የ2020 የቻን ውድድር ላይ ለመሳተፍ የማጣሪያ ጨዋታውን ለማድረግ በዝግጅት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከጂቡቲው ጋር ላለበት የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ዝግጅቱን በአዳማ እያደረገ ይገኛል። ይህንን አስመልክቶም ዛሬ ከሰዓት በጁፒተር ሆቴል መግለጫ ተሰጥቷል።
የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ (ኢንስትራክተር) እና የቡድኑ አምበል አስቻለው ታመነ በሰጡት የ45 ደቂቃ መግለጫ ወቅታዊ የቡድኑ ዜናዎች እና ተያያዥ ጉዳዮች ለብዙሃን መገናኛዎች አብራርተዋል።
በቅድሚያ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ባሳለፍነው ሳምንት ጅማሮ ስለጀመሩት ልምምድ ገለፃ ማድረግ ጀምረዋል። “ልምምዳችንን ከረቡዕ ጀምሮ በአዳማ በጥሩ ሁኔታ እያከናወንን እንገኛለን። አዳማ ከገባንበት ዕለት አንስቶ በቀን ሁለት ጊዜ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሜዳ እንዲሁም በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በጥሩ ሁኔታ እየሰራን ነው። ወደ አዳማ ስናቀና በየቦታው ሁለት ሁለት ተጨዋቾችን በአጠቃላይ 23 ተጨዋቾችን ለመያዝ ሞክረናል። ይሁንና ከያዝናቸው 23 ተጨዋቾች ውስጥ አህመድ ረሺድ እና አቡበከር ናስር በጉዳት ምክንያት ሙሉ የልምምድ መርሃ ግብሩን እየወሰዱ አይደለም። ከእነሱ በተጨማሪ ሙጂብ ቃሲም የፓስፖርት ጉዳይ ስላልተጠናቀቀለት እና ወደ ጅቡቲ እስኪያናቀና ጉዳዩ ሊጠናቀቅ ስለማይችል ከስብስባችን ውጪ ሆኗል” ብለዋል። ነገር ግን አሰልጣኙ ስለ ሙጂብ አክለው በሰጡት መግለጫ ተጨዋቹ ቡድኑ ከጂቡቲ ሲመለስ እንደሚቀላቀል እና ለመልሱ ጨዋታ አብሮ እንደሚዘጋጅ ገልፀዋል።
አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ስለ ቡድኑ ወቅታዊ ሁኔታ ከገለፁ በኋላ በዝግጅት ጊዜ ፈተና ስለሆነባቸው ጉዳይ መናገር ቀጥለዋል። “በዝግጅታችን ትልቁ ፈተና የሆነብን ጉዳይ የተጨዋቾች የአካል ብቃት መውረድ ነው። ይህ ደግሞ የሆነው በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መቆራረጥ እና መንዛዛት ነው። ስለዚህ ይህንን ነገር ማስተካከል እንዳለብን በማመናችን ከአሰልጣኞች ቡድኑ ጋር እና ከምግብ ባለሙያው ጋር በመሆን ስራዎችን እየሰራን እንገኛለን” በማለት አስረድተዋል።
ከመግለጫው በኋላ የተለያዩ ጥያቄዎች ከብዙሃን መገናኛ አባላት የተሰነዘሩ ሲሆን መብራራት ያለበት ጉዳይ ላይ ማብራሪያ፤ በአጭሩ መመለስ ያለበት ጉዳይ ላይ መልስ ተሰጥቶበታል።
በተያያዘም ስለ 2021 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከአይቮሪኮስት፣ ማዳጋስካር እና ኒጀር የደረሳቸውን ድልድል አስመልክቶ እግረ መንገዳቸው የተጠየቁት አሰልጣኙ ምድቡን እንደማይፈሩ ተናግረው ” ምድቡን የሚመጥን ስራዎች ከሰራን እናልፋለን።” ብለው ሃሳባቸውን በአጭሩ ቋጭተዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡