ላለፈው አንድ ወር በፈርዖኖች ሃገር ግብፅ ሲካሄድ የቆየው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነገ ሴኔጋል እና አልጀርያ በሚያደርጉት ተጠባቂ የፍፃሜ ጨዋታ ይጠናቀቃል። በተካሄደበት ወቅትና በተሳታፊ ቁጥር ብዛት የመጀመርያ የሆነው ይህ ውድድር እንደባለፉት ውድድሮች ሁሉ ማራኪ ጨዋታ ያልታየበት ቢሆንም ለእግር ኳስ ማኅበረሰቡ አዳዲስ ፊቶች በማሳየት ግን የተሻለ ነበር።
እስካሁን ድረስ ሃምሳ አንድ ጨዋታዎች ተደርገውበት 101 ግቦች (1.98 በጨዋታ) የተመዘገቡበት ይህ ውድድር ደጋፊ በብዛት ወደ ስታድዲም ገብቶ ያልተመለከተው ሲሆን ወቅቱ የአውሮፓ ሊጎች እረፍት ላይ የሆኑበት እንደመሆኑ የመገናኛ ብዙሀንን ትኩረት በስፋት ይስባል ተብሎ ቢጠበቅም እንደከዚ ቀደሙ ሁሉ በትላልቅ መገናኛ ብዙሃን በቂ ሽፋን ያልተሰጠው ነበር።
በዚህም ትልቁ የአህጉሪቱ ውድድር በአንድ ጨዋታ በአማካይ 16,896 ደጋፊዎች ብቻ ወደ ሜዳ ገብተው ሲመለከቱት የቴሌቪዥን ተመልካች ቁጥርም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
ውድድሩ ምንም እንኳ ጥሩ ፍሰት ያለው ጨዋታ ያልታየበትና የተመልካች ትኩረት ያልሳበ ቢሆንም ጥቂት የማይባሉ ጥሩ ጎኖች የተስተዋሉበትም ነበር። ከነዚህም የዳኝነት ጉዳይና የመጫወቻ ሜዳ ጥራት በቅድሚያ ይጠቀሳሉ።
ከግዜ ወደ ጊዜ የውድድር ደረጃው እየወረደ የሚገኘው ይህ ውድድር ልክ አውሮፓ ዋንጫ የውድድር ተሳታፊ ሃገሮች ከጨመረ በኃላ ይበልጥ የሚዛናዊ ፉክክር ስሜት ማነስ አጋጥሞታል። በዚህም የምድብ ጨዋታዎች ውጤት ተገማች እና ፉክክር አልባ ነበሩ። ከዚ ውጭም ከዚ ቀደም ትላልቅ የአውሮፓ ሊጎች በሚደረጉበት ወቅት እየተካሄደም የብዙዎች ትኩረት ሲስብ የነበረው ውድድር በአንፃራዊነት ብዙ ውድድር በሌለበት ወራት ተደርጎም የዓለም ቀልብ መሳብ ተስኖታል።
የፍፃሜ ጨዋታ
በአንድ ምድብ ውስጥ የነበሩት ሁለት ቡድኖች የሚያገናኘው ይህ የፍፃሜ ጨዋታ በርካታ ከዋክብት እና ተስፈኞችን ያቀፉ ሁለት ቡድኖች እንደማገናኘቱ ከጥሩ ፉክክር አልፎ ጥሩ ፍሰት ያለበት ጨዋታ ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ከውድድሩ መጀመር በፊት ለዋንጫ የታጩት በአሊዩ ሲሴ የሚመሩት የቴራንጋ አናብስት በጨዋታው ኮከብ ተከላካያቸውና እስካሁን አንድ ጎል ብቻ ያስተናገደው የተከላካይ መስመር መሪው ካሊዱ ኩሊባሊን በቅጣት ማጣታቸውን ተከትሎ ከወዲሁ በቡድኑ የመከላከል አጨዋወት ላይ ጥርጣሬዎች በዝተዋል። ቡድኑ የአልጀርያ ፈጣን የማጥቃት አጨዋወት የሚመክትበት መንገድም በጨዋታው ወሳኝ እና ተጠባቂ ነጥብ ነው።
ዩጋንዳ ፣ ቤኒን እና ቱኒዝያን በተመሳሳይ አንድ ለባዶ አሸንፈው ወደ ፍፃሜው ያለፉት ሴኔጋሎች በጥሎ ማለፉ ከፍተኛ የሆነ የግብ ማስቆጠር እና የፈጠራ እጦት ታይቶባቸዋል። ከወገብ በላይ ባለው የቡድኑ ብዙ አማራጭ አጣጥሞ መጠቀም ያልቻለው አሊዩ ሲሴ በፍፃሜ ጨዋታው የወርቃማው ትውልድ የማጥቃት ስብስብን ወደ ዋንጫ የመቀየር ግዴታ አለበት።
በውድድሩ ሳይጠበቁ ብዙዎች እያስገረሙ ወደ ፍፃሜው ያለፉት አልጀርያዎች በውድድሩ በነበራቸው ቆይታ ለዋንጫ ቀዳሚ ግምት ይሰጣቸዋል። በወጣቱ አሰልጣኝ ጀማል በልማዲ እየተመሩ ሁነኛ የውድድር ቡድን የሰሩት አልጀርያዎች ሴኔጋል፣ ኬንያ እና ታንዛኒያ የነበሩበት ምድብ በዘጠኝ ነጥብ በበላይነት ካጠናቀቁ በኃላ በጥሎ ማለፉ ጊኒ ( 3-0) ፣ አይቮሪኮስት (በፍ.ቅ 3-4) እና ናይጀርያን ( 2-1) አሸንፈው ነበር ወደ ፍፃሜው ጨዋታ ያለፉት።
በውድድሩ አስፈሪ የማጥቃት ክፍል የነበራቸው አልጀርያዎች በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ፉክክር የሚገኙ ሪያድ ማህሬዝ ፣ አዳም ኡናስ እና የሱፍ ቤላይሊን በመያዛቸው ካሊዱ ኩልባሊን ላጣው የሴኔጋል ተከላካይ ክፍል ከባድ ፈተና ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አሰልጣኞች
የፍፃሜው ጨዋታ የአፍሪካውን ቁንጮ ቡድን ከመለየት ባለፈ ልዩ ትርጉም የሚሰጠው ነው። ሁለቱም ብሔራዊ ቡድኖች የሚመሩት በሀገራቸው ዜጋ መሆኑ ያልተመደ ነው። በ1998 የቡርኪና ፋሶ አፍሪካ ዋንጫ የግብፁ መሐመድ ኤልጎሀሪ እና የደቡብ አፍሪካው ጆሞ ሶኖ ከተገናኙበት ፍፃሜ በኋላም ይህ የመጀመርያው ነው። የቀድሞዎቹ የብሔራዊ ቡድን አምበሎች አሊዩ ሲሴ (ሴኔጋል) እና ጀማል ቤልማዲ (አልጄርያ) የሀገራቸውን የዋንጫ ረሐብ ለማስታገስ ነገ የሚያደርጉት ፍልሚያ ምናልባትም ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ለሀገራቸው ዜጋ አሰልጣኞች ዕድል ስለመስጠት እንዲያስቡ ሊያደርጋቸው ይችላል።
ዳኛ
ጨዋታውን ካሜሩናዊው አሊዩ ሲዲ ይመሩታል። ትላንት 37ኛ ዓመታቸውን የደፈኑት ዳኛ በ2014 ዓለም ዋንጫ ማጣርያ ኢትዮጵያ በሜዳዋ በናይጄርያ 2-1 ስትሸነፍ ሳላዲን ሰዒድ ያስቆጠረውን ጎል በአጨቃጫቂ ሁኔታ ከመስመር አላለፈም በሚል በመሻራቸው በሀገራችን እግርኳስ ተመልካቾች የሚታወሱ ሲሆን በተከታታይ አምስት የአፍሪካ ዋንጫዎች ላይ ጨዋታዎችን መምራት ችለዋል። የሀገራቸው ዜጎች ኤቫሪስት ማንኬዋንዴ እና ኤልቪስ ኖፑዌ በረዳትነት የሚመሩ ናቸው።
* ጨዋታው ዓርብ ሐምሌ 12 ቀን 2011 በካይሮ ስታዲየም ከምሽቱ 4፡00 ይደረጋል።