የ2011 የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር ዛሬ ተጀመረ

ወደ አንደኛ ሊግ የሚገቡ ስምንት ቡድኖችን ለመለየት በ36 ክለቦች መካከል የሚካሄደው የክልል ክለቦች ሻምፒዮና ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

በሁለት ሜዳ ተከፍሎ በተጀመረው ውድድር በወጣት ማዕከል ሜዳ 03:00 ይጀምራል ተብሎ መርሐ ግብር የወጣለት ጨዋታ የሜዳው ቀኝ ጠርዝ ላይ ተከምሮ የነበረን አፈር ለማስተካከል ሲባል የነበረው ቁፋሮ ጨዋታው መጀመር ከነበረበት ጊዜ 40 ደቂቃ በማዘግየቱ ውድድሩ በአስገራሚ ክስተት ተከፍቷል።


ከሜዳው መስተካከል በኋላ 03 ድሬዳዋ ከ ቦዲቲ ከተማ ያገናኘው የመክፈቻ ጨዋታ ብዙም ሳቢ የሚባል ነገር ሳንመለከት ያለ ጎል 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት 03 ድሬዳዋዎች የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም ወደ ጎል በመቅረብ እና የጎል ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ የነበረባቸው ድክመት ጎል ለማስቆጠር እንዲቸገሩ አድርጓቸዋል። በአንፃሩ ቦዲቲዎች ጉልበታቸውን እና ፍጥነታቸውን በመጠቀም በአንድ ሁለት ቅብብል በረጃጅም ኳሶች ወደ ጎል በመድረስ አደጋ ለመፍጠር ቢሞክሩም ኳስና መረብን የሚያገናኝ አጥቂ ባለመኖሩ ጎል ለማስቆጠር ተቸግረዋል። በዚህም መሠረት ጨዋታው ምንም ጎል ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

05:00 የቀጠለው የሸዋሮቢት እና የኛ አዲስ ከቴ ጨዋታ ሸዋሮቢቶች በመጀመርያው አጋማሽ አከታትለው ባስቆጠራቸው ጎሎች 3-0 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል። በወጣት ተጫዋቾች የተደራጁት ሁለቱ ቡድኖች ያደረጉት ጨዋታ ጥሩ ፉክክር የተመለከትንበት ቢሆንም ሸዋሮቢቶች ያገኛቸውን የጎል አጋጣሚዎች በመጠቀም ከአዲስ ከቴ የተሻሉ በመሆናቸው አሸንፈው ሊወጡ ችለዋል። 6ኛው ደቂቃ ጣሂር መሐመድ ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ጎል በመምታት ባስቆጠረው ጎል ሸዋሮቢቶች ቀዳሚ መሆን ችለዋል። በዚህች ጎል የተነቃቁት ሸዋሮቢቶች በተደጋጋሚ ወደ ጎል በመድረስ ጠንካራ የጎል ዕድሎችን በመፍጠር የተሻሉ በመሆናቸው 16ኛው ደቂቃ ረድኤት አላዩ ከሳጥን ውጭ ግብጠባቂውን ከግብ ክልሉ መውጣቱን በማየት በጥሩ ሁኔታ ወደ ጎል መጥኖ የላካት ኳስ ሁለተኛ ጎል ሆና ተቆጥራለች። የሁለቱ ጎሎች በፍጥነት መቆጠራቸው በተወሰነ መልኩ የቡድኑን እንቅስቃሴ ቢያቀዘቅዘውም ኳሱን አደራጅተው በመጫወት ረገድ አዲስ ከቴዎች የተሻሉ ነበር ። ያገኙትን አጋጣሚዎች በመጠቀም ስኬታማ የነበሩት ሸዋሮቢቶች ግን 26ኛው ደቂቃ ረድኤት አላዩ ለቡድኑ ሦስተኛ ለእራሱ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል።

ከእረፍት መልስ በተደጋጋሚ ወደ ጎል መድረስ የቻሉት አዲስ ከቴዎች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን የጎል እድሎች ቢያገኙም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። 76ኛው ደቂቃ እስጢፋኖስ አክሊሉ ከመዕዘን ምት ደርቦ የተመለሰን ኳስ ወደ ጎልነት በመቀየር የአዲስ ከቴን ብቸኛ ጎል ሲያስቆጥር በቀሪ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ሌሎች ጎል መሆን የሚችሉ ዕድሎችን ሁለቱም ቡድኖች ሳይጠቀሙ ጨዋታው በሸዋሮቢት 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።


09:00 በአበበ ቢቂላ ሜዳ በተካሄደ የሲልቫ እና የዳውሮ አላላ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ጎል 0–0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ ከተጫዋቾቹ ጋር ሰላምታ በመለዋወጥ በተጀመረው በዚህ ጨዋታ ጠንካራ የሆነ በበርካታ የጎል ሙከራዎች ብንመለከትም ጎል መቆጠር ሳይችል ጨዋታው ያለ ጎል 0–0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።


በሌሎች ጨዋታዎች የተመዘገቡ ውጤቶች

ሐረር ቡና 0–0 ኩሩምኩ ከተማ
ሞጣ ከተማ 2–2 ሐውዜን ከተማ
ፍራውን ከተማ 6–2 ሐረር ዮናይትድ
አሚን ኑር 3–2 ደጋን ከተማ
ሙከየር 1–0 ዓድዋ ውሃ አገልግሎት

ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2011

03:00 | አሳይታ ከተማ ከ አባድር ሠላም (አበበ ቢቂላ ሜዳ)
03:00 | ካማሽ ከተማ ከ ምዕራብ ዐባያ (ወጣት ማዕከል ሜዳ)
05:00 | ኤጀሬ ከተማ ከ አቃቂ ማዞርያ ( አበበ ቢቂላ ሜዳ)
05:00 | ዶዶላ ከተማ ከ መከላከያ B (ወጣት ማዕከል ሜዳ)
07:00 | አኳ ድሬ ከ ሾኔ ከተማ (አበበ ቢቂላ ሜዳ)
07:00 | 02 ቀበሌ ድሬደዋ ከ ኣብዲ ሱሉልታ (ወጣት ማዕከል ሜዳ)
09:00 | ጂኮ ከተማ ከ ሐረር ሶፊ (አበበ ቢቂላ ሜዳ)
09:00 | ደጋ ዳሞት ከ ኮረም ከተማ (ወጣት ማዕከል ሜዳ)


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡