ሮበርት ኦዶንካራ የዲዲዬ ጎሜስን ቡድን ተቀላቀለ


በአዳማ ከተማ የውድድር ዘመኑን ያሳለፈው ሮበርት ኦዶንካራ ወደ ጊኒው ሆሮያ የሚያደርገውን ዝውውር አጠናቋል።

ዩጋንዳዊው ግብ ጠባቂ የተቀላቀለው የጊኒው የሁለትዮሽ ዋንጫ አሸናፊ በቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ የሚመራ ሲሆን አሰልጣኙ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ የሮበርትን እንቅስቃሴ በቅርበት እንደሚከታተሉና ምርጫቸው እንዳደረጉት ተገልጿል። የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ጠባቂ ወደ ጊኒ ላደረገው ዝውውር ቢኒያም ሚደቅሳ የተባለ ግለሰብ የማመቻቸት ሥራ የሰራ ሲሆን በሆሮያ የህክምና ምርመራውን በተሳካ ሁኔታ ካከናወነ በኋላ የ2 ዓመት ኮንትራት ተፈራርሟል።

ሮበርት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ ከታዩ ድንቅ ግብ ጠባቂዎች አንዱ ሲሆን በ2003 አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከተቀላቀለ በኋላ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት መጀመርያ ወደ አዳማ እስካመራበት ጊዜ ድረስ ለአራት ተከታታይ ዓመታት የሊጉ ኮከብ ግብ ጠባቂ ሆኖ ሲመረጥ ለረጅም ደቂቃዎች ግብ ባለማስተናገድም ባለሪከርድ መሆን ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡