ቻን 2020 | የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነገ ወደ ጅቡቲ ያመራል

ከሀገር ውስጥ ሊግ በሚመረጡ ተጫዋች ብቻ በሚዋቀሩ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል የሚደረገው የቻን ማጣሪያ ከሳምንቱ መጨረሻ ጀምሮ ይካሄዳሉ። ዋልያዎቹም ለመጀመርያ ጨዋታ ነገ ወደ ጅቡቲ ያመራሉ።

ለዚህ የማጣሪያ ጨዋታ 23 ተጫዋቾችን በመያዝ ከአንድ ሳምንት በፊት በአዳማ ኤክስኪውቲቭ ሆቴል ማረፊያውን ያደረገው እና ልምምዱን በጂም እና በአዳማ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ካለፉት ሶስት ቀናት ወዲህ ደግሞ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በቀን አንድ ጊዜ ሲሰራ የቆየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 20 ተጫዋቾችን ጨምሮ 28 አባላትን በመያዝ ረፋድ 3:00 ወደ ጅቡቲ ይጓዛል፡፡

ቡድኑ ዝግጅት ከጀመረ ወዲህ ተከላካዩ ሙጂብ ቃሲም በፓስፖርት ጉዳይ ከመጀመሪያው የጅቡቲ ስብስብ ውጪ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ዛሬ ደግሞ በመጀመርያ ተሰላፊነት ይገባል የሚል ቅድመ ግምት አግኝቶ የነበረው ከሲዳማ ቡና የተመረጠው ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ እንደ ሙጂብ ሁሉ በተመሳሳይ ከፓስፖርት ጋር በተገናኘ ከሚጓዙት መሐል መካተት ሳይችል ቀርቷል። አጥቂው አቡበከር ናስርም ልምምድ ያልሰራ ሲሆን በጉዳት ምክንያት ወደ ጅቡቲ አያመራም፡፡

ቡድኑ ዛሬ አመሻሽ 11:00 በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ከጉዞው በፊት የመጨረሻ የሆነው ልምምዱን ሲያደርግ ለሁለት ተከፍለውም ጨዋታ አድርገዋል፡፡ ቡድኑ ነገ ወደ ስፍራው ካመራ በኋላ የፊታችን ዓርብ በሞቃታዋ ጅቡቲ የመጀመሪያ ጨዋታውን በማድረግ ቅዳሜ ተመልሶ የመልስ ጨዋታ በሚያደርግበት ድሬዳዋ ልምምዱን የሚቀጥል ይሆናል፡፡

ወደ ጅቡቲ የሚጓዙ 20 ተጫዋቾች

ግብ ጠባቂዎች፡ ተክለማርያም ሻንቆ (ሀዋሳ ከተማ)፣ ምንተስኖት አሎ (ባህር ዳር ከተማ)

ተከላካዮች፡ አስቻለው ታመነ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ደስታ ደሙ (ወልዋሎ)፣ ያሬድ ባዬ (ፋሲል ከተማ)፣ ወንድሜነህ ደረጀ (ባህር ዳር ከተማ)፣ አህመድ ረሺድ (ኢትዮጵያ ቡና) ጌቱ ኃይለማርያም (ሰበታ ከተማ)፣ አምሳሉ ጥላሁን (ፋሲል ከተማ)፣ ረመዳን የሱፍ (ስሑል ሽረ)

አማካዮች፡ አማኑኤል ዮሐንስ (ኢትዮጵያ ቡና)፣ ሙሉዓለም መስፍን (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ሐይደር ሸረፋ (መቐለ)፣ አፈወርቅ ኃይሉ (ወልዋሎ)፣ ሱራፌል ዳኛቸው (ፋሲል ከነማ)፣ ታፈሰ ሰለሞን (ሀዋሳ ከተማ)

አጥቂዎች፡ አቤል ያለው (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል (መቐለ)፣ ፍቃዱ ዓለሙ (መከላከያ)፣ አዲስ ግደይ (ሲዳማ ቡና)


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡