በክልል ክለቦች ሻምፒዮና ቦዲቲ ከተማ ከውድድሩ በመሰረዙ ቅሬታውን አሰምቷል

ቦዲቲ ከተማ ከክልል ክለቦች ሻምፒዮና እየተወዳደርኩ ካለሁበት ውድድር ያላግባብ ታግጃለው በማለት ቅሬታውን አሰምቷል።

የ2011 የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና ከሐምሌ 14 ጀምሮ በ36 ክለቦች መካከል በስምንት ምድብ ተከፍሎ የሚካሄደው ውድድር አራተኛ ቀኑ ላይ ደርሷል። በምድብ 3 ተደልድሎ የመጀመርያ ጨዋታውን ከ03 ድሬዳዋ ጋር በማድረግ 0-0 የተለያየው ቦዲቲ ከተማ የምድቡን ሁለተኛ ጨዋታውን ዛሬ 03:00 ላይ ከሸዋሮቢት ጋር እንዲጫወት መርሐግብር ወጥቶለት ነበር። ይሁን እንጂ ሰዓቱን አክብሮ በሜዳ በተገኘበት ሰዓት ከውድድሩ መታገዱ ተነግሮታል።

አቶ ዋሲሁን ወ/ዮሐንስ የቦዲቲ ክለብ የቡድን መሪ ለሶኮር ኢትዮጵያ ሲናገሩ ” ሀዋሳ ፕላኔት የሚባል ክለብ በበጀት ዕጥረት ምክንያት እንደማይሳተፍ ሲያሳውቅ እኛ በእርሱ ምትክ እንድንሳተፍ የደቡብ እግርኳስ ፌዴሬሽን በፃፈልን ደብዳቤ በመሠረት አስፈላጊውን የምዝገባ ክፍያ በመፈፀም የዕጣ ማውጣት ስነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተን የመጀመርያ ጨዋታችንም ማድረግ ችለን ነበር። ትናንት በደረሰን አዲስ የውድድር መርሐ ግብርም የዛሬውን ጨዋታ እንደምናደርግ የሚገልፅ ነበር። ሆኖም ጨዋታው ሰዓት ሜዳ ብንገኝም ተጋጣሚ ቡድናችን ሸዋሮቢት በሜዳው ላይ ልምምድ ሲሰራ ተመልክተን አንድም የውድድር ኮሜቴ ሳናገኝ በአሳዛኝ ሁኔታ ተመልሰናል። ፌዴሬሽኑ እኛን ከውድድር ያገደበት ምክንያቱ ምን እንደሆነ በኮሚኒኬም ሆነ በደብዳቤ እንዲያሳውቀን ብንጠይቅም ምላሽ አጥተናል። ክለባችን ላይ ከፍተኛ ደባ ተፈፅሟል፤ ፍትህም አጥተናል።” ብለዋል።

ከፌዴሬሽኑ በኩል ክለቡ ከውድድር የወጣበት ምክንያት ምን እንደሆነ ለማወቅ ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቢቀርም አሁን ፌዴሬሽኑ ቦዲቲ ከተማን ያገደበትን ምክንያት በኮምኒኬ ይፋ አድርጓል። ሆኖም ” ከደቡብ ስፖርት ኮሚሽን ከውድድሩ እንዲሰረዝ በመጣ ደብዳቤ መሠረት ተሰርዟል ” ከማለት ውጪ ከውድድር ስለመታገዱ ዝርዝር ምክንያት አልገለፀም።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡