ሎዛ አበራ ለሙከራ ወደ ማልታ ታቀናለች

ሎዛ አበራ በሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ቅድመ ማጣርያ ለሚሳተፈው የማልታው ቻምፒዮን ቢርኪርካራ ለመጫወት የሙከራ ዕድል አገኘች።

ባለፈው የውድድር ዓመት አጋማሽ በስዊድኑ ከንግስባካ የሙከራ ጊዜን አሳልፋ በሁለተኛው ዙር ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ ለአዳማ ከተማ በመፈርም የፕሪምየር ሊግ አሸናፊ የሆነችው ሎዛ አበራ ወደ ማልታ ሰኞ የምታመራ ሲሆን በክለቡ የአንድ ሳምንት የሙከራ ጊዜ እንደምታሳልፍ ሒደቱን የሚመራው ወኪሏ ሳምሶን ናስሮ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል። ተጫዋቿ ወደ ክለቡ አምርታ የምትጫወትበት ዕድል የሰፋ እንደሆነ እና ከሷ ውጭም ሌሎች ኢትዮጵያውያን በሌሎች ሀገራት የመጫወት ዕድል እንዲያገኙ በድርጅታቸው ሰርነስ ሶከር ኤጀንሲ አማካኝነት እየሰሩ እንደሆነም ወኪሉ ጨምሮ ገልጿል።

በ1999 የተመሰረተው ክለቡ የሀገሪቱን የሴቶች ሊግ ላለፉት ተከታታይ ሦስት ዓመታት ያነሳ ሲሆን በ2019/20 የውድድር ዓመትም በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የማጣርያ ውድድር ላይ ከአየርላንዱ ዌክስፎርድ፣ ከአልቤንያው ቭላዝኒያ እና ከሉቲኒያው ጂንትራ ጋር ተጫውቶ ምድቡን በበላይነት ካጠናቀቀ ወደ ዋናው የምድብ ድልድል የሚካተት ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡