በአር ሲ በርካን እና ዛማሌክ መካከል የተደረገውን የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ የመራው በዓምላክ ተሰማ በወቅቱ የሞሮኮ ሮያል እግርኳስ ፌደሬሽን እና የካፍ ሁለተኛ ምክትል ፕሬዝዳንት ፋውዚ ሌካ ጥቃት እንደተሰነዘረበት ይታወሳል።
በዓምላክ ጨዋታውን በመራበት መንገድ ደስተኛ ያልነበሩት የዓመቱ “የካፍ ይድነቃቸው ተሰማ ሽልማት” አሸናፊ እና የኤሲ በርካን የክብር ፕሬዝዳንት ፋውዚ ሌካ በዓምላክ ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ለካፍ ክስ በማቅረብ ግለሰቡ እንዲቀጣ ደብዳቤ መላኩ ይታወሳል። ካፍም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽንን ክስ እና አቤቱታ በመስማት ግለሰቡን ለአንድ ዓመት ከእግር ኳስ እንዲታገዱ እንደወሰነ ሲነገር ቆይቷል።
በካፍ ውሳኔ ዙርያ የተለያዩ መረጃዎች በተለያዩ የአፍሪካ ሚዲያዎች እየተዘገበ ቢገኝም በዓምላክ ለጉዳዩ መቋጫ ያበጀለት ይመስላል። ዛሬ ከሰዓት ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ በነበረው ቆይታም ለፋውዚ ሌካ ይቅርታ ማድረጉን በይፋ አስታውቋል።
በዓምላክ በንግግሩ” ይቅርታ አድርጌለታለው። ይህንን ደግሞ ያደረኩት በራሴ ነው፤ ምክንያቱም ይቅር መባባል አለብን። እዚህ ውሳኔ ላይ እንድደርስ ማንም ጫና አላደረገብኝም።” በማለት በአጭሩ ውሳኔውን አስረድቷል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡