ባህር ዳር ከተማዎች ከአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ጋር ከተለያዩ በኋላ ፊታቸውን ወደ ፋሲል ተካልኝ አዙረዋል።
ከአምስት ወራት በፊት አዲስ አመራር የሾመው ቡድኑ በ2012 ፕሪምየር ሊግ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ የመጀመሪያ ስራውን የአሰልጣኝ ቅጥር አድርጓል። ቡድኑ በመጀመሪያ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌን ለማምጣት አስቦ ሲንቀሳቀስ የነበረ ቢሆንም ከአሰልጣኙ ጋር ሳይስማሙ ቀርተው ድርድሩ ተቋርጧል። በመቀጠልም ፊታቸውን ወደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ያዞሩት ባህር ዳሮች ከአሰልጣኙ ጋር ድርድር ማድረጋቸውን ለማወቅ ተችሏል። ከዋሊያዎቹ ጋር የሚገኘው አሰልጣኙ እስካሁን በአካል ከቡድኑ አመራሮች ጋር ተገናኝቶ ማውራት ባይችልም በስልክ ሁለቱ አካላት እንደተስማሙ ከክለቡ አካባቢ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል። በቅርቡ ወደ ሀንጋሪ አምርቶ የአሰልጣኝነት ስልጠና የወሰደው ፋሲል ከእሁዱ የጅቡቲ ጨዋታ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በይፋ ፊርማውን ለባህር ዳር እንደሚያኖርም ይጠበቃል።
በተያያዘ ዜና ከ25 የባህር ዳር ተጨዋቾች ሁለት ተጨዋቾች (በዓመቱ አጋማሽ የፈረሙት ልደቱ ለማ እና ሚካኤል ዳኛቸው) ብቻ ውል እንዳላቸው የተነገረ ሲሆን በቀጣይ አሰልጣኙ ፊርማውን ካኖረ በኋላ ውል የሚራዘምላቸው እንዲሁም አዲስ ወደ ቡድኑ የሚመጡ ተጨዋቾች ተለይተው እንደሚታወቁ ተሰምቷል። ከዚህም በተጨማሪ አሰልጣኙ ምክትላቸውን እንዲሁም የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ራሳቸው እንዲመርጡ እንደሚደረግ ተገልጿል።
የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና መድን ድንቅ ተጫዋች ፋሲል ተካልኝ ወደ አሰልጣኝነት ከመጡ ወዲህ በቅዱስ ጊዮርጊስ (በጥቂት አጋጣሚዎች ዋና አሰልጣኝ) እና ብሔራዊ ቡድን ረዳትነት የሰሩ ሲሆን በቅርቡ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ” ዋና አሰልጣኝነት በህይወቴ የተራራ ያህል የገዘፈ ተደርጎ የሚታሰብ ነገር አይደለም፡፡ አሁን ስሜቴ (ምክትል አሰልጣኝነት) ‘በቃህ!’ እያለኝ ስለሆነ እድሉን ካገኘሁ ዋና አሰልጣኝ እሆናለሁ፡፡ ” ሲሉ ለዋና አሰልጣኝነት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡