የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ከረዳቶቻቸው ጋር በመሆን በርካታ ታዳጊዎች ያቀፈው አዳማ እግር ኳስ ፕሮጀክት የተሰኘ ማሰልጠኛን ጎብኝተዋል፡፡
በመላው ሀገሪቱ በመዞር የታዳጊዎችን የማሰልጠኛ ፕሮጀክቶችን በመጎብኘት፣ በማበረታታት እና በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ የቁሳቁስ ድጋፍን እያደረጉ የሚገኙት አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ አሁን ደግሞ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር አዳማ የሚገኙ ሲሆን እግረ መንገዳቸውን እድሜያቸው ከ13-15 እና 17 ዓመት በታች በጥቅሉ ከ60 በላይ ተስፈኛ ወንድ እና ሴት ተጫዋቾችን አቅፎ በሚሰራው አዳማ የእግር ኳስ ማሰልጠኛ ፕሮጀክት ከረዳቶቻቸው ሙሉጌታ ምህረት፣ ፋሲል ተካልኝ እና ውብሸት ደሳለኝ ጋር በመሆን ዛሬ ከሰዓት በመመልከት ለሰልጣኞቹ ምክር እና ንግግር አድርገዋል፡፡
አሰልጣኙ በንግግራቸው “የኢትዮጵያ የወደፊት የእግርኳስ ዕድገት በናንተው ልጆች እጅ ነው። ጠንክራችሁ በመስራት ለነገ ተተኪ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ትሆናላችሁ። ባላችሁ ነገር ላይ ቀጥሉ።” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል። አሰልጣኝ አብርሃም ለሶከር ኢትዮጵያ እንዳሉትም ለቀጣዮቹ ዓመታት በጊዜያዊ ውጤት ላይ ብቻ ማተኮር ሳይሆን በነዚህ ላይ በመስራት ቀጣይነት ያለው የጋራ ስራ በመስራት የማይቋረጥ ውጤት ለማምጣት ሁሉም የድርሻውን ይወጣ ብለዋል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡