ ደግሞ ጎል አስቆጥራለሁ፤ ሁለተኛ ዲቪዚዮን እየተጫወትኩ የማላገባበት ተጋጣሚ አልነበረም፤ በዚህም ዝነኛ ሆንኩና በአሰልጣኙ ሉቻኖ አማካኝነት ብሄራዊ ቡድን ተጠራሁ፤ ላምን አልቻልኩም! ደብረዘይት ሄድን፤ መሰረታዊ የሆኑ ነገሮችን ገመገመኝ፡፡ ማንቀርቀብ በቅጠል የተማርኩ ነኝ፤ ለዓይን እስኪታክት አንጠባጥባለሁ፡፡ ሁሉንም ችሎታዬን ከፈተነኝ በኋላ “ኮተን መሄድ ትፈልጋለህ ወይ?” ብሎ ጠየቀኝ፡፡ ጥጥ ማህበር እኮ ያኔ እነ ኢታሎ የሚጫወቱበት ክለብ ነበር፡፡ ‘ ኧረ እኔ አልችልም!’ አልኩት፡፡ ” ትችላለህ እንጂ! እዚህ የተጠራኸው’ኮ ስለምትችል ነው!” አለኝ፡፡ የመጓጓዣ ገንዘብ ሰጠኝ፤ ሄድኩ፡፡ በስድስተኛው ወር በብሄራዊ ቡድኑ ውስጥ ቋሚ ተሰላፊ ሆንኩ፡፡ ከዚያ በኋላ ለብሄራዊ ቡድን ተመርጬ በብቃት መውረድ ሳቢያ የተቀነስኩበት አጋጣሚ የለም፡፡ እንግዲህ እስከ መጨረሻው ድረስ በዚህ መልኩ ቀጠልኩ፡፡
ወደ ዋናው ነጥብ ስመጣ ስልጠና ትልቅ ጥቅም የሚኖረው ከሁሉም ባለሙያዎች ብዙ ቁም ነገሮችን እየወሰድክ በተለየዩ አሰልጣኞች ስር በተጫዋችነት ስታሳልፍ ይመስለኛል፡፡ እኔ ከመንግስቱ፣ ከሉቻኖ፣ ከሸዋንግዛው፣ ከታደሰ ወልደአረጋይ፣ ከፈረንጆቹ… ከእያንዳንዳቸው የተለያዩ ነገሮችን ወስጃለሁ፡፡ የጨዋታ ዝርዝር ትንተና (Game Analysis) በተመለከተ መንግስቱ ወርቁ በምን መልኩ ጨዋታዎችን አንብቦ እንደሚያብራራ ስላየሁ ከእርሱ ያን ተምሬያለሁ፤ ከሉቻኖም እንዲሁ፡፡ እነዚህ ተመክሮዎች ት/ቤት አይገኙም፡፡ ቲዎሪው የትም ሊኖር ይችላል፤ ነገር ግን ከተግባራዊ ልምድ ጋር የተያያዘ አይሆንም፡፡ ‘Anybody can be a coach. But it is very difficult to be a good one.’ አየህ ያለ ልምድ ጥሩ ሆነህ ለመውጣት አስቸጋሪ ነው፤ የአካል ብቃት ልምምድ (Fitness Training) ለማሰራት ስትፈልግ በዚያ ዘርፍ ምርጥ የነበረው አሰልጣኝህ በአዕምሮህ ይመላለሳል፤ የተደራጀ ልምምድ (Organized Training) ልትሰጥ ስታስብም በፊት ሲያሰራህ የምታደንቀው ሰው በሃሳብህ ድቅን ይላል፡፡ በሥነ ምግባር፣ ቡድን በመምራት፣… በሌሎችም ጉዳዮች በሥራቸው ያለፍክባቸው ባለሙያዎች ትውስ ይሉሃል፡፡ ግጥሚያ ሲደርስ የጭንቀት መፈጠር (Game Fever) ካለብህ ተጫዋቾችህ ያንን እንዲያውቁ ማድረግ የለብህም፡፡ ስም መጥቀስ አያስፈልግም እንጂ ገና ጨዋታው ሳምንት እየቀረው ምግብ ከጉሮሯቸው የማይወርድላቸው አሰልጣኞችን አውቃለሁ፡፡ በተግባር ውስጥ ስታልፍ እነዚህን ችግሮች እንዴት እንደምታልፍ ትማራለህ፡፡ ምንም በማያወላዳ ሁኔታ የአሰልጣኞቻችን አበርክቶ ሁላችንም ውስጥ አለ፡፡
ሌላው እኛ በቀለም ትምህርትም ቢሆን ጥሩ ነበርን፡፡ መግባባት እንችላለን፤ እናነባለን፡፡ እዚህ ለአንድ ወር ያህል ጠዋትና ከሰዓት በከፍተኛ ጫና የሚሰጠውን የፊፋ ኮርስ ስንወስድ ዳቦ በሙዝ እየበላን አሳልፈናል፡፡ ፈተናው ከዙሪክ ነበር የሚመጣው፤ ዛሬ ስለተማርከው ነገ በጠዋት ትፈተናለህ፤ ውጤትህ ወዲያውኑ ሁሉም ሰልጣኝ በሚያየው መልኩ ግድግዳ ላይ ፊት ለፊት ይለጠፋል፤ ዝቅተኛ ውጤት ካስመዘገብክ ታፍራለህ፡፡ ማንም ወድቆ መታየት ስለማይሻ ጠንክሮ ይሰራል፡፡ የአካዳሚ እውቀት ካለህ ደግሞ ጥሩ ውጤት ታመጣለህ፤ ምንም ችግር አይኖርብህም፡፡ አሁን ያሉት አሰልጣኞች ግን ጥሩ ሲጫወቱ የመጡ ቢሆኑም የቋንቋ ችግር እንዳለባቸው ታስተውላለህ፡፡ አሁን እኛ የምንለውን ነገር መናገር አይችሉም፡፡ ልናስተላልፍ የምንችለው “ተማሩ!” የሚለውን መልዕክት ነው፡፡ በአፍሪካ ውስጥ የፊፋ የሥራ ቋንቋ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ አረብኛ እና ስዋሂሊ ናቸው፡፡ ከእነዚህ አራት ቋንቋዎች ውጪ ስለሌለ ራስን በአንደኛው መግባቢያ አብቅቶ መጠበቅ የግድ ይላል፡፡ በትምህርቱ ያለፍንባቸው የማንበብ፣ የመጻፍና ራስን በአግባቡ የመግለጽ መሰረታዊ ልምዶች እኛን ጠቅመውናል፡፡
ቀድሞ በእናንተ ስር በተጫዋችነት ያሳለፉና አሁን አሰልጣኝነቱ ሙያ ላይ ያሉ ሰዎች ጋር የተነሳሽነት ችግር ነበር ማለት ነው?
★ ተናግሬዋለሁ! በጊዜው ብዙ መክረናል፡፡ አሁን የሚሰጡ ልምምዶችን እናስተውል እስቲ! ከብዙ ዓመታት በፊት ስናሰራ የነበረውን ልምምድ አሁንም ሲያሰሩ አያለሁ፤ እኔ የድሮውን ልምምድ በፍጹም አላሰራም፡፡ በዚያን ወቅት እኛ የምናሰራው ልምምድ ውጤታማ ካደረገን አሰልጣኞቹ አሁንም ይጠቀሙበታል፡፡ ካለፉባቸው የተለያዩ አሰልጣኞች እየቀላቀሉ (mix) አልያም የአንደኛውን በቀጥታ በመውሰድ (copy) ያሰራሉ፡፡ እግርኳሱ ውስጥ ለውጥ ይካሄዳል፡፡ (There is evolution in Football.) እንደ አሰልጣኝ ራስህን እየቀየርክ መሄድ አለብህ፡፡ ያን ለውጥ ለማምጣት ደግሞ ማንበብ እና አርቆ ማየት የግድ ይላል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የመፍጠር አቅም እንዲኖርህ ራስህ መጣር ይኖርብሃል፡፡
በራድዮ የአሰልጣኞች ሀገራዊ ፓናል እንዲለመድ ጥረሃል፡፡ አላማው ምንድን ነበር?
★ አሰልጣኞች ሆነው ቃለ መጠይቅ ለመስጠት የሚቸገሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ በዚህ ጉዳይ ለአሰልጣኞች የሚዘጋጅና ቃለ-ምልልሶችን እንዴት ባለ ስልት ማከናወን እንደሚገባ አስረጅ የሚዲያ ኮርስ አለ፡፡ (How to tackle the Interview) አልፎ አልፎ ጋዜጣዊ መግለጫዎች (Press Conference) ላይ የምትናገረው ሊጠፋህ ይችላል፡፡ እነዚህን ተግዳሮቶች የምታልፈው የሚዲያ ኮርስ ስትማር ነው፡፡ በአሰልጣኝነቱ ዓለም ከፍ ወዳለ ደረጃ በተጓዝክ ቁጥር ማወቅ የሚኖሩብህ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ እኛ እድሉ ስለነበረን ምንም አይነት ጥያቄዎች ቢመጡ ግድ የለንም፡፡ እኔ ስለምጠየቀው ነገር አውቃለሁ፤ ከጥያቄው ተነስቼ ምላሽ እሰጣለሁ፡፡ ፓናሉን ለማዘጋጀት የፈለግነውም ይህ ልምድ እንዲዳብር በማሰብ ነው፡፡ ለአዲስ አበባ አሰልጣኞች ማኅበር በየወሩ አዳዲስ ነገሮች ሲመጡ አሳውቃቸው ነበር፡፡ ሁሌም አበክሬ የምናገረው “ቋንቋ ተማሩ!” የሚለውን ሐሳብ ነበር፡፡ አብዛኞቹ የሰሙኝ አይመስለኝም፡፡ እነ ጳውሎስ ጌታቸው እና ዮሴፍ ተስፋዬ ተጫዋቾቼ ነበሩ፡፡ ሲያገኙኝ ” ያኔ አንተ የምታስተምረን…” ይሉኛል፡፡ አየህ በተጫዋችነት ዘመንህ ከአሰልጣኝህ የምታገኘው ይህን መሰል እውቀት ነው፡፡ ቲዎሪውንማ በደንብ ያውቁታል፡፡ ያ ልምድ ከሌለ ንድፈ ሐሳባዊውን እውቀት ወደ ተግባር ለመለወጥ ትቸገራለህ፡፡ አንድ አሰልጣኝ ኳስ መጫወት ከጀመርክበት ጊዜ አንስቶ በስራቸው ያለፈባቸው ሰዎች ሙሉ ውጤት ነው፡፡ የከፍተኛ ደረጃ ተማሪ ሆነህ የሒሳብ ትምህርት በጣም ደስ ይልህ ከነበረ ያን መምህር መቼም አትረሳውም፡፡ ሁልጊዜ እርሱ ያለው ትዝ ይልሃል፡፡ በትምህርት ዓለም ሰርተህ ከተሳሳትክ በኋላ በእርማት የምታገኘው እውቀት ፍጹም ከጭንቅላትህ አይጠፋም፡፡ ቀድመህ ትክክል የሆንከውንማ ብዙም ትኩረት አትሰጠውም፡፡ እናም ውይይት ስታደርግና ስትነጋገር ለራስህ የመፍታታት ሁኔታ ትፈጥራለህ፤ በመጠያየቅ ደግሞ እውቀት የመቃረም እድል ታመቻቻለህ፡፡ የፓናሉ ግብም ይህን ማሳካት ነበር፡፡
ከላይ ያነሳሃቸው ችግሮች ሌሎቹን የእግርኳሱ ባለ ድርሻዎች አይመለከትም? ተጫዋቾች፣ የቡድን መሪዎች፣ የክለብ አመራሮች፣…
★ አይ! በመጀመሪያ የቡድን መሪ ሲመደብ በድርጅቱ የትራንስፖርት ክፍል ኃላፊ ከሆነ መኪና እንዲፈቅድ ተብሎ ነው የሚመጣው፡፡ ስለ ኳሱ ምንም ግንዛቤ አይኖረውም፡፡ አንዳንዴ ደግሞ የተጫዋቾች፣ አሰልጣኞችና የጤና ባለሙያዎችን ወርሃዊ ደመወዝ ቶሎ ቶሎ እንዲያቀለጣጥፍ ዋናውን የሒሳብ ሹም ከቡድን መሪ አባላት አንዱ ታደርገዋለህ፡፡ እነዚህን በመሳሰሉ መስፈርቶች እንጂ የስፖርት እውቀቱ ጥያቄ አይነሳበትም፡፡ ስታዲየም መግባትም እንደ መለኪያ ይወሰዳል፤ ‘እንዴ እሱማ’ኮ ቅዳሜና እሁድ ከስታዲየም አይቀርም!’ ይባልና የኮሚቴ አባል ይደረጋል፡፡ ከያዝከው እውቀት ጋር ባልተያያዙ መመዘኛዎች ሹመቱ ሊሰጥህ ይችላል፡፡ ያ ሰው እዚያ ትሪቡን ቁጭ ብሎ የሰማውን ይዞ ይወጣና ካንተ ጋር ይጨቃጨቃል፡፡ ከላይ ያሉትም ቢሆኑ ምን የሚያውቁት ነገር ነበር? የክለብ ፕሬዘዳንት ስለ ዓለም እግርኳስ የሚያውቀው ነገር ነበር? ስለ አፍሪካውስ? በፍጹም!
እዚህ ጋር አንድ ነገር ላንሳ! ይህን ሌላም ሚዲያ ላይ ተናግሬዋለሁ፡፡ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን ጋሽ ይድነቃቸው የፌዴሬሽኑ ፕሬዘዳንት በነበሩ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ <ፕሮፌሽናል> ተጫዋቾች አይሳተፉም ነበር፡፡ የአፍሪካ እግርኳስ ማኅበር አማተር ስለነበር በአውሮፓና በሌሎች አህጉራት ለሚገኙ ክለቦች ለሚጫወቱት ተጫዋቾች ተሳትፎው ተከልክሏል፡፡ በዚያ ወቅት ከሜዳችን ውጪ ማዳጋስካር ላይ ጨዋታ ኖረን፤ የእግርኳስ ማኅበራችን ጸሃፊና ቡድናችንን የሚመራው አቶ ካሣ ነበር፡፡ ክቡር ጋሽ ይድነቃቸው አቶ ካሣን ይጠራውና እኔ አሁን የዘነጋሁትን አንድ የማዳጋስካር ፕሮፌሽናል ተጫዋች ስሙን ይጠቅስለትና ” ኖንት ለሚባል የፈረንሳይ ክለብ ይጫወታል፤ እርሱን ካሰለፉት የክስ <ሪዘርቭ> አስይዝ፡፡” ብሎ ያዘዋል፡፡ የሚገርመው እኛ እዚያ ስንሄድ ተጫዋቹ ሊጫወት ተዘጋጅቶ ጠበቀን፡፡ ትልቅ ተስፋም ጥለውበት ቆዩን፡፡ የከተማው ሰዎች በሙሉ የተጫዋቹን ምስሉ እያሳዩ ” ይህን ሰው ታውቁታላችሁ?” እያሉ ይጠይቁናል፡፡ አምስት እንደሚያገባብን በዛቻ መልክ ይተነብያሉ፡፡ በመጨረሻም ጨዋታው ሊጀመር ወደ ሜዳ ልንገባ ስንል የክስ ሪዘርቩን ማስያዝ ስላለብን አቶ ካሣ ይሄድና ” እገሌ የተባለው ተጫዋች ተሰላፊነት ተገቢ አይደለም፡፡” ብሎ ሲከስ ሰዎቹ ደነገጡ፡፡ የስታዲየሙ ጋዜጠኞችም ለተመልካቹ ያ የተመኩበት ተጫዋች መግባት እንደማይችል ሲያሳውቁ የማዳጋስካር ደጋፊዎች “ይግባ!” ብለው መጮህ ጀመሩ፡፡ ከዚያ ተጫዋቹ ገባና የእኛን ጠንካራ የተከላካይ ክፍል አልፎ ሁለት ጎሎችን አስቆጠረ፡፡ ከእኛ በኩልም <ሰበታ> ሁለት ጎሎች አገባና 2-2 አቻ ተለያየን፡፡ በመሰረቱ ጨዋታው ፎርፌ ሊሰጠን ይገባ ነበር፡፡ ይህ አጋጣሚ ምን ያሳየናል? አቶ ይድነቃቸው የሃገሩን ወይም የአፍሪካን ብቻ ሳይሆን የዓለምን እግርኳስ አብጠርጥሮ ስለሚያውቅ ብዙ ህግጋትና ደንቦችን ያጤን እንደነበር ያመላክታል፡፡ አሁን ይህን የሚያውቁ መሪዎች አሉን ወይ? እዚህ አዲስ አበባ ቁጭ ብሎ ባህርዳር ላይ እየተደረገ ያለውን እንኳ በቅጡ አያውቅም፡፡
ፌዴሬሽኑ በሁሉም ዘርፍ እውቀት ያለው አስተዳደር (All Rounded Manager) የሌለበት ተቋም ሆኗል፡፡ ድሮ’ኮ ስፖርቱ ስርዓትና የህግ የበላይነት ስለሰፈነበት ማንም እንዳሻው አያሾረውም፤ ተጫዋቾችም ዝም ብለው እንደፈለጉ ከቦታ ቦታ የሚሽከረከሩበት አይደለም፡፡ ደንቡ በጣም ጥብቅ ነበር፡፡ የእርስ በርስ መስተጋብሩ ቤተሰባዊ ትስስር ፈጥሯል፡፡ ለምሳሌ በዝውውር ወቅት “አንድ ተጫዋች ከነበረበት ቡድን ወደ ሌላ ቡድን ተዛውሮ ነጻ የሚሆነው ሁለት ዓመት ካረፈ በኋላ ነው፡፡” ይላል፡፡ ስለዚህ እዚያው የነበርክበት ስለምትቆይ የቡድን ስሜት፣ የማልያ ፍቅርና ከደጋፊ ጋር የሚፈጠር መስተጋብህ እየጠነከረ ይሄዳል፡፡ ከዚያ በተጨማሪ የተረጋጋ ቡድን (Constant Team) ይኖርሃል፡፡ በዚያ መልኩ የቀድሞው እግርኳስ በጥሩ ሁኔታ ሰንብቷል፡፡ በአሁን ዘመን ሁሉም ነገር ምቹ ነው፡፡ በርካታ ገንዘብ ለእግርኳሱ ይመደባል፤ ተጫዋቾች ከፍተኛ ክፍያ ያገኛሉ፤ “አያግኙ!” አይባልም፤ ያግኙ! ግን ‘የሚያገኙትን ያህል ይገባቸዋል ወይ?’ ዋናው ጥያቄ ነው፡፡ ወደፊት ሊያድግ የማይችል ነገር የሆነ ቦታ ላይ መቆሙ አይቀሬ ነው፡፡ አንድ ሃኪም በወር አምስት ሺህ ብር እያገኘ ኳስ ተጫዋቹ ሰባ አምስት ሺህ ብር ሲከፈለው “የትኛው ይበልጥ ሃገራዊ ጥቅም ይሰጣል?” የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ ሃኪሙ ነፍስ የሚያተርፍ ሲሆን ተጫዋች ደግሞ አዝናኝ ነው፡፡ ይህ ንጽጽር ሳይመጣ ጠንቀቅ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ከሁሉ በላይ ‘እውቀት ያለው ባለሙያ ስፖርቱን ይምራ!’ ከተለያዩ አካላት ስሰማ በድርጅት ውስጥ ሥራ አስኪያጅ ከሚሆን ይልቅ የስፖርት አመራሮች አባል መሆንን የሚያስቀድሙ አሉ፤ በቀላሉ ገንዘብ ይገኝበታላ!
ሥዩም አባተ ቡናን ለዚህ ደረጃ አድርሷል፤ መንግስቱ ወርቁና አስራት ኃይሌም ቅዱስ ጊዮርጊስ የሃገሪቱ ቁንጮ ክለብ እንዲሆን የራሳቸውን ትልቅ አሻራ አሳርፈዋል፡፡ ከአመራሮችም በላይ አንድን ክለብ በሁለት እግሩ የማቆም ግዙፍ ድርሻ ነበራችሁ፡፡ ሚስጥሩ ምንድን ነበር?
★ በመጀመሪያ የእኔን ተመክሮ ልግለጽ! ስለ እግርኳስ የማያውቅ አመራር ከእኔ ጋር ሊነጋገር አይችልም፡፡ ለማንም ይህንን አስረግጬ ነው የማሳውቀው፡፡ አመራሩ የምፈልገውን ካደረገ እቆያለሁ፤ አለበለዚያ ጥዬ እሄዳለሁ፡፡ አሁን ግን ፍራንኩ ሁሉ ነገር ላይ የዝርክርክነት ችግር (Mess Up) ፈጥሯል፡፡ ከተጫዋች ገንዘብ እየተቀበልክ መልሰህ ልትተቸው ወይም ልትገስጸው የምትችለው እንዴት ነው? እንዴትስ ከሜዳ ልታስወጣው ይቻልሃል? ለልምምድም ይሁን ለጨዋታ “አሞኛል!” ካለህ’ኮ “እሺ!” ባይ ትሆናለህ፡፡ ምክንያቱም አንዴ ተነካክተሃላ! (Spoiled ሆነሃል፡፡) በእርሱ ወጥመድ ውስጥ ስለገባህ ጠንከር አድርገህ እንኳ ልትተቸው የሚያስችል ቁመና አይኖርህም፡፡ በእኛ ጊዜ ቀልድ የለም፡፡ “ውጣ!” ስትለው “አልወጣም!” ቢልህ በቀጥታ ከቡድኑ ይባረራል፡፡ ከአሰልጣኞቹ በላይ ማንም አይኖርም፡፡ ከጀርባ ምንም ድብቅ ፍላጎት አናሳይም፤ እኛም የምንፈልገው ስም ብቻ ነበር፡፡ የእኔ እና የሥዩም ቡድኖች ሲጫወቱ እጅግ ፈታኝ ፉክክር ይታያል፡፡ “እነ ሥዩም ጋር’ኮ ሙሉጌታና ሚሊዮን አሉ፤ እነ ካሣሁን ጋርም እነ ዐቢይና ባና አሉ!” ይባላል፡፡ ጊዮርጊስ፣ መብራት ኃይል፣ መቻል፣… ስትሄድም የአንድን ጨዋታ ውጤት ሊቀይሩ የሚችሉና በትልልቅ ስም የሚነሱ ተጫዋቾች ነበሩ፡፡ ተጫዋቾቻችን የአሰልጣኙን ባህሪ ይወርሳል፤ አሰልጣኙም በጥሩ ስነምግባር የታነጸ ሆኖ ለመገኘት ይጥራል፡፡ ብርቱ የመሸናነፍ ፍልሚያ ይኖረናል፤ ስንሸናነፍ ደግሞ እንዲህ በቀላሉ እንዳይመስላችሁ፤ በጥሩ ጨዋታና በሰፊ የጎል ልዩነት ነው፡፡ ተመልካቹ’ኮ ስታዲየም መሰለፍ የሚጀምረው በጠዋት ነበር፡፡ ምን አግኝቶ ነው? ቆንጆ ነገር ስለሚመለከት! ከኮሚቴው ጋር ስንወያይ እኔ የምነግረውን ብቻ ይሰማል እንጂ ስለቴክኒክ አያወራም፡፡ “ዝምበል!” ነው የምለው፡፡ አሁን አንድ አሰልጣኝ ይህን ይላል? አይልም! የእኛ ዘመን አሰልጣኞች ጠንካራ ጎን ይሄ ነበር፡፡
እስቲ ያንተን ዘመን ምርጥ አሰልጣኞች እናንሳ…
★ አሁን የምጠራልህን አሰልጣኞች መቼም ልናገኛቸው አንችልም፡፡ ሥዩም አባተና አስራት ኃይሌ የተለዩ አሰልጣኞች ናቸው፡፡ ሰውነት ቢሻውም ከእኛ ጋር ከመሰረታዊ ኮርሶች ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ አብሮን የተማረ ሰው ነው፡፡ እርሱ እንደ’ኛ በሚታወቅ ክለብ ውስጥ አለመጫወቱ ጥላ አጥልቶበት ያን ጊዜ ብዙ እንዳይታወቅ አድርጎት ሊሆን ይችላል፤ ግን በጣም ጥሩ ስራ ሰርቶ አሸናፊ ሆኗል፡፡ ከበፊት ጀምሮ ውስጡ የሰረጸውን ትልቅ አሰልጣኝ የመሆን ምኞት አሳክቷል፡፡
ብዙ ስለማይወራለት ገዛኸኝ ማንያዘዋልስ ምን የምትለን ይኖራል?
★ ገዛኸኝ ማንያዘዋል እጅግ ብልህ አሰልጣኝ ነበር፡፡ የሚገርም ታሪክ ባለቤትም ነው፡፡ ገዛኸኝ እኮ ከነ መንግስቱና ሉቻኖ በፊት ምዕራብ ጀርመን ሄዶ የተማረ እንዲሁም በጋና ለሶስት ወር ኮርሶችን የተካከለ ባለሙያ ነበር፡፡ ገና የብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ሳለ የአሰልጣኝነት ኮርሶችን የመውሰድ ልምዱ ነበረው፡፡ እኔ የቴክኒክ ኮሚቴ አባል ሳደርገው ብቃቱን አውቅ ነበር፡፡ ፌዴሬሽን የነበሩ ሰዎች ተጠራጠሩት፤ የተምህርት ማስረጃዎቹን ሲመለከቱ ግን ደነገጡ፡፡ ወዲያው ኬንያ ተልኮ ሲመለስ ወጣት ቡድኑ ተሰጠው፡፡ የሰነድ አያያዝ ችግራችን እንጂ ትልቅ ስብዕና የነበረው አሰልጣኝ ነው፡፡ እኛ ሃገር የተጫወትክበት ክለብ እንኳ ስምህን በአግባቡ አይዝልህም፡፡
ሐጎስ ደስታ…
★ ሐጎስ ሲጫወት መንግስቱም ሉቻኖም አሰልጥነውታል፡፡ ያ ተመክሮው የፈጠረለት መነሳሳት ነው ትልቅ አሰልጣኝ ያደረገው፡፡ የትውልድ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ሁላችንም ይዘን የምንመጣው እኮ ጠንካራና ተወዳዳሪ ቡድን ነበር፡፡
አሁን ኳሷችንን ትከታተላለህ?
★ አዎ አያለሁ፡፡ አንዳንዴ ግን እንቅስቃሴው የድሮ ፊልም ነው የሚመስለኝ፡፡ አሁን እኮ አንዳንዱ አሰልጣኝ የልምምድ እቅዱን ” እንዲህ ባለ መንገድ ነው የማሰለጥነው፡፡” ብሎ የማኅበራዊ ገጾች ላይ ይለጥፋል፡፡ እንዴት እንዲህ ይደረጋል?! የስልጠና እቅድ እኮ የአሰልጣኙ ምስጢር ነው፡፡ ተገቢ አይደለም፡፡ በእንዲህ መልኩ መታየት ያለበት Low Profile ሲሆን ነው፡፡ እነዚህን ነገሮች ስመለከት በጣም ይገርመኛል፡፡
ስለ ካሣሁን ተካ…
ኢንስትራክተር ካሣሁን ተካ በኳስ ተጫዋችነት ዘመናቸው ከፍተኛ እውቅናን ያተረፉ ናቸው፡፡ የኢትየጵያ ብሄራዊ ቡድንንም በተጫዋችነትና አሰልጣኝነት ለማገልገል ችለዋል፡፡ የካፍ ኢንስትራክተር የሆኑት ካሣሁን ተካ እ.ኤ.አ. ከ1994 ጀምሮ በተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት በሲሸልስ፣ ዩጋንዳ፣ ሱዳን፣ ዚምባብዌ እና ጋና የአሰልጣኝነት ኮርስ ሰጥተዋል፡፡ በትምህርታቸውም በምስራቅ ጀርመን ላይፕዚሽ ዩኒቨርሲቲ በ<Physical Education> ዘርፍ በእግርኳስ specialize አድርገው በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ በምዕራብ ጀርመንም በአሰልጣኝነት የ<A Licence> ከኼነፍ አግኝተዋል፡፡ በ10ኛውና 11ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በተጫዋችነት ሃገራቸውን የወከሉት ካሣሁን ተካ በ1990ዎቹ አጋማሽ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት ተወዳድረው በከፍተኛ ድምጽ በአንደኝነት ተመርጠው ነበር፡፡ (ምንጭ – ኢንተር ስፖርት)