አቤል ያለው ለጅቡቲው ጨዋታ ይደርስ ይሆን?

ለቻን 2020 ቅድመ ማጣሪያ ዓርብ አመሻሽ ከጅቡቲ ጋር የሚጫወተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ትላንት የመጀመርያ ልምምዱን ሲያደርግ አቤል ያለው ጉዳት አስተናግዷል።

ትናንት አመሻሽ ላይ የመጀመርያ ልምምዳቸውን በሀሰን ጉሌት ኦብቲዬዶ ስታዲየም ለአንድ ሰዓት የሰሩት ዋልያዎቹ በልምምድ ወቅት አጥቂው አቤል ያለው ባጋጠመው የጡንቻ መሳሳብ ጉዳት ምክንያት ልምምዱን አቋርጦ መውጣቱ ተነግሯል። በፈረሰኞቹ ቤት በጉዳት ምክንያት እንደታሰበው በቂ አገልግሎት ያልሰጠው አቤል ያለው ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ወደ ጅቡቲ ቢያቀናም በልምምድ ወቅት ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት ልምምድ አቋርጦ ስለመውጣቱ የፌዴሬሽኑ ህዝብ ግንኙኝፀነት ገልጿል። ይሁን እንጂ የጉዳቱ መጠን ምን ያህል ነው? ለዓርቡ ጨዋታ ይደርሳል ወይስ አይደርስም ስለሚለው ጉዳይ በዝርዝር አልተገለፀም።

“በዝግጅታችን ትልቁ ፈተና የሆነብን ጉዳይ የተጫዋቾች የአካል ብቃት መውረድ ነው። ይህ ደግሞ የሆነው በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መቆራረጥ እና መንዛዛት ነው። ስለዚህ ይህንን ነገር ማስተካከል እንዳለብን በማመናችን ከአሰልጣኞች ቡድኑ ጋር እና ከምግብ ባለሙያው ጋር በመሆን ስራዎችን እየሰራን እንገኛለን” በማለት በዝግጅታቸው ወቅት ፈተና ስለሆነባቸው ጉዳይ ለተናገሩት አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የአቤል ጉዳት ሌላ ፈተና ይዞ እንዳይመጣባቸው ተሰግቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡