አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ስለ ግብፅ የአፍሪካ ዋንጫ ቆይታቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል

በግብፅ አስተናጋጅነት በተከናወነው የ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በቴክኒክ ጥናት ቡድን ውስጥ ተካተው በሥፍራው የነበሩት አብርሃም መብራቱ (ኢንስትራክተር) ግብፅ ላይ ሲሰሯቸው ስለነበሩ ሥራዎች፣ ስላገኙት ልምድ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዛሬ በጁፒተር ሆቴል በነበረ መግለጫ ገለፃ አድርገዋል።

አሰልጣኙ በተመደቡበት የአሌክሳንድሪያ ግዛት የነበሩ ቡድኖችን አቋም ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር ሲተነትኑ እንደነበረ ያስረዱ ሲሆን በተለይ የቡድኖቹን አቋም ከልምምድ ጊዜ አንስቶ እስከ ዋናው የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ድረስ ተከታትለው ትንተናዎችን እንደሰጡ አስረድተዋል።

አሰልጣኙ ስለ ቆይታቸው ሲናገሩ ” በአፍሪካ ዋንጫ ቆይታዬ ትልልቅ ስም ካላቸው ዓለማቀፍ ተጨዋቾች ጋር እንዲሁም የቴክኒክ ክፍሉን ከሚያግዙ ታላላቅ የአህጉሪቱ ኢንስትራክተሮች ጋር የመገናኘት እና ልምዶችን የመቀያየር አጋጣሚ አግኝቻለው።” ብለዋል።

አሰልጣኙ ጨምረውም በቆይታቸው ሊጋችንን መገምገም እንዳለብን እንደተማሩ እና በሊጉ ሊሻሻሉ የሚገባቸውን ነገሮች ማሻሻል እንዳለብን ፤ ያ ካልሆነ ግን በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ስኬት ሊመጣ እንደማይችል እንደተገነዘቡ አስረድተዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ አሰልጣኙ በቅርብ ጊዜ ከዋሊያዎቹ ስፖንሰር ጋር በመተባበር የሊጉን ጠንካራ እና ደካማ ቴክኒካዊ ጎኖችን ከሙያተኞች ጋር ለመገምገም እንዳሰቡ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም የቡድኖች የዝግጅት ጊዜን፣ የወዳጅነት ጨዋታ ጥቅሞችን እንዲሁም የተለያዩ ዘመናዊ ስልጠናዎችን እውቀት ቀስመው እንደመጡ አስረድተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡