ሽመልስ በቀለ በፔትሮጀት የመሰለፍ ዕድል ተነፍጎታል

 

ከሃገር ውጪ ለሚጫወቱ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾችን የውድድር ዘመኑ የሚመች አልሆነም፡፡ በግብፅ ፕሪምየር ሊግ ለፔትሮጀት የሚጫወተው ሽመልስ በቀለም በክለቡ የመሰለፍ ዕድል እያገኘ አይደለም፡፡

ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ድንቅ ብቃቱን ያሳየው የዋልያዎቹ የአጥቂ አማካይ በተለይ ከውድድር ዘመን አጋማሽ ጀምሮ ባሳየው ድንቅ ብቃት የፖርቹጋሉ ስፖርቲንግ ሊዝበንን ለመቀላቀል ከጫፍ ደርሶም ነበር፡፡

ነገር ግን በ2015/16 የውድድር ዘመን በተቃራኒው የተሳካ ጊዜ ማሳለፍ እየተሳነው ይገኛል፡፡

በተለይም የቀድሞ የግብፅ ብሄራዊ ቡድን የመሃል ሜዳ ተጫዋች አህመድ ከክለቡ ከተለያየ በኃላ ሽመልስ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ለመግባት እየተሳነው መጥቷል፡፡

ባሰለፍነው ረቡዕ ፔትሮጀት ከሜዳው ውጪ ሃራስ ኤል ሆዶድን በአሌክስሳንደሪያ 2-0 ባሸነፈበት ጨዋታ ሽመልስ በ87ኛው ደቂቃ አህመድ ጋፍርን ቀይሮ ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡ ለፔትሮጀት የድል ግቦቹን ኦሳማ መሃመድ እና ጄምስ ኦዎቦስኪኒ አስገኘተዋል፡፡ ፔትሮጀት በሊጉ በ19 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

ዓምና በሊጉ 7 ግቦችን ያስቆጠረው ሽመልስ በግብፅ እግርኳስ ላይ ትኩረት ሰጥቶ በሚሰራው የኪንግፉት ድረ ገፅ ወደ አውሮፓ ሊጎች ሂደው መጫወት ከሚችሉ 10 የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ተጫዋቾች መካከል አስቀምጦት እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡

ያጋሩ