ወላይታ ድቻ በዚህ ሳምንት መጀመርያ የክለቡን ቀጣይ አሰልጣኝ ለመሾም በወጣው የአሰልጣኞች የቅጥር ማስታወቂያ መሠረት እስካሁን አራት አሰልጣኞች ለመወዳደር ማመልከቻቸውን ማስገባታቸው ታውቋል።
ማመልከቻቸውን ካስገቡት አሰልጣኞች መካከል ያለፉትን ሁለት ዓመታት ከከፍተኛ ሊግ እስከ ፕሪምየር ሊግ ባህር ዳር ከተማን በማሰልጠን ስኬታማ ቆይታ ያደረጉት የቀድሞ ኢትዮጵያ ቡና፣ ሱሉልታ ከተማ፣ ሰበታ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው (ማንጎ) አንዱ ናቸው።
በደቡብ ፖሊስ፣ ሀዋሳ ከተማ፣ አዳማ ከተማ፣ ደደቢት፣ ሲዳማ ቡና፣ ድሬደዋ ከተማ፣ ወልዲያ እና ደቡብ ፖሊስ አሰልጣኝነት የሚታወቁት እና ያለፉትን ወራት ክለብ አልባ የነበሩት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው (ሞውሪንሆ) የስራ ልምዳቸውን ካስገቡት መካከል ይገኙበታል።
በአርባምንጭ ከተማ እና በሲዳማ ቡና በነበራቸው ቆይታ የሚታወቁት እና ከ2011 የውድድር ዘመን አጋሓሽ በኋላ በሀምበሪቾ ያሳለፉት ዓለማየው ዓባይነህ (አሌኮ) ሌላኛው የስራ ልምዳቸውን ካስገቡ አሰልጣኞች መካከል ናቸው።
ሌላው በዲላ ከተማ ታዳጊዎችን በማሰልጠን እና በማብቃት የሚታወቁት በኃላ በከፍተኛ ዲላ ከተማ በዘንድሮ ዓመት ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ደቡብ ፖሊስን ሲያሰለጥኑ የቆዩት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራ የሰራ ልምዳቸውን ካስገቡት ውስጥ ይገኙበታል።
የፊታችን ዓርብ የመጨረሻ ቀኑ በሆነው የወላይታ ድቻ የአሰልጣኞች ቅጥር ማስታወቂያ ምንልባትም እየወጡ ካሉት መረጃ አንፃር ከተወዳዳሪዎቹ መካከል አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ቀጣዩ የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ የመሆናቸው ዕድል የሰፋ ይመስላል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡