የ2011 የኢትዮጵያ ዋንጫ (ጥሎ ማለፍ) የፍፃሜ ጨዋታ ዛሬ ረፋድ ቢሾፍቱ ላይ ተከናውኖ ፋሲል ከነማ እና ሀዋሳ ከተማ በመደበኛው ክፍለ ጊዜ 1-1 አጠናቀው በመለያ ምቶች ፋሲል 3-1 በማሸነፍ ባለ ድል ሆኗል፡፡
ከተያዘለት ደቂቃ ሠላሳ ደቂቃዎች ዘግይቶ የጀመረው ጨዋታ በክብር እንግድነት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ጂራ እና ምክትሉ ዐወል አብዱራሂም፣ ስራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት ዘሪሁን ቀቀቦን ጨምሮ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ የሁለቱን ክለብ ተጫዋቾች ከተዋወቁ በኃላ ጅማሮውን አድርጓል፡፡
ኳስን ለማንሸራሸር አመቺ ባልሆነው ሜዳ ምክንያት ረጃጅም ኳሶች የበዙበት ሆኖ በዋለው በመጀመሪያው አጋማሽ ፋሲል ከነማዎች በሱራፌል ዳኛቸው ላይ በተመሰረተ የማጥቃት አጨዋወት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ጠጣር የነበረውን የሀዋሳ የመከላከል አደረጃጀት አስከፍቶ ለመግባት ግን ሲቸገር ተስተውሏል፡፡ ሱራፌል ከቅጣት ምት የተገኙ ሁለት ኳሶችን አክርሮ መትቶ ሶሆሆ ሜንሳ ከያዘበት ውጪም በጉልህ መጠቀስ የሚችሉ የጠሩ አጋጣሚዎችን መመልከት አልቻልንም፡፡ በዚህ ሁኔታ በ13ኛው ደቂቃ በስታዲየሙ ባሉ ደጋፊዎች ዘንድ አድናቆትን ሲቸረው የነበረው እና በተደጋጋሚ የፋሲልን የተከላካይ ክፍል ሲያስጨንቅ የታየው መስፍን ታፈሰ ከተከላካዩ ሰዒድ ሀሰን እግር ስር የነጠቀውን ኳስ ወደ ሳጥን በፍጥነት በመግባት አስቆጥሮ ሀዋሳን ቀዳሚ አድርጓል፡፡
ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ያገኟቸውን ኳሶች ወደ ግብነት ለመለወጥ ጫና ፈጥረው የታዩት ዐፄዎቹ ያገኟቸውን ዕድሎችን መጠቀም ላይ ክፍተት ታይቶባቸዋል። 36ኛው ደቂቃ ላይ በግራ በኩል ከቅጣት ምት የተሻማችን ኳስ ያሬድ አመቻችቶ ሰጥቶት ፋሲል አስማማው በቀላሉ ወደ ውጪ የሰደዳት እና ሙጂብ ከሱራፌል የተቀበለውን ኳስ መትቶ ዳንኤል ተደርቦ ያስጣለው አጋጣሚ በመጀመርያው አጋማሽ የሚጠቀሱ ነበሩ።
ፋሲሎች ኢዙ አዙካን ከተጠባባቂ ወንበር አስነስተው የማጥቃት ኃይላቸውን በማጠናከር በጀመሩት ሁለተኛ አጋማሽ የእንቅስቃሴ ብልጫን ሲያሳዩ ሀዋሳዎች በመልሶ ማጥቃት ዕድል ለመፍጠር ሞክረዋል። ያኦ ኦሊቨር ከማዕዘን ያሻማውን አዲስዓለም በግንባር ገጭቶ ሳማኪ የያዘበት በሀዋሳ በኩል ተጠቃሿ ነበረች፡፡ ሱራፌል ከማዕዘን አሻምቶ ያሬድ ሲያበርድለት ከድር ኩሊባሊ መትቶ ለጥቂት የወጣችበት ደግሞ በፋሲል በኩል ትጠቀሳለች። 60ኛው ደቂቃ ላይ ኢዙ አዙካ እና የሀዋሳው ተከላካይ አክሊሉ ተፈራ የጋራ ኳስን ለመጠቀም በሚሻሙበት ሰዓት የዕለቱ ዳኛ ኳስ በእጅ ተነክቷል በሚል የፍፁም ቅጣት ምት የሰጡ ሲሆን ያሬድ ባየህ በአግባቡ ተጠቅሞ ፋሲልን አቻ አድርገል።
ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በተወሰነ መልኩ ወደ ጨዋታ እንቅስቃሴ ለመግባት የሞከሩት ሀዋሳዎች በአጥቂው መስፍን ታፈሰ አማካኝነት አጋጣሚዎችን የፈጠሩ ቢሆንም የተደራጀ የማጥቃት እንቅስቃሴ ባለማድረጋቸው በቀላሉ ሲባክኑ ታይቷል፡፡ 71ኛው ደቂቃ መስፍን ታፈሰ ከእስራኤል እሸቱ ተቀብሎ ጠንካራ ሙከራን ቢያደርግም ከድር ኩሊባሊ ተንሸራቶ ያዳነበት በሀዋሳ፤ 76ኛው ደቂቃ በቀኝ በኩል ዓለምብርሀን ብልጠቱን ተጠቅሞ የሰጠውን ኢዙ ወደ ሳጥን ገብቶ ከግብ ጠባቂ ሶሆሆ ጋር ተገናኝቶ ቢመታም ወደ ውጪ የወጣችበት በፋሲል በኩል ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች ነበሩ።
ከደጋፊዎቹ ድባብ ውጪ እምብዛም ማራኪ እንቅስቃሴ ያልታየበት ጨዋታ 1-1 ከተደመደመ በኋላ አሸናፊውን ለመለየት ወደ መለያ ምት በሚኬድበት ጊዜ ሜዳው አጥር ካለመኖሩ የተነሳ ተመልካቾች ወደ ሜዳ ለመግባት ጥረት ሲያደርጉ ከፀጥታ አካላት ጋር ግብ ግብ የነበረ ሲሆን የፀጥታ አባላትም ካረጋጉ በኋላ ወደ መለያ ምት አምርቷል።
በዚህ መሠረት ከተመቱት ምቶች ሀዋሳዎች ሦስት ሲስቱ፤ ሁለቱን የፋሲሉ ግብ ጠባቂ ሳማኬ መልሶ የእስራኤል እሸቱ ምት ወደ ውጪ ወጥታለች። ፋሲሎች ከመቱት ምቶች ሶሆሆ ሜንሳህ አንድ ሲያድን ቀሪዎቹ ከመረብ አርፈው በፋሲል 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ፋሲል ከነማም የ2011 የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ በመሆን የተዘጋጀለትን ዋንጫ ከፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ተረክቧል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡